ቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና የ2006 ዓ.ም. የቦርዱን ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ ለምክር ቤቱ አባላት ለጥያቄ በተሰጠ ዕድል ነው አቶ ግርማ ምሬታቸውን ያሰሙት፡፡ ‹‹በምክር ቤቱ ፊት የምናገረው›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ግርማ፣ ፓርቲያቸው አንድነት ጋዜጣ በማተም አቋሙን ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ አንደኛ ተግባሩ ቢሆንም፣ ማተሚያ ቤቶች ለማተም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹ማተሚያ ቤቶች አናትምም የሚሉት የጋዜጣ ማሳተሚያ ፈቃድ አምጡ በሚል ምክንያት ነው፡፡ እኛ ለንግድ አይደለም ጋዜጣ የምናትመው፤›› ያሉት አቶ ግርማ፣ ‹‹በፓርቲ ሰርተፊኬት ማሳተም ባለመቻሉ ቦርዱ ሕጋዊ መሆናችንን ደብዳቤ እንዲጽፍልን ብንጠይቅም እሺ አላላችሁንም፤›› ሲሉ ለፕሮፌሰር መርጋ ነግረዋቸዋል፡፡
ይህ በመሆኑ አንድነት ፓርቲ የማተሚያ ማሽን መግዛቱን ነገር ግን ፓርቲው የተከራየው ቤት ባለንብረት ለማተሚያ ማሽኑ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መሸከም የሚችል መስመር ለማስገባት ‹‹የምታትሙት ሕጋዊ መሆኑን ካላረጋገጥኩኝ አላስገባም፤›› እንዳሉና በዚህም ምክንያት ፓርቲው ሕጋዊ መሆኑን የሚያስረዳ ደብዳቤ ቦርዱ እንዲጽፍ ቢጠየቅ እንቢ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
‹‹ለፓርቲያችን ቢሮ ያከራየንን ሰውዬ እናመሰግነዋለን፡፡ ምክንያቱም ቢሮ መከራየት መከራ በመሆኑ፡፡ አንድ ደብዳቤ ለመጻፍ ፈቃደኛ ባለመሆናችሁ ግን ጋዜጣ ማተም አልቻልንም፤›› ሲሉ የቦርድ ሰብሳቢውን ምክር ቤቱ ፊት ወቅሰዋል፡፡
የፓርቲዎች አንዱ ተግባር ኅብረተሰቡን በተለያየ መንገድ መድረስ መሆኑን ያስረዱት አቶ ግርማ፣ ሕዝቡን ለማግኘት ፓርቲያቸው ቤት ለቤት መቀስቀስ ወይም በራሪ ወረቀቶችን እንደሚበትን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
በሚበተነው ወረቀት ላይ የሰፈረ መልዕክት ሕጋዊ ካልሆነ ፓርቲው መጠየቅ እንደሚችል አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ለመበተን በወጣን ቁጥር ሰላሳና መቶ ሰዎችን አሳስረን ነው የምንገባው፡፡ እባካችሁ አንድ ነገር አድርጉልን ብንላችሁ ይኼው እስካሁን የመጣ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ስብሰባ ለማድረግ አዳራሽ አከራዮች ፈቃድ አምጡ ይሉናል፡፡ ስብሰባ ለማካሄድ ፈቃድ መጠየቅ የማይገባ ቢሆንም ፈቃድ የግድ ስለሆነብን ፈቃድ የሚሰጠውን ስንጠይቅ በመጀመርያ አዳራሽ መከራየታችሁን ደረሰኝ አምጡ ይሉናል፤›› ብለው፣ ‹‹እኛ ከዚህ አንፃር እንዴት አድርገን ነው ወደ ሕዝብ መድረስ የምንችለው ወዴት ሄደንስ ነው አቤት የምንለው?›› በማለት ፕሮፌሰር መርጋን ጠይቀዋቸዋል፡፡
አቶ ግርማ በማከልም ለዚህች አገር የግጭት ፖለቲካ አይጠቅምም በማለት፣ ከቦርዱ ሰበሳቢ ጋር በግልጽ መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች በጠበበ ምኅዳር ነው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ የሚካሄደው ያሉት አቶ ግርማ፣ ‹‹ክቡር ሰብሳቢ የ2007 ዓ.ም. ምርጫን በእኩል ሜዳ ነው የምናጫውተው ብለው እንደ ዳኛ ሊፈርዱን ይችላሉ፤›› በማለት ጠይቀዋቸዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ ለዚህ መሥሪያ ቤት ደብዳቤ ጻፉልን የሚል ደብዳቤ እንደሚመጣ፣ ነገር ግን ቦርዱ አንዴ ሕጋዊ ዕውቅና ከሰጠ በኋላ ሕጋዊ ነው የሚል ደብዳቤ መጻፍ አስፈላጊነቱ እንዳልታያቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቦርዱ መብት የለውም፡፡ ሊቀጣ አይችልም፡፡ ሕጋዊ ፓርቲ በመሆናችሁ ወደ ሕግ መሄድ ትችላላችሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እኛ ፓርቲውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል ብለን ነው የምናስበው፡፡ አቶ ግርማ እዚህ ምክር ቤት ተወዳድረው የገቡት በፓርቲ ተወዳድረው አሸንፈው ነው፡፡ እናንተ ራሳችሁን ከምታስተዋውቁት በተጨማሪ ስለፓርቲዎች እኛም እናስተምራለን፤›› ያሉት ፕሮፌሰር መርጋ፣ ቦርዱ ማድረግ የሚገባው ላይ ወደኋላ እንደማይል ነገር ግን ከድንበሩ መወጣት አይችልም ብለዋል፡፡
ከተጠቀሱት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመነሳት ስለ 2007 ዓ.ም. ምርጫ የሜዳ እኩልነት አቶ ግርማ ላነሱት ጥያቄም፣ ‹‹ቦርዱ ሜዳ ማመቻቸት ነው ሥራው፡፡ ለፓርቲ አናደላም፡፡ ብይን የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ምርጫው በእኩል እንዲካሄድ ግን መቶ በመቶ በሙሉ እምነት መናገር ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
0 comments:
Post a Comment