የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በሀዋሳ ከተማ ሰኔ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ሊያካሂደው የነበረውን ህዝባዊ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ አባላት ባለፈው ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የዋስትና መብታቸው ተነፍጎ በግዜ ቀጠሮ ለአርብ ሰኔ 20 ቀን 2006 ዓ.ም የተቀጠሩ ቢሆንም በዛሬው እለት ሰኔ 18 ቀን 2006 ዓ.ም ከተሰጠው ቀጠሮ 2 ቀን አስቀድሞ አቃቤ ህግ ምስክሮቼን አርብ እለት ለማቅረብ ስለማልችል ዛሬ ያደመጡልኝ በማለቱ ምክንያት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡የተቀጠርነው ለዓርብ በመሆኑ የፓርቲአችንን ጠበቃ ሳናቀርብም ሆነ ሳናማክር የዓቃቤ ህግ የምስክሮች ቃል ሊደመጥ አይገባም በማለት ለፍርድ ቤቱ ተቃውሞአቸውን ታሳሪዎች ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ በመታዘዙ የ5 ምስክሮችን ቃል አስደምጧል፡፡የምስክሮቹ ቃል ከተደመጠ በኋላ የመሀል ዳኛው በመጀመሪያው ቀነ ቀጠሮ ታሳሪዎች የዋስትና መብታቸው የተነሳው አቃቤ ህግ ታሳሪዎች መረጃዎችን የማጥፋት ብቃት ስላላቸውና በምስክሮቼ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል በማለት በጠየቀው መሰረት መሆኑንና አሁን ግን አቃቤ ህግ ምስክሮቹን አሰምቶ በመጨረሱ ፍ/ቤቱ ተከላከሉ አለበለዚያ ሊያስጠይቃችሁ አይችልም የሚለውን ብይን ለመስጠት ለሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም የቀጠረ መሆኑንና ታሳሪዎች እያንዳንዳቸው በ5000(አምስት ሺ ብር) ዋስትና በማስያዝ ጉዳያቸውን ከውጭ ሆነው መከታተል እንደሚችሉ አሰረድተዋል ፡፡ታሳሪዎች በበኩላቸው እኛ ህገመንግስታዊ መብታችንን ተጠቅመን እንጂ የፈፀምነው ወንጀል ሳይኖር ልንጠየቅ አይገባም የተባለውን ያህል መጠን ገንዘብም ለማቅረብ እንቸገራለን ብለዋል ፡፡የማሀል ዳኛው የተጠቀሰውን ገንዘብ ማስያዝ የማትችሉ ከሆነ ብይን እስኪሰጥማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ የእለቱ ችሎት አብቅቷል፡
0 comments:
Post a Comment