በዛሬው "የፍርድ ቤት" ውሎ ፓሊስ 28 ቀናት የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ጠይቆ 15 ቀናት ተፈቅዶለታል
ዛሬ በአራዳ አንደኛ ደረጃ "ፍርድ ቤት" አንደኛ ምድብ ወንጀል ችሎት ሶስቱ የዞን 9 ጦማሪ ጓደኞቻችን የቀረቡ ሲሆን ፓሊስ ለ28 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ "ፍርድ ቤቱ" 15 ቀናትን ሰጥቶታል፡፡ በእለቱ የነበሩት ዳኛ ይህ ጉዳይ በጣም ተራዝሟል በሚል 15 ቀን መፍቀዳቸው የተሰማ ሲሆን ችሎቱ የተሰየመው ለ10 ደቂቃ ላነሰ ጊዜ ነበር፡፡ ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ እስር ቤት ውስጥ እሱ ያላለውን ቃል በመጻፍ እንዲያምን በፓሊስ መገደዱንና የሱ ቃል እነዳልሆነ ለ"ፍርድ ቤቱ" የተናገረ ሲሆን ዳኛዋ ይህ ችሎት ያንን የማይመለከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"የፍርድ ቤቱ" ቅጥር ግቢ ውስት ከ300 በላይ የሚጠጉ የጦማርያኑ ጓደኞች እና ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን በተለይ ይህ ሁለተኛ ቡድን "ፍርድ ቤት" በሚቀርብበት ወቅት የሚታየው በፓሊሶችና ለታሳሪዎቹ አጋርነት ለማሳየት በመጡ ወዳጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ዛሬም ታይቷል፡፡
ፓሊስ ፎቶ ለማንሳት ሙከራ ያደረጉ ሁለት ወጣቶችን እና የነሱን መያዝ ላይ ጥያቄ የጠየቀ አንድ ወጣትን በጥቅሉ ሶስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ታውቋል፡፡(ሁለቱ ወጣቶች የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መሆናቸውም ተረጋግጧል) ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወዳጆቻቸውን ሲወጡ ለመመልከት በፍርድ ቤቱ ጊቢ ይጠበቁ የነበሩ ሰዎችን ፓሊስ ከግቢው አስገድዶ ለማስወጣት ባደረገው ጥረት ውጥረት ሰፍኖ የነበረ ሲሆን ለመጻፍ የሚከብዱ አጸያፌ ስድቦችን ፓሊሶች ሲሳደቡ እነደነበረ በቦታው የነበሩ ወዳጆች ሪፓርት አድርገዋል፡፡ በስተመጨረሻም ታሳሪዎቹ ቅጥር ጊቢውን ለቀው ሲወጡ ለማየት ያልተፈቀደ ሲሆን የ"ፍርድ ቤቱ" በር ተዘግቶባቸው መንገድ ላይ ሲጠብቁ የነበሩም ወዳጆቻቸው የማየት እድሉ ሳይገጥማቸው ተመልሰዋል፡፡ ፓሊስም አድማ በታኝ እንጠራለን የሚል ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ሲያሰማ ነበር፡፡
ከፍተኛ የፓሊስ ስርአት አልባነት የተንጸባረቀበት ይህ ሂደት የፍትህ ስርአቱ መገለጫ ሲሆን የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ጓደኞቻችን በምንም አይነት ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው አንዳልነበረና ክሱም ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው የተመሰረተ ፓለቲካዊ ክስ መሆኑን ለማስታወስ አንወዳለን፡፡
ፍርድ ቤት ለተገኛችሁ ሂደቱን በተለያዩ መንገዶች ሪፓርት ስታደርጉ ለነበራችሁ እና አጋርነታችሁን ላሳያችሁ ዞን 9 ነዋሪያን በታሰሩ ወዳጆቻችን ስም ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
0 comments:
Post a Comment