የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሌጋሲ እናስቀጥላለን ያሉ ሰዎች …. የሰውዬውን ሌጋሲ እየሸረሸሩት እንደሆነ ያወቁ አይመስለኝም፡፡ አውቀውት የራሳቸውን ሌጋሲ ለማኖር ከሆነም እሰዬው የሚያሰኝ ነው፡፡ ሰሞኑ ለጅቡቲ መንግሰት ውሃ አቅርቦት በሚመለከት አንድ አዋጅ ምክር ቤት መቅረቡን ተከትሎ ትንሽ ጫጫታ መነሳቱ የሚታወስ ነው፡፡ የዚህ ነገር አንጓ ያለው ደግሞ የመንግሰት ተጠሪ ሚኒሰትሯ ወ/ሮ ሮማን ገ/ስላሴ ጥቅሙ ፖለቲካ ነው ያሉት ላይ ነው፡፡ ከምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ምን ጥቅም ታገኛለች? በሚል ለቀረበ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ጥቅሙ ፖለቲካ ነው የሚል ነበር፡፡ ከዓለም የባህር በር/ወደብ ከሌላቸው ሀገሮች በህዝብ ብዛት አንደኛ የሆነችውን ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት የተደረገው ደባ እየዋለ እያደር ብዙ ዕዳ እንደሚያስከፍለን ምልክቱ እየታየ ነው፡፡
በእኔ እምነት ህወሃት/የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት ከሻቢያ ጋር በመተባበር በዕቅድ ይዞት ነበር ለሚባለው የትግራይ-ትግረ መንግሰት ምስረታ አንፃር ሲታይ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የባህር በር እንዳይኖረው ማድረግና በሚመሰርቱት የትግራይ-ትግረ መንግሰት ጥገኛ ማድረግ ተገቢ ሊመስል ይችላል፡፡ በ1980 መጀመሪያ ኢህአዴግ የሚባል ግንባር ሲመሰርቱ ግን የአማራው ክንፍ ኢህድን/ብአዴን በመጨረሻም ኦህዴድ እና ደኢህዴን የተቀላቀለው ግንባር ለዚህ እቅድ ገብሮ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ በዚህ ደረጃ ማን ያወያያቸዋል ካልተባለ በስተቀር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ቢሆን ከኢሳያስ ጋር ያጣላቸው የሚመስለኝ ብዙ ሰው እንደሚለው በኢትዮ-ኤርትራ ቅጥ ያጣ ግንኙነት የትግል ጓዶቻቸው ተበሳጭተው ባደረጉባቸው ግፊት ብቻ ሳይሆን የሚኒሊክ የሚሏት ኢትዮጵያ ቤተመንግሰት ውስጥ ቁጭ ብሎ ከአሰመራ ትዕዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጭምር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሁሉም መስፈርት ትልቅ ሀገር ነች፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህችን ትልቅ ሀገር ለመምራት እድል አግኝተው ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት እድል ያለመፍጠር፤ እድል ሲገኝም ለመጠቀም ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ነው፡፡ አሰበውት የነበረ ነገር ካለም ይዘውት ሄደዋል፡፡
አሁን ባለው አለማዊ ሁኔታ እንዲሁም አሁን በምድር ላይ ባለው ተጨባጭ እውነት ትግራይ- ትግረ ቅዥት ነው፡፡ ሊሳካ የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ለምን? እያልን ደጋግመን መጠየቁን እናቁምና በዚህ ሃሳብ መነሻ ግን ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሀገር በተለይ ትግራይን በቅርብ ርቀት የባህር በር እንዳይኖር ተግቶ መስረት ምን ዓይነት ልክፍት እንደሆነ የሚያሰረዳን እንፈልጋለን፡፡ ባህር እንዲኖረን ጥረት እናድርግ ሲባል ጦር ናፋቂዎች እንደሚሉን እምነቴ ነው፡፡ ይህ መልስ ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል፣ጥፋትን መሸፈኛ ነው፡፡ አሁን ያለው ጥፋት ጥፋትን በጥፋት ማረሙ ላይ፡፡
ይህ ግትር አቋም እንደ አፍ ወለምታ ብቻ ሳይሆን ቋሚ የገዢው ፓርቲ መርዕ አድርገው ወደብ ሸቀጥ ነው ያሉን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በህይወት እያሉ ነው ወደብ ሽቀጥ ብቻ እንዳልሆነ ምልክቱን ያዩት፡፡ በመስከረም 2004 ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ከጅቡቲ ጋር የነፃ (እንዲሁም ከፍለን) ውሃ ለማቅረብ የተስማሙት፡፡ ሁለት ዓመት አስቆጥሮ ደግሞ ይህ ሰምምነት ህግ ይሆን ዘንድ ለምክር ቤት ቀርቦዋል፡፡
ዛሬ ጅቡቲ በምትባል አንዲት ትንሽ ሀገር በፀባይ ለመያዝ ውሃ በነፃ ለዚያውም ከነሙሉ የደህንነት ጥበቃው ጋር መስጠት ጥቅሙ ወደብ ሽቀጥ ነው ብለው ያሰተማሩን ትምህርት ትክክል ያለመሆኑን ከማረጋገጥ በላይ ነው፡፡ ወደ ዘለገ ያለ የፖለቲካ ጥቅም አለው ለሀገር ደህንነትም ወሳኝ ነው፡፡ ዛሬ የዚህ የተሳሳተ ወደብ ሸቀጥ ነው ፍልስፍና ለወደብ ኪራይ ከምንከፍለው ገንዘብ በተጨማሪ በነፃ ውሃ ልናቀርብ መሆኑ ነው፡፡ በእኔ እምነት በቅርባችን ያለችው መሪዋ አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት ጅቡቲዎች ውሃ ቢያገኙ ደስ ይለኛል፡፡ የሃረሪ ክልል ከድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ውሃ እንደሚያገኘት ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ችሮታ ደግሞ ሁሌ ቤት ሞልቶ ሲተርፍ ከሆነ ስጦታው ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ ያለን በማካፈል ስሜት ሲሆን ደስ ይላል፡፡ እነካ በንካም ትክክል አይደለም፡፡
የሚቆጨው እና የሚያንገበግበው ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ አድርጋበት የገነባቸውን አሰብ የግመል ውሃ መጠጫ እንዲሆን ፈቅደውና ተስማምተው፤ እንደ ሸቀጥ እንገዛዋለን ብለው ያሰቡትን የጅቡቲ ወደብ ከፈተኛ ዋጋ እያሰከፈለ ቢሆንም አሁንም በዓይነት ደግሞ የምንከፍልበት ፖለቲካው ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡ ለጅቡቲ ከጫት እስከ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ከመብራት እሰከ መጠጥ ውሃ የማቅረብ ፍቅራችን ጥቅሙ ፖለቲካ መሆኑ መታመኑ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደብ ሸቀጥ ነው ብለውን ነበር እኮ፡፡ ለባቡር ግንባታ የሚያስፈልገውን ብድር ዋስትና የሰጠች ሀገር አሁን ደግሞ የመጠጥ ውሃ ቢያገኙ ምን ይላቸዋል በሚል የህግ ረቂቅ ቀርቧል፡፡ በነገራችን ላይ በመሃል ሀገር የጅቡቲ መንግሰት የእርሻ መሬት እንዳለው መዘንጋት የለብንም፡፡
ብዙ ሰው ያልተረዳው ነገር ኢትዮጵያ ነዳጅ ብታመርትና በጅቡቲ በኩል ለመላክ ከወሰነች ነዳጅ በነፃ የምንሰጥበት ግዴታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታሰብ ማነኛውም ወደ ወጭ የሚላክ ምርትን ዋጋው እጅግ በጣም ውድ ነው፡፡ ዋጋ ውድ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የሎጀስቲክ ስርዓቱ ነው እያሉ ሊያታልሉን ይሞክራሉ እንጂ ከሎጀስቲክ ስርዓቱ ውስጥ ዋነኛው የባህር በር የሌለን መሆኑ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር ዋጋ ትልቁ መስፈርት ነው፡፡ የባህር በር ናፍቆታችን መቼም ቢሆን በደረቅ ወደብ ምስረታ እንደማይሳካ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የግመል መጠጫ እንዲሆን የፈረድንበትን የአሰብ በር ኢትዮጵያዊያን በአማራጭነት የምንጠቀምበት ሁኔታ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ እሰከዚያ ድረስ ከጅቡቲ ጋር ያለንን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ከዚህም በላይ አጠናክረን መቀጠል ምርጫ አይደለም ግዴታ ነው፡፡
ወደብ ተራ ሽቀጥ አይደለም! ወደብ ለአንድ ሀገር ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው እድገት ወሳኝ የሆነ ግብዓት ነው፡፡ ለሀገር ደህንነትም ጭምር፡፡ ኤርትራዊያን ሞልቶ ከተረፈ የባህር በሮቻቸው አንዱን በተለይም በኢትዮጵያ ብብት ውስጥ የሚገኘውን የአሰብ ወደብ በነፃነት ሰሜት መጠቀም መቻል ይኖርብናል፡፡ ይህ ማለት በጅቡቲ ወደብ መጠቀም ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ መተንፈሻችን ይሰፋል ማለት ነው፡፡
የነፃነት ዋጋ ስንት ነው? በሚል መፅሃፌ ላይ “ጅቡቲ ያለ ኢትዮጵያ ሀገር ነች ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ …. ኢትዮጵያ አሁን እያቀረበችው ያለውን መሰረታዊ አቅርቦት በማሻሻል የጅቡቲ ዜጎች በኢትዮጵያ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን እና ድሬዳዋን እና አካባቢዋን ተመራጭ ሀገራቸው እንዲያደርጉት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም በጅቡቲ የኤኮኖሚ ትስስር ፈጣሪ እንዲሆኑ መንግሥት ቀጥተኛ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡” ብዬ ነበር፡፡ በማስከተልም “በእኔ ዕይታ ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ መስጠት ይኖርባታል፡፡ በተለይ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሱማሊያ የመሰሉት የሰሜንና ምስራቅ አጎራባች ሀገሮችን በጋራ በመሆን ልናሸንፋቸው የምንችላቸው ብዙ ጉዳዮች አሉን፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ለማጠናቀቅ ግን ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምነት ከታሪካዊ ጠላትነት ፍልስፍና ወጥታ ለታሪካዊ አጋርነት መመሥረት መሥራት ይኖርባታል፡፡ እነዚህ የሰሜንን እና ምስራቅ አጎራባች ሀገሮች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሥራት አንድ ሰጥተው ሁለት የሚያገኙበት መሆኑን ማስጨበጥ ሲሆን ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ እነርሱ ሁለት ያገኙት ከኛ ተቀንሶ ሳይሆን አብረን በመሆናችን ከተገኘ ትርፍ መሆኑን አብረን ካልሆንን እኛም አንድ እነርሱም ሁለት አያገኙም የሚለውን ማስጨበጥ ይኖርብናል፡፡” ብዬ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ሲመዘን የሰሞኑ ለጅቡቲ የተሰጠው ውሃ እጅግ ጠቃሚ ጅምር አድርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ትግሉን አሁን ባለ ነባራዊ ሁኔታ ትክክል የሆነን ውሳኔ በመቃወም ሳይሆን ዘላቂ ጥቅም ልናረጋግጥ የምንችልበትን ነፃ የባህር በር የማግኘት መብታችንን ማረጋገጡ ላይ ይመስለኛል፡፡
ልክ ነው ጅቡቲ ትንሽ ሀገር ነች፡፡ ለኢትዮጵያ ግን የመተንፈሻ በር ነች፡፡ ዋነኛ መተንፈሻችን ጅቡቲ እንድትሆን ያደረጉን ደግሞ በትግራይ ነፃ አውጪ ስም ተደራጅተው ኢትዮጵያ የሚመሩ ያሉት ቡድኖች ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በመቶ እጥፍ ከምንበልጣት ጅቡቲ ጋር በእኩል ደረጃ ልንደራደር አንችልም፡፡ በእኩል እንዳንደራደር ሀገራችንን ባህር በር አልባ ያደረጉን የትግራይ ነፃ አውጪዎች የሚያስከፍሉን ዕዳ ወደፊትም በዚህ የሚያበቃ አይመሰለኝም፡፡ በእኔ እምነት በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙት ሀገሮች ሁሉ ባለ ራዕይ መሪዎች በተመሳሳይ ወቅት መፈጠር ይህን ዕዳችንን ሊያሳጥረው ይችላል የሚል ቅን አመለካከት አለኝ፡፡
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ
0 comments:
Post a Comment