Saturday 21 June 2014

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትና ኢህአዴግ

                                     10250324_10202266872494109_591151525615905132_n

በዳዊት ሰለሞን


ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትና ኢህአዴግ

አለማችን ለጋዜጠኞች፣ለብሎገሮችና ሐሳባቸውን በመግለጽ ተፈጥሯዊ መብታቸውን ለሚጠቀሙ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ገሃነማዊ መልክ እየተላበሰች ትገኛለች፡፡በሶሪያ፣ሶማሊያ፣ኢራቅ፣አፍጋኒስታን፣ሊቢያ ፣ግብጽና ዮክሬይን የተፈጠሩ ሰብኣዊ ቀውሶች የጋዜጠኞችና ጦማሪያን ህይወትን በልተዋል፡፡ የቀውሱ ሃይሎች ጋዜጠኞቹንና ጦማሪያኑን የመጀመሪያ ኢላማቸው በማድረጋቸውም ዛሬ በእነዚህ አገራት በሚገኙ ማጎሪያዎች ስቃይ እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡በዚህ ዓመት ብቻ በእነዚህ አካባቢዎች የ27 ጋዜጠኞች ህይወት ተቀጥፏል፡፡
በግብጽ እስር ቤት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ለወራት የዘለቁበት የርሃብ አድማ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ጆሮ መሳብ አለመቻሉም በአለማቸን የጋዜጠኞች ህይወት እንደ ተራ ነገር እየተቆጠረ ለመምጣቱ ማሳያ ነው፡፡
በአለማችን ከሚገኙ 197 አገራት መካከል የነጻ ፕሬስ አየር የሚነፍስባቸው አገራት ቁጥር 14 እንደማይደርስም ሰሞነኛ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ሀሳብን ለመግለጽ ነጻነት የተለየ ስፍራ ትሰጣለች የምትባለው አሜሪካ አንኳን ለዊኪሊክስ መረጃ የሚመግቡ ሰዎችን የማደን ስራ ተጀምሯል፣የናሳ አናሊስት የነበረው ኤድዋርድ ስኖውደን ለህይወቱ በመስጋት ስደትን መርጧል፣የሲአይኤ ሰዎች የአሶሼይትድ ፕሬስ ቢሮን ስልክ ጠልፈው ለጋዜጣው ይደርሱ የነበሩ ጥቆማዎችን ሲቀዱ መክረማቸው ተደርሶበታል፡፡
እነዚህ ነጥቦች የማነሳው አጠቃላይ የሆነ ስዕል እንዲኖረን እንጂ እንኳን በኢትዮጵያ በአሜሪካም ጋዜጠኞች ይሰለላሉ፣ይታሰራሉ፣ቶርች ይደረጋሉ ወይም ይገደላሉ ለማለት እንዳልሆነ ተገንዘቡልኝ፡፡

ኢህአዴግና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት—–

ኢህአዴግ ምን አይነት ግምባር ነው ? ግምባሩ ሀሳብን በመግለጽ ነጻነት ዙሪያ ያለውን አቋም ለማወቅ በግምባሩ ውስጥ በዚህ ዙሪያ ያለውን እውነታ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ግምባሩ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ተራ አባሉ ድረስ ሀሳብ የሚፋጭበት፣የሀሳብ ልዩነቶች ለአቅመ ክርክር ቀርበው በተለመደው የአብዛኛው ድምጽ የሚረቱበትን አሰራር የዘረጋ አይደለም፡፡ከዚህ ይልቅ ሀሳብ፣እቅድ፣ሪፖርትና የአይድኦሎጂ ትንተና ከላይ ወደ ታች የሚወርድበት ግምባር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የግምባሩ ጭንቅላት ተደርገው ይወሰዱ የነበሩት ሟቹ መለስ ዜናዊ የተናገሩትን አሜን ብሎ መቀበልና ያንኑ እንደ ገደል ማሚቱ ማስተጋባት የግምባሩ አባላት ዕጣ ፈንታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ከመሪው የተለየ ሐሳብ ይዘው የተገኙና ይህንኑ ለማራመድ የሞከሩ ‹‹ጋንግሪን፣ተንበርካኪ፣ጸረ ድርጅት፣ወዘተርፈ እየተባለ ለእስርና ለስደት ይዳረጋሉ፡፡
በአንድ ወቅት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ መለስን ‹‹ መንግስቱ ሀይለማርያምን መሰልከኝ በማለታቸው እነ ወይዘሮ ገነት ዘውዴ ምርር ብለው ሲያለቅሱ ያየናቸውም ግምባሩ ውስጥ ሀሳብን መግለጽ ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ነው፡፡ገነት መለስ መንግስቱን አለመሆናቸውን ከማስረዳት ይልቅ ወይም ነጋሶን ከመለስ ያነጻጸሩበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ከመጠየቅ ለቅሶ ቀድሟቸዋል፡፡ነጋሶም እግዜርን በቤተመቅደስ የሰደቡ ያህል ተቆጥሮባቸው እንትን የነካው እንጨት ተደርጋዋል፡፡
ኢህአዴግ የሀሳብ ፍትጊያ የሚከናወንበት ግምባር አለመሆኑን ለማየት ፓርላማውን መመልከትም አስረጂ ነው፡፡ካሉት 547 ወንበሮች 546ቱን የያዘው ኢህአዴግ(ዶክተር አሸብር በይፋ የኢህአዴግ ደጋፊ መሆናቸውን በመናገራቸው አንዱን ወንበር የግል አድርገን መቁጠራችን ስህተት ይመስለኛል)በፓርላማው አዋጆች ከመጽደቃቸው በፊት ወይም ሪፖርቶች ሲቀርቡ ደመቅ ያለ ክርክር ቀርቶ የሀሳብ ልዮነት የመትመስል ነገር እንኳን አንመለከትም፡፡ይህ ከየት መነጨ?የፓርላማ አባላቱ ፓርላማ ከመግባታቸው በፊት የግምባሩ አባላት ነበሩ፡፡በግምባሩ ቆይታቸው በሀሳብ ላይ የሚከራከሩበት ልምድ አዳብረው ቢሆን የህንድ አይነት ፓርላማ ለማየት ባንታደል እንኳን እንዲህ አይነት ፓርላማ አይኖረንም ነበር፡፡(ከሱማሌ ክልል የመጡ አንድ የፓርላማ አባል እጃቸውን አውጥው እንዲናገሩ እድል ሲሰጣቸው እኔ እኮ አብዱል መጂድ ሁሴን እጃቸውን ሲያወጡ ለድጋፍ መስሎኝ ነው ማለታቸውን አልዘነጋውም)

ኢህአዴግ ከግምባሩ ውጪ

ገዢው ፓርቲ እመራበት ዘንድ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሰጡኝ ህገ መንግስት ነው በሚለው ሰነዱ የሚዲያ ነጻነት፣ሀሳብን የመግለጽ መብት፣የመደራጀት፣ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራስን አመለካከት የማራመድ መብት የመሳሰሉትን እንደሚያከብር ምሎ የተገዘተ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነታ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ሰው ያለውን እንጂ የሌለውን ሊሰጥ አይችልም፡፡
ግምባሩ ለአባላቱ ያልሰጠውን፣ያላሳየውን ለሌላው ይሰጣል በማለት መጠበቅም ስስነት ነው፡፡ላለፉት 23 ዓመታት ሚዲያውን ግምባሩ እንደ ጠላት እየተመለከተው የዘለቀውም በቤቱ ውስጥ የሀሳብና ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ባለመለመዱ ነው፡፡ ሚዲያ እንደ አራተኛ የመንግስት አካል መታየት የሚኖርበት ቢሆንም ኢህአዴግ ሚዲያውን በጠላትነት ይፈርጀዋል፡፡ጠላት ደግሞ በተገኘበት ሁሉ ይደበደባልና ይህው እየተከናወነ ነው፡፡
የዞን ዘጠኞችና የሶስቱ ጋዜጠኞች ድንገተኛ እስር
ኢመደበኛ በማለት የሰየሙትን የጡመራ መድረክ የሰረቱ ወጣቶች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለራሳቸው፣ለሚኖሩበት ማህበረሰብና ለአገራቸው ርዕይ ሰንቀዋል፡፡ራዕያቸው የሀሳብ የበላይነት የነገሰባት፣ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት የሚዳኝ የፍትህ ስርዓት የተዘረጋባት አገር ማየት ነበር፡፡
ዞን ዘጠኞች በህቡዕ የተደራጁ አልነበሩም በሶሻል ሚዲያ የሚያቀርቧቸውን ጽሁፎች ከእነ ሙሉ ስማቸውና ፎቶ ግራፋቸው በማስደገፍ ያቀርቡ ነበር፡፡በህቡዕ የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ደግሞ ይህንን ሊያደርግ አይችልም፡፡

ጥያቄዎቻቸው ምንድን ነበሩ

በሶሻል ሚዲያ ካደረጓቸው ካምፔኖች መገንዘብ እንደሚቻለው ገዢው ፓርቲ ህገ መንግስቱን እንዲያከብር ፣ፍትህ እንዲሰፍን፣የመሰብሰብ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች ከወረቀት ላይ ድንጋጌ ወርደው መሬት ላይ እንዲተገበሩ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡አያያዛቸውና የክስ ሂደቱበፍቃዱ ሀይሉና አቤል ዋበላ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በመርማሪዎቻቸው ቶርች እንደተደረጉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ይህ ህገ መንግስቱን መጣስ፣አለም አቀፍ የህግ ድንጋጌዎችን መጨፍለቅ ከመሆኑም በላይ በተያዙ ሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸም መቼም ቢሆን በይርጋ የማይታለፍ ወንጀል ነው፡፡(ህገ መንገስት አንቀጽ 28)

አስሮ መረጃ ማሳደድ

ይህ እጅግ ኋለ ቀር የሆነ መንገድ ነው፡፡አንድን ሰው አስረህ መረጃ መፈለግ በዘመናዊ መንገድ የሰለጠነ፣በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚመራ ለሚሰኝ መርማሪ አካል የሚመጥን አይደለም፡፡በዚህ ላይ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ለፖሊስ የስልክ ፣የፋክስ፣የሬዲዩ ፣የኢንተርኔት ፣የአሌሌክትሮኒክስ፣የፖስታና የመሳሰሉ ግኑኝነቶችን መጥለፍና ወደማናቸውም ቤት በሚስጥር ለመግባት ይህንኑ ለመፈጸም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ እንዲችል ይፈቅዳል፡፡
ይህን ሁሉ የማድረግ ፈቃድና አቅም እንዳገኘ የሚነገርለት ፖሊስ ብሎገሮቹንና ሶስቱን ጋዜጠኞች ላለፉት 57 ቀናት አስሮ ለፍርድ ቤት ምርመራውን አለመጠናቀቁን እየተናገረ ነው፡፡በጸረ ሽብር አዋጁ የተቀመጠውን የአራት ወር ቀጠሮ የመጠቀሚያ መብት ፖሊስ ግምት ውስጥ አስገብቶ ምንም አይነት የሚታይ ስራ ሳይሰራ ቀኑ ሲቀርብበት ያንኑ የተለመደ ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ እያስተዋልነው ነው፡፡ፖሊስ አዋጁ የሚሰጠውን ቤት የመበርበር፣ስልክ፣የመጥለፍና ኢሜሎችን የመፈተሽ መብቱን በመጠቀም ልጆቹ ላይ በቂ መረጃ ከሰበሰበ በኋላ ቢያስራቸው ምን የሚያጣው ነገር ነበር?ተጠርጣሪዎቹ ከአገር ሊወጡ ይችላሉ ብሎ ከገመተም የቦሌን በር እንዴት መቆጣጠር እንደሚችል የሚጠፋው አይመስለኝም፡፡ፖሊስ ይህንን ማድረግ ችሎም ቢሆን አሁን እየተሰነዘረበት ከሚገኘው ትችት አይድንም ነበርን?ማን ያውቃል ፖሊስ የእስር እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ምርመራ ላይ ጊዜውን አጥፍቶ ቢሆን ልጆቹን ለማሰር የሚያነሳሳውን ምክንያት ሊያጣ ይችል ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

0 comments:

Post a Comment