Thursday, 17 July 2014

መጠርጠሪያዎቻችን፤ ግንቦት ሰባት እና ኦነግ ምን እና ምን ናቸው…

BrXBZTmIIAAIEPYAbetoikichaw
መጠርጠሪያዎቻችን፤ ግንቦት ሰባት እና ኦነግ ምን እና ምን ናቸው…
ግንቦት ሰባት እና ኦነግ ለብዙዎች መጠርጠሪያ እና እስር ቤት መወርውሪያ ምክንያት ሆነው ማየት ከጀመርን ሰነባበትን።
ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ ከወለጋ ከአዳማ ከአምቦ ከባሌ ወይም ከሌላ ቦታ… ግብር በዛብን ብለው ሲያጉረመርሙም ይሁን ”ጉርምርሜ ና ጉሩምርሜ” ብለው ጮክ ብለው ሲያዜሙ የተገኙ ሁላ ከኦነግ ጋር ተባብራችሁ ሀገ መንገስታዊውን ስራዓት ሀገ ወጥ በሆነ መልኩ ልታፈርሱ ነበር። እየተባሉ የት የት እንደገቡ እርሱ ዋርዲያው ይወቀው።
አዲሱ ፋሽን ደግሞ ግንቦት ሰባት ከሆነ ጥቂት የማይባሉ ግንቦት ሰባቶች አለፉ።
ዛሬ የሰማነው ዜና እንደሚያሰረዳው “እኔም ያገባኛል” የሚለውን ሃይለቃል አንግበው ዞን ዘጠኝ በሚል ስያሜ ራሳቸውን በራሳቸው አደራጅተው፤ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሲጽፉ የነበሩ ጦማሪያን ኦነግ እና ግንቦት ሰባት ጋር ተገናኝተው ሀገመንግስታዊውን ስርዓት አልበኝነት በሀገወጥ መልኩ ሊንዱ ከኦነግ እና ግንቦት ሰባት ጋር ሲንቀሳቀሱ ደርሰንባቸዋል ብሎ አቃቤ ህግ ክስ መመስረቱን በይፋ ነግሮናል።
በቀጣይም ይህንኑ የሚያሳይ በርካታ የኢቲቪ ድራማዎች እንደምናይ ተስፋችን የበዛ ነው።
በዋናነትም ያለተያዘችው ሶሊያና (እንኳንም አልተያዘች) አስተባባሪ ሆና ”ሴኩሪቲ ኢን ኤ ቦክስ” የተባለ ስልጠና እንዲወስዱ ስትመራ ቆይታለች፤ ተብላለች። (የሆነ የጦር ስልጠና አይመስልም… ሆሆ የኢንተርኔት ደህነነት ስልጠና እኮ ነው። እንኳን እንዲወስዱ አደረገቻቸዋ… ታድያ ምን ይጠበስ እስቲ በሞቴ አሁን ይሄ ያስከስሣል…  ይሄንን ስልጠና እኮ መስጠት የነበረበት መንግስት ራሱ ነበር…) በነገራችን ላይ ወዳጃችን ዘርሽ የዚህን ስልጠና አማርኛ ቅጂ ፌስ ቡክ ገጹ ላይ አድርጎት አግኝቼዋለሁ በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ሰው አንብቦት ራሱን ከኢንሳ አደጋ ሊጠብቀበት ይገባል እና ዘርሽን እያመሰገንን እዝች  ጋ ጠቅ በማድረግ ራሳችንን እናሰልጥን።
ሌሎቹ ፍቄ እና ናቲ ናቸው… በፍቃዱ ሃይሉን የሀገር ውስጥ የሽብር ቡድንን ይመራ ነበር ብለውታል…. (እንደው ትንሽ እንኳ የማይሰቀጥጣቸው ከሳሾች እነ ኢህአዴግን አየሁ) ናትናኤል ፈለቀ ደግሞ ካለተያዙ ግብረአብሮቹ ጋር በመሆን ለሽበር ተግባር የተላከላቸውን አርባ ስምንት ሺህ ብር አከፋፍሏል ብለውታል… (ይሄንን የሰማ አንድ ወዳጄ እንግዴ አንድ ቀን ሉካንዳ ቤት ሲገባ አይተውት ይሆናል ብሎኛል…) ናቲ ማለት ከጆን ኬሪ ጋር የኢትዮጵያ ወጣቶችን ወክሎ አምና ውይይት አድርጎ ዘንድሮ የታሰረ ነው። ጆን ኬሪ ይሄንን ሲሰሙ ”የኢትዮጵያ ወጣቶች ጉዳይ ስሄድ አገኝኋት ስመልስ አጣኋት” ነው ብለዋል ተብሎም ሲነገር ነበር…
የሆነው ሆኖ፤ መጠርጠሪያዎቻችን እነ ግንቦት ሰባት እነ ኦነግ እንዲሁም እነ አርበኛ ግንባር እነ ደህሚት የመሳሰሉት ሲጠረጠሩ ብቻ ነው አንድ ላይ የሚጠረጠሩት ወይስ ሲታገሉም አንድ ላይ ይታገላሉ የሚለው በጣም መሰረታዊ ጥያቄ ነው።
ሳስበው ሳስበው ኢህአዴግ አንድ ላይ የምትጠራቸው ቢጨንቃት ቢሆንም እግረ መንገዷንም ግን እያሰታወሰች ነው እና እነ ኦነግ እነ ግንቦት ሰባት፣ እነ አረበኛ፣ እነ ደህሚት እስቲ ”በኢህአዴግ ጥያቄ መሰረት ግንባር ፈጠረናል!” በሉና አስደስቷት። እኛም መጠርጠሪያዎቻችን ምን እና ምን ናቸው… ብለን በግምት ከምንሞት በይፋ ተዛመዱ እና ”የጆሮ ጉትቻ የአንገት ሀብል ናቸው…” እንበልላችሁ።
ማስታወቂያ በፌስ ቡክ በኩል ለምታነቡን ወዳጆች የ Security in-a-box አማርኛ ቅጂ በአስተያየት ቦታ ላይ አስቀምጠዋልሁ ጎራ ብላችሁ እዩት። አዲሳቦች ሳይዘጋ ቶሎ ቶሎ አንብቡት!

0 comments:

Post a Comment