Friday 6 June 2014

እህት ብርቱካን ወደ ቦታሽ ተመለሽ – ግርማ ካሳ


አንድ ፎቶ አየሁ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጥቁር ጋዉን አድርጋ፤ ይመስለኛል በማስተር ዲግሪ ተመርቃ። ለርሷም ለቤተሰቦቿም እንኳን ደሳ አላችሁ እላለሁ።

ኢ.ኤም.ኤፍ፣ ወ/ት ብርቱካን ወደ ፖለቲካ እንደማትመለስ፣ ምናልባትም ኑሮዋን በዉጭ አገር ልታደርግ እንደምትችል ዘግቧል። ጋዜጠኛ አበበ ገላው በበኩሉ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለከፈለችው ታላቅ መስዋእትነት አድናቆቱን ገልጾ፣ «You are a truly phenomenal woman that must continue to fight in the battles we have not yet finished» ብርቱካን የጀመረችውን እንድትጨርስ ያበረታታል።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አቶ መለስ ባረፉበት ጊዜ ለአዉራምባ ታይምስ ከሰጠችው ቃለ ምልልስ በኋላ ብዙ ተሰምታ አታውቅም። «ፖለቲከኛ ዝም ብሎ አይቀመጥም። ብርቱካንም ይሄን ያል ጊዜ ዝምታን ከመረጠች ፖለቲካዉን ብትተወው ነው» ከሚል ይሆናል፣ ኢ.ኤም.ኤፍ ወደ ፖለቲካ አትመለስም ሲል የዘገበው።

ወ/ት ብርቱካን እስከ አሁን ድረስ በትምህርት ላይ ነበረች። ከዚህ በኋላ በፊቷ ብዙ አማራጮች አሏት። ኑሮዋን በዉጭ አገር አድርጋ ፣ በአንድ አለም አቀፍ ድርጅት ተቀጥራ፣ ብትኖር የሚቀየም ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም። ይች እህት ብዙ ዋጋ የከፈለች፣ ለትግሉ ብዙ ያበረከተች ታላቅ ሴት ናትና። እንደ ቀድሞ አድናቂዋ ዉሳኔዋን በጣም ነው የማከብርላት፤ ለምን ቢባል ከማንም የበለጠ ለርሷና ለቤትሰቧ የሚጠቅመዉን የምታወቀዉ እርሷ እራሷ በመሆኗ።

ወደ አገር ቤት ተመልሳ ከፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ ዉጭ፣ አገሯን እና ሕዝቡን ለመጥቀም ፍላጎት ይኖራትም ይሆናል። አገርና ሕዝብን ለመርዳት የግድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን የለብንም። ይሄንንም አማራጭ አከብርላታለሁ።

ከላይ የተጠቀሱትን አማራጮችን «አክብርላታለሁ» ስል ግን «አላስከፋኝም» ማለት እንዳልሆነ እንዲታወቅለኝ እፈልጋለሁ። ብርቱካን ሚደቅሳ ለብዙዎች የኢትዮጵያ አን ሳን ሱኪ ነበረች። ብዙ ዋጋ ከፍላለች። እርሷ ዝምታን እንድትመርጥ፣ ከፖለቲካው እንድትወጣ አሳሪዎቿ አሰቃይተዋታል። ከፖለቲካዉ ከወጣች እነርሱ እንዳሸነፉ፣ እንደተሳካላቸው አድርጌ ነው የምቆጠረው።

ለርሷ ያለኝ ምክር አጭርና ቀላል ነው። «የድሮ ፓርቲሽን ፣ አንድነትን ተቀላቀዪ።» እላታለሁ። አንድነት በሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ፣ በአገሪቷ ሁሉ ጠንካራ የሰለጠ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በአዲስ አበባ ….በቅርቡ የተደረጉትን ሰላማዊ ሰልፎች በማድረግ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ ተችሏል። የፊታችን እሁድ ሰኔ አንድ ቀን ፣ በኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ፣ በአማራዉ ክልል በደብረ ማርቆስና በደቡብ ክልል በቁጫ ወረዳ ሕዝቡ ድምጹን ያሰማል። ለጥቆም በአዋሳ፣ በአርማጭሆ፣ በወገራ፣ በነቀምቴ፣ በድረዳዋ በመቀሌ እያለ የነጻነት ደዉል ይደወላል።

አንድነት ኢሕአዴግን መቃወም ሳይሆን ግልጽና የተጨበጡ የፖሊሲ አማራጮችን ለማቅረብ ሰነዶች እያዘጋጀ ነው።
ተቃዋሚዎች ሲከፋፈሉ ነው የምናውቀው። አንድነት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር እየተዋሃደ ነው። በቅርቡ ከመኢአድ ጋር የቅድመ ዉህደት ስምምነት ይፈርማል። ቀጥሎ 33ቱ ተብለው የሚታወቁ፣ እየተዋሃዱ ወደ 8 የደረሱትንና ትብብር ተብለው ከሚታወቁት ጋር የዉህደት ንግግር ጥሩ ዉጤት እያመጣ እንደሆነ ይሰማል። አንድነት የኢትዮጵያን ሕዝብን በአንድነት በቶኩማ ዙሪያ፣ ለነጻነት ለቢሊሱማ እያሰባሰበ ነው።

ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ለአንድነት ፓርቲ፣ ለሚሊዮኖች ንቅናቄ ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍትህና ለእኩልነት ለሚያደርገው ወሳኝ ትግል ታስፈልጋለች። እኔም ሆንኩ በሚሊዮኖች የምንቆጠር የቀድሞ አድናቂዎቿ፣ ብርቱካን ተመልሳ የነጻነትን ችቦ እንድትይዝ እንማጸናለታለን። ቃሊቲ እሥር ቤት እያለች ብርቱካን አንድ ጽሑፍ አስነብባን ነበር። ጽሁፏን ስታጠቃልል፣ «ሰው ያለ ነጻነቱ ምንድን ነው ?» ነበር ያለችው።

0 comments:

Post a Comment