Monday 23 June 2014

በደቡብ ክልል በግንቦት 3/2006 በጐፋ ሳውላ በተደረገው የመኢአድ የተቃውሞ ሠላማዊ ሰልፍ ምክንያት በመኢአድ አባላት ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡-ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ


                                                         images

ኢህአዴግ የግንቦት 3 ቀን 2006 ዓ.ም የጐፋ ሳውላ ሰላማዊ ሰልፍን እቅድ ከሰማበት ጊዜ አንስቶና ከሰልፍ በኋላም እጅግ አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ይህም የሰላማዊ ትግሉን ሂደት ከምርጫ 2007 የቅድመ ዝግጅት የዕለት ተዕለት ሥራው አንዱ ዲሞከራሲን የማጥፋት ተግባር በመሆኑ ለጐፋ አካባቢ ከተማ ፍ/ቤት ጀምሮ እስከ ወረዳ ፍ/ቤቶች ከፓሊስ ኃይል ጋር በመተባበር እያጠቁ ናቸው፡፡ ተግባሩን በምንከታተልበት ጊዜም ሊያነጋግሩን ፈቃደኛ አይደሉም የዜግነት መብታችንም እየረገጡ ይገኛሉ፡፡

የደምባ ጎፋ ወረዳ ፍ/ቤት ተከሳሽ ኮልታ ቀበሌ የመኢአድ አመራሮች 1ኛ. አቶ ባሻ በላይነህ እና አቶ በቀለ ዋና በወረዳው የኢህአዴግ ካድሬዎች በአቶ ለሌ ለበኔ ተልካ ማሳቸውን ተነጥቀው እና የፓርቲ ኘሮግራም ከእጃቸው ተቀምተው በሐሰት ክስ ወንጀል ተከሰው የብዙ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት ለ3 ወር ያህል ወደ ወህኒ ተወርውረዋል፡፡ በጌዜ ጎፋ ወረዳ፡- 12 የመኢአድ አባላት የቀበሌ መዋቅር በኃይል ማፍረስ፣ በራሳቸው ጊዜ ስልጣን መያዝ፣ ልማትን ማደናቀፍ፣ ሕገ-መንግሥቱን በኃይል ለመናድና የመንግሥት ንብረት ማውደም በሚል መጋቢት ወር 2006 ዓ.ም በፋይል ቁጥር 03673 ተከሰዋል፡፡
ይህንም በይግባኝ በአዋሳ ጠቅ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳያቸው እየታየ እያለ በቀን 26/09/2006 ዓ.ም ከሳውላ ማረሚያ ፍ/ቤት በደረቅ ፖሊስ ጣቢያ መልሰው በማሰር በድጋሚ በሦስት የወንጀል ክሶች ማለትም 1ኛ. ዕውቅና ያልተሰጠ ስብሰባ በማድረጋቸው 2ኛ. 226 የመኢአድ አባላትን በማሰባሰብ የመኢአድን መታወቂያ የያዛችሁ በሙሉ የልማት ሥራ እንዳትሠሩ በማለት አስተባብሯል፣ የመንግሥትን ትዕዛዝ እንዳይፈጸሙ በማለት የውንብድና ወንጀል ፈጽመዋል የሚሉ ናቸው፡፡ 3ኛ. በቡልቂ ከተማ ውሰጥ በመሆን በስልጣን ያለውን የመንግሥት መዋቅር ሳያስፈቅድ የፓርቲ መዋቅር በመዘርጋት አመራር በመሾም 226 አባላት በማደራጀት በሕገ-ወጥ መንገድ መዋጮ አሰባስቧል ተብለው ታስሯል፡፡
የአይዳ ልዩ ወረዳ ፍ/ቤት እነ አቶ አልታዬ ኤሶ 7 የመኢአድ አመራሮችና አባላትን በመንግሥት ላይ የሐሰተኛ ሐሜት በማነሳሳት በማለት በወረዳ ፋ/ቁ. 07417 ተከሰው በጎፋ አካባቢ ፍ/ቤት ፋይል ቁ. 10492 በተሰጠው ውሳኔ 1ኛ. በፋ/ቁ. 06362 በ16/09/05 የመንግሥት ሥራ አስናከሉ ከማለቱ በፊት ለ3 ወራት አስሯቸዋል፡፡ 2ኛ. በፍይል ቁ.06656 በቀን 09/05/2006 የሙታን ክብር በመንካት በሚል 300 ብር ተቀጥተዋል፡፡ 3ኛ. በፋ/ቁ. 06298 በቀን 27/06/05 በብር 150.00 ቅጣት ተከሰው ተቀጥተዋል፡፡ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ 1 ዓመት በ8ኛ እና በ2ኛ ተከሳሽ ላይ 10 ወር በ3ኛ ተከሳሽ እና 5ኛ ተከሳሽ ላይ 9 ወር የተፈረደባቸው ሲሆን ይህ ድርጊት በቂም በቀልነት የተፈፀመ እየገለጽን፣ በመኢአድ ፓርቲ ተደራጅተው የመቃወም መብት አጥተው ሰላማዊ ትግሉን እንዲያቋርጡ የአፈና ተግባር እየተፈጸመባቸው ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)

0 comments:

Post a Comment