Thursday, 3 July 2014

የመኢአድ/አንድነት የውህደት አመቻች ኮሚቴ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

udJ&AEUP

የኢትዮጵያን ህዝብ የለውጥ ፍላጎት እውን ለማድረግ የመኢአድ እና የአንድነት መዋሀድ ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው!!!

የኢትዮጵያን ህዝብ የለውጥ ፋላጎት ዕውን ለማድረግ የተቃዋሚው ጎራ በመሰባሰብ አንድ ግዙፍ አማራጭ ኃይል ወደ መገንባት ሊሸጋገር እንደሚገባ መላው የአገራችን ህዝብ ለረጅም ግዜ ሲያሳስብ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡
በዚሁ መሰረትም ትግሉ የሚጠይቀውን የፖለቲካ ተክለ ቁመና ለመያዝ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የደረሱበትን ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ እውን ለማድረግ ከሁለቱም ፓርቲዎች በእኩል ቁጥር የተቀወከሉ አሥር አባላት ያሉት የውህደት አመቻች ኮሚቴ ተቋቁሞ የውህዱን ጉባኤ በስኬት ለማጠናቀቅ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የውህደት አመቻች ኮሚቴው ሁለቱ ታርቲዎች በተናጠል የሚያካሂዱት እና በጋራ ውህዱ ፓርቲ የሚያደርገው ጉባኤ በተያዘለት ግዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱ ፓርቲዎች መዋሃድ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረበት ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች አካላት በውህደቱ ሂደት ላይ ተግዳሮት ለመደቀን በርካታ ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አስተውለናል፡፡
ስለሆነም መላው የሀገራችን ህዝብ ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተልና ገዥው ፓርቲ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከግሉ ሚድያ ጋር ተመሳስለው አፍራሽ ተልእኮ እንዲፈጽሙ ባደራጃቸው አካላት እና ሚዲያዎች ሁለቱ ፓርቲዎች የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት በማጠልሸቱ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ እየተደረገ ያለውን ስውር ሴራ በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
የሁለቱ ፓርቲዎች መዋቅርም ሆነ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የውህደት አመቻች ኮሚቴው መረጃዎችን በጥንቃቄ እንደሚከታተል እና ይፋ እንደሚደረግ እየገለፅን በአጭር ጊዜ ውስጥ ውህደቱን በማጠናቀቅ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እንደምንሸጋገር ለመላው ህዝባችን እንገልጻለን፡፡ ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ለውህደቱ መሳካት አስፈላጊውን የፋይናንስ፣ የማቴሪያል፣ የሞራልና የሀሳብ ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነታችንን በጋራ እንድንወጣ ጥሪ እንቀርባለን፡፡
በ1997 ዓ.ም የታየውን የህዝብ የለውጥ ፋላጎት እና የፖለቲካ ተሳትፎ ዳግም ለመመለስ ሳንታክት እንሰራለን!!!
ከውህደት አመቻች ኮሚቴ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ
Source: Zehabesha

0 comments:

Post a Comment