አርብ ሰኔ 20/2006
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው!
ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን!
እንኳን ለ 1435 ዓ.ሂ ታላቁ የረመዳን ፆም አደረሰን!
ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን!
እንኳን ለ 1435 ዓ.ሂ ታላቁ የረመዳን ፆም አደረሰን!
የዘንድሮ ረመዳን በመብት ትግላችን ውስጥ ሆነን ያገኘነው ሶስተኛው ረመዳን ነው፡፡ መብታችንን ለማስከበር በጀመርነው ሰላማዊ ትግል ውስጥ ያሳለፍናቸው ረመዳኖች አንድነታችንን ለመበታተን ያሰፈሰፉ ሃይሎች የበረቱበት እና ህዝባችንን በፍርሃት ለማሸማቀቅ ቀን ከሌት የተደከመባቸው ነበሩ፡፡ አካላዊ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ በህዝባችን ላይ የስነ ልቦና ሽንፈት ለመፍጠር ቀን ከሌት የተሰራባቸው ጊዜያትም ነበሩ፡፡ መጪው ረመዳን እነዚያን ትላልቅ ፈተናዎች ተሻግረን ዛሬም በአንድነታችን እና በትግላችን ላይ ፀንተን የምንገኝበት ወቅት መሆኑ ወሩን በልዩ ትኩረት እንድንቀበለው የሚያበረታታን ነው፡፡
በዘንድሮው ረመዳን በተዘነበለ ፍትህ ምክንያት በርካቶች የቀደሙ ረመዳኖችን አብረው ከፆሟቸው የቤተሰብ አባላት ጋር አይፆሙም፡፡ የዜግነት መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በሞት፣ በስደት እና በእስር የተለያዩ ቤተሰቦች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ዛሬ ገሃድ ሆኖ ያየነው መጪው ጊዜ ለዲን የሚከፈል መስዋእትነትን የመቀበል አቅማችን የደነደነ እና ለድልም የበለጠ የቀረብን መሆናችንን አመለካች መሆኑን ነው፡፡
ይህንን ለማለት ያስቻሉን በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እዚህ ሳንጠቅሰው የማናልፈው አንዱ ምክንያታችን ግን ለታሪክ ግብኣት ይሆን ዘንድ በምንታደመው የፍርድ ቤት ሂደት ላይ በምስክርነት የሚቀርቡ ወንድም እና እህቶቻችን ላይ ያስተዋልነው አስደናቂ በራስ የመተማመን መንፈስ ነው፡፡ ለትግሉ ያላቸው የቁርጠኝነት መንፈስ በእርግጥም የሚደንቅ ነው፡፡ ምስክሮች እየሰጡ ያለው ምስክርነት ለእኛ የፍርድ ሂደት ካለው ታሪካዊ ፋይዳም ባለፈ ተወክለንበት ስንንቀሳቀስበት የነበረው ሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ምን ያክል ህዝባዊ መሰረት እንደያዘ የሚያረጋግጥ ክስተት ነው፡፡ ህዝባችን ዛሬም መስዋእትነት በከፈለለት ትግል ፅኑ እምነት እንዳለውም ያሳያል፡፡ ይህንን ከታሰርን በኋላ በነበሩት ወቅቶች በአካል ለመታዘብ የቻልንባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ በመላው ሃገሪቱ፣ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ከእኛ መታሰር በኋላ እየተካሄዱ ያሉ ግዙፍ ተቃውሞዎችም በምስክሮቻችን እና ለጉብኝት በሚመላለሱ ወገኖቻችን ላይ እንዳየነው ሁሉ ለትግሉ ካላቸው እውነተኛ ተቆርቋሪነት የሚመነጭ መሆኑን ማወቅ ለእኛ ከምንም በላይ ትልቅ እርካታ የሚሰጥ ክስተት ነው፡፡
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች!
ኢስላማዊ ስነምግባሮች ይበልጥ ጎልተው ለሚወጡበት እና የለውጥ ዋነኛ ጊዜ ለሆነው ለተከበረው ወረሃ ረመዳን በድጋሚ እንኳን አደረሰን፡፡ ረመዳን ለቤተሰብ እና ማህበረሰብ ለውጥ ዋነኛ መነሻ ወቅት ነው፡፡ በኢስላም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ክስተቶች በዚሁ ወርሃ ረመዳን ተከስተዋል፡፡ ለእኛም ትግላችንን አስፍተን ለመቀጠል ከረመዳን የተሻለ አጋጣሚ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ያነሳናቸው ሶስት ቀላል ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ አልተመለሱም፡፡ መንግስት የሚሊዮኖችን ድምፅ በማፈን የወሰዳቸው ህገ ወጥ እርምጃዎች በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ ባለቤትነቱ የሰላም ወዳዱ ሰፊ ህዝበ ሙስሊም የሆነው መንፈሳዊ ድርጅታችን ቅቡልነት ባጣ ቀበሌኛ የሹመት ሥነ-ሥርዓት አማካኝነት በመጡ ህገ-ወጥ ሹማምንት እጅ ወድቋል፡፡ ይህም በመሆኑ መንግስት ከድርጊቱ እንዲታቀብ፣ እርምጃውንም በድጋሚ እንዲያጤነው ህዝበ ሙስሊሙ ያደረጋቸው ያላሰለሱ ጥረቶች ሰሚ ጆሮ በማጣታቸው ሳቢያ የሹመት ሥርዓቱንም ሆነ ህገ ወጥ ሹማምንቱን ቅቡልነት ነፍጓል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸው ህጋዊ የመብት ጥያቄዎች አለመመለሳቸው ሳያንስ የመሰረታዊ መብቶቻችን ንጥቂያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀጥሎ መገኘቱ ጉዳዩ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትኩረት በሚያሻው ወቅት ላይ መድረሳችንን ያመላክታል፡፡ ይህ የመብት ጥሰት እየጨመረ መቀጠሉም ህዝበ ሙስሊሙን ተግባራዊ የሆኑ ጫናዎችና እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያስገድድ እንደመሆኑ መጠን በአገሪቱ ከሚካሄዱ ሁለንተናዊ ማህበረ ፖሊቲካዊ ሂደቶች ጋር ትግላችንን በመቃኘት ለተሻለ ውጤት መታገል የግድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ ረመዳንም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ፈተናው በውጤት የሚለወጥበት ጊዜ እንዲሆን እንመኛለን፤ እንደሚለወጥም በአላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ላይ ያለን እምነት ፅኑ ነው!
በመጨረሻም በረመዳን ቤተሰባዊ አንድነታችንን በማጠናከር የተለመደ ኢስላማዊ እና ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህላችንን በመጠቀምና ይበልጥም በማጠንከር ከመካከላችን ለችግር የተጋለጡ፣ በተለይም መብት በመጠየቃቸው ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመንከባከብ ላይ አደራ እንላለን::
አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በረመዳን ከሚጠቀሙት ያድርገን!
========================================
========================================
ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
0 comments:
Post a Comment