Tuesday 10 June 2014

ግትር አቋም ትቶ፤ እኔም የሀገር ጉዳይ ያገባኛል፣ መልመድ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ራስን ችሎ፤ በራስ ተማምኖ ለመኖር ራስን ሆኖ መፈጠርን ይጠይቃል፡፡

 Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)
በሀገራችን ከድህነት እኩል የሚፈታተነን ችግር፤ ቢያንስ ግማሽ መንገድ እንኳ ሄዶ ለመደራደር ዕውቀቱን፣ ጥበቡን አሊያም ቀና ልቡናውን ማጣታችን ነው፡፡ ግማሽ መንገድና የመቻቻል፣ ልዩነትን የማስተናገድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመልመድ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ አገር በኔ ብቻ ተመርታ አገር አትሆንም ብሎ፤ ኃይለኛውና አሸናፊው ከወጣበት መሠላል ዝቅ ብሎ፤ ግማሽ መንገድ ወርዶ እንነጋገር፣ እንወያይ የማለት ባህል፤ ተሸናፊውም ከቁጭቱ፣ ከቂሙ፣ ለመጣል እንጂ አብሮ ለመቀመጥ አልፈልግም የሚልበትን ግትር አቋም ትቶ፤ እኔም የሀገር ጉዳይ ያገባኛል፣ “እንድትሰፉ እንጂ እንደትጠፉ አልፈልግም” ብሎ፤ መንገድ መሻት ያሻዋል፡፡
የኋላ ታሪክ የሌለው የሚያውቀው ዛሬን ብቻ ነው፡፡ የአንድ ቀን ታሪክ የሌለው የሚያውቀው ዛሬን ብቻ ነው፡፡ አንድ ቀን ባዶነት መሰማቱ አይቀርም፡፡ ከሌላ አካል ተከፍሎ መፈጠር ዕድሜ ልክ ሙሉነት ሳይሰማን እንድንኖር ማድረጉ አሌ አይባልም፡፡ ራስን ችሎ፤ በራስ ተማምኖ ለመኖር ራስን ሆኖ መፈጠርን ይጠይቃል፡፡
በሀገራችን በፖለቲካ መከፋፈል እንጂ ተስማምቶ መጓዝ አይሆንልንም፡፡ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ እንደባህል የተያዘ ፈሊጥ ነው፡፡ አይጥና ድመት የታረቁ ለታ ባለንብረቱ ወዮለት! አይጥና ድመት እንኳ ታርቀው ጠላታቸውን የሚያጠቁበት ቀን ይመጣል ፡፡ “የማይለወጥ ነገር የለም – ከለውጥ ህግ በስተቀር” ታሪካችንን ወደኋላ ብንመረምር ምን ያህል እንደተለወጥን ወይም እንደተለዋወጥን መገንዘብ ቀላል ነው፡፡
ስለተሰሩ መንገዶች፣ ስለፈረሱ ቤቶችና ስለተሠሩ ህንፃዎች፣ ስለታሰሩ ሰዎችና ስለተፈቱ ሰዎች፤ ስለተፃፉ ደንቦችና ስለተጣሱ ህጐች፤ ስለማይሸጡ መሬቶችና በሊዝ ስለተወሰዱ መሬቶች፤ ስለማይነኩ ሰዎችና ኋላ ስለተወረወሩ ሰዎች፡፡ ለውጥ አይቀሬ ነው፡፡ ህገመንግስቱን እንኳን “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይደለም ሰው ነው የፈጠረው ሰው ይለውጠዋል፡፡” ብለው ነበር የቀድሞው መሪ፡፡ የብሔር ብሔረሰብ አካሄዳችንም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የሚሸጋገርበት ቀን ሊመጣ ይችላል፡፡
“ዕድሜ ሙሉ ከመሞት ለአንድ ደቂቃ ፈሪ መሆን ይሻላል” ማለታቸውን አንርሳ፡፡ “ዘለዓለም ውሻ ሆኖ ከመኖር አንድ ቀን አንበሳ ሆኖ መሞት” የሚለውን መዘንጋትም ተገቢ አይሆንም፡፡ ሁሉም ወቅት ወቅት አለውና! ሁኔታዎችን እንደየአመጣጣቸው መመዘን፣ እንደየልኬታቸው ዓይነተኛ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በደስታ ሰዓት ደስታችንን መግለጽ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የሚያዘናጉንን ሁኔታዎች፤ ይሆነኝ ብሎ ማሰብ ወሳኝ ነው! ይሄ በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በባህልም፣ በሥነ አዕምሮአዊ ሂደትም፤ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም፣ ፓርቲም፣ ግለሰብም ተሁኖ ቢታሰብ፤ ዋናው ነገር ይሄው ነው፡፡ “ከሳቅህ ዓለም አብሮህ ይስቃል፡፡ ካንኮራፋህ፤ ብቻህን ትተኛታለህ!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ እንዳንተኛ አናንኮራፋ!ቤት ንብረት በሀራጅ ከሚያስሸጥ ድህነት ይሰውረን፡፡ በሎተሪ ከሚያሳምን የገጠመኝ ዘመን ያውጣን፡ ከሁሉም በላይ ግን ለመለመን እንኳ ጥቂት የራስ መንቀሳቀስ እንደሚያሻን መገንዘቢያ የሚሆነን ልብ ይስጠን!!

0 comments:

Post a Comment