አበሻና ቀጥታ መስመር አይተዋወቁም፤ ቀጥታ መስመር መጀመሪያ አለው፣ መጨረሻም አለው፤ አበሻ እንዲህ ተጀምሮ የሚያልቅ ነገር አይወድም፤ እልቅ ሲል ጭር ይልበታል፤ አበሻ የባህርዩ የሆነውና የሚስማማው ክብ መስመር ነው፣ ክብ መስመር መጀመሪያ የለው፣ ማለቂያ የለው፣ ሲዞሩ መዋል ነው፤ አበሻ ነገሩ ሁሉ ክብ ነው፤ ቤቱ ክብ ነው፣ እንጀራው ክብ ነው፣ ዳቦው ክብ ነው፣ ድስቱ ክብ ነው፣ ጋኑም ክብ ነው፤ ክብ ያልሆነ
ነገር አበሻ ምን አለው?
አበሻ ነገሩ ሁሉ ክብ ነው፣ አዙሪት ነው፣ ታሪኩም አዙሪት ነው፣ ሄደ የተባለው ሁሉ ተመልሶ ይመጣል። አበሻ ማለት አዙሪት ነው፣ አዙሪት ማለትም አበሻ ነው። የእንግሊዝ ወይም የሩስያ ወታደሮችን ሰልፍ ስታዩ ቀጥታ መስመር ምን እንደሆነ ተገነዘባላችሁ። የአበሻ ወታደሮችስ? ተለያይቶ የተገጣጠመ ክብ መስመር?
አበሻ በመስመር መሄድም ሆነ መቆም አይሆንለትም። አበሻ ቀጥታ መሰመር ሲያጋጥመው የሚታየው ተለምጦ ነው፣ ክብ ሆኖ ነው፣ መጀመሪያ የሌለው፤ መጨረሻም የሌለው በፈለገበት በኩል ሊገባበትና በፈለገበት በኩል ሊወጣበት የሚያስችለው ክብ ሲሆን ነው፤ ሰዎች ተራ ይዘው በመስመር እንዲጠብቁ በሚደረግበት ግዜ አበሻ ጭንቀቱ ነው፤ እንዴት ብሎ ጀርባውን ለማያውቀው ሰጥቶ ከፊቱ ደግሞ አንድ የማያውቀው ሰው ተደንቅሮ በሰላም መቆም ይችላል? አንዱ ደፋር ከኋላው መጥቶ ቀድሞት ቢሄድ ግድ የለውም፤ ለነገሩ ራሱም ቢሆን ፈርቶ ነው እንጂ ያደርገው ነበር! የድሮዎቹን ሰዎች ጭንቀታቸውን ለመቀነስ አንተ ቅደም አንተ ቅደም እየተባባሉ የተራውን ቀጥታ መስመር ይቆለምሙት ነበር፤ የዛሬው የሰለጠነው ትውልድ አንተ ቅደም ብሎ ነገር አያውቅም፣ ሁሉም በየፊናው ለመቅደም ሲሞክር መተራመስ ነው፤ መተራመስ ቀጥታ መስመርን ድራሹን ማጥፋት ነው።
አበሻ ለቀጥታ መስመር ያለውን ኃይለኛ ጥላቻ ለመረዳት አምስት ደቂቃ ያህል በአዲስ አበባ መንገዶች ዳር በተለይ መስቀልያ በሆኑት ላይ ቆም ብሎ ማየት ነው። የትራፊክ ፅሕፈት ቤት በፈረንጅ አገር ሲደረግ አይቶ በየመንገዶቹ ላይ ሁሉ ነጭ መስመር ይለቀልቃል፣ ልፋ ያለው በህልሙ ዳውላ ይሸከማል እንደሚባለው ሆኖ ነው እንጂ መኪና የሚነዳው አበሻ መቼ ስራ አጥቶ ነው ያንን ቀጥታ መስመር የሚያየው? እያንዳንዱ ነጂ በፊናው በራሱ በውስጡ ያለውን ክቡን እየተከተለ በኩራት የትርምስ ትርኢት ያሳያል፤ ተመልካቾቹ የትራፊክ ፖሊሶች ናቸው። የትራፊክ ፖሊሶቹ አራትም አምስትም እየሆኑ የትርምሱን ቲያትር በመደነቅ ይመለከታሉ፣ በመንገዶቹ ላይ ቀጥታ መስመሮች የተሰመሩት ለመኪናዎቹ እንደአጥር ሆነው ቀጥታ እንዲሄዱ ለማድረግ ነበር፣ አበሻ ምኑ ቂል ነው? መኪናውን በመስመሩ ላይ አንፈራጥጦ እየነዳ ይሸፍነውና መስመሩን ከነኖራው ጋር ከህልውና ውጭ ያደርገዋል። መስመሩ ሲጠፋ ለትርምሱ ይበጃል፤ ለሁለት መኪናዎች የተቀየሰውን መንገድ አንዱ ብቻውን ይዞት ወሬውን እያወራ ይንፈላሰሳል።
ትርምስ ፈጣሪዎች ባለመኪናዎች ብቻ አይደሉም፣ እግረኞችም ናቸው፣ ለእግረኞቹ ማቋረጫ ተብሎ የተሰራ መንገድ አለ፣ እግረኞች ሁሉ በዚያ ለእግረኞች በተሰመረው መንገድ ገብተው ለማቋረጥ ይፈራሉ፤ መፍራታቸው አያስደንቅም። መስመሮቹ ለእግረኞቹም ሆነ ለመኪና ነጂዎቹ አይታዩም፤ የሚያስደንቀው ግን እግረኞቹ በባቡር መንገዱ መሃል ገብተው በሙሉl ልብ ሲያተራምሱ ነው! የሚተራመሱት የትራፊክ ፖሊሶችም ቢሆኑ መስመሮቹን አያዩም፤ እግረኞቹንም አያዩም፤ መኪናዎቹን አያዩም፣ ለወጉ ለብሰው የሚተራመሰውን እያዩ እነሱም ይተራመሳሉ!
አበሻ በሩጫ በዓለም የታወቀ ሆኖአል፤ ግን በመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር ስስጥ አበሻ የለበትም፣ የመቶ ሜትር ውድድር ውስጥ ትርምስ የለም፣ መስመር ይዞ መሮጥ ያስፈልጋል፣ ታዲያ አበሻ በሩጫ የተደነቀ ጎበዝ ቢሆንም በመስመር ውስጥ ገብተህ ሩጥ ሲሉት ግራ ይገባዋል፤ አበሻ ንጉስ እንደኀይሌ ንግሥት እንደ ጥሩነሽ የሚሆነው በርቀት ሩጫ ትርምስ ውስጥ ብቻ ነው፤ በመኪናም የርቀት ውድድር ቢኖር አበሻን ማን ይቀድመው ነበር! ለሽቅድድም የወጣውን መኪና ሁሉ በትርምስ እያጣበቀ ቀጥ ያደርገው ነበር፤ ለመሆኑ ባቡሩ ተሰርቶ ሲያልቅ አበሻ ምን ይበጀዋል? ችግር ነው ጌትነት!
የአበሻ የመስመርና የወረፋ ጥላቻ ከምን የመነጨ ይመስላችኋል ከጌታና ሎሌ ስርዓት አይመስላችሁም? ከጨዋነት ነው የሚሉም አይጠፉም ይሆናል፣ በመተሳሰብ አንተ ቅደም አንተ ቅደም እየተባባለ ግዜን ሲያቃጥል ኖረና አሁን ደግሞ በትርምስ ጊዜን ያቆመዋል!
ደጉ ዘመን አንተ ቅደም የሚባልበት ዛሬ ከቻለ ገፍትሮ መቅደም፣ጨዋው ሲገፈትሩት አንገቱን ደፍቶ ዝም ማለት፣ በደርግ ዘመን ቤንዚን በሰልፍ በሚቀዳበት ግዜ መኪናዬ ውስጥ ሆኜ ተራዬን እጠብቃለሁ። አንዱ ጮሌ መስመሩን ስቶ መጣና ከእኔ መኪና ፊት ለመግባት ቆልመም አድርጎ አቆመ፤ መኪናዬን አስነሳሁና ገጨሁበት። ከመኪናው ወርዶ የተገጨውን ሲመለከት « እኔ ወፍ የምጠብቅ ይመስልሃል?» አልሁት፤ እሱም አግድም እያየኝ «እኔ ምን አውቃለሁ» ሲል መለሰልኝ።
0 comments:
Post a Comment