Wednesday 16 July 2014

በጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ላይ የተከፈተው የጊዜ ቀጠሮ ፋይል ተዘጋ

“ዐቃቤ ሕግ ክሱን በ15 ቀናት ውስጥ ክስ መመሰረት ይጠበቅበታል”
ጠበቃ አመሃ መኮንን
ፖሊስ በሽብር ወንጀል ጠርጥሮ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ፤ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች መረጃዎችን ሲለዋወጡና በውጪ ሀገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስልጠና ወስደው፤ ህዝባዊ አመጽ ለመቀስቀስ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተው፤ በሕጋዊ መንገድ ስልጣን የጨበጠውን መንግስት በሕገ-ወጥ መንገድ ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ በሚል ከሁለት ወራት በላይ አስሮ በማዕከላዊ ምርመራ ላይ የቆዩት ዘጠኙ ጋዜጠኞችና የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን በፖሊስ ተከፍቶባቸው የነበረው የጊዜ ቀጠሮ ፋይል ተዘግቶ፤ ወደ ዐቃቤ ሕግ መመራቱን በድንገት ስለመስማታቸው የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አመሃ መኮንን አስታወቁ።
ባሳለፍነው ቅዳሜ እና ሰኞ (ሐምሌ 5 እና 7 ቀን 2006 ዓ.ም) በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት፤ በሁለቱ ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ የነበራቸው ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ባልቀረቡበት፤ የአያያዝ ሁኔታቸውን በግልፅ ለችሎቱ ባላስረዱበትና የዋስትና መብታቸውን ጠይቀው ምላሽ ባልተሰጠበት አኳሃን ጠበቃቸው ሲቀርቡ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ፋይሉን ስለመዝጋቱና በቀጣይ ጉዳዩ ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ደርሶ ክስ ሊመሠረትባቸው መሆኑን ከችሎት መስማታቸውን የሚናገሩት ጠበቃ አመሃ መኮንን፤ በፍርድ ቤቱ ፋይሉ የተዘጋበትን ሁኔታ በተመለከተ “የተለመደ አሠራር ነው” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ። ጠበቃው ሒደቱን ስርዓቱን ያልተከተለና የደንበኞቻችንንም ሕጋዊ መብት የጣሰ ነው ሲሉ ይናገራሉ። በተለይም በሰኞው ዕለት (ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም) ቀጠሮ በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ቀደም በማለት ተገኝተው እንደነበር ያስታወሱት ጠበቃው፤ ሦስቱም ተከሳሾች ማለትም በዕለቱ የተቀጠሩት ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉና አቤል ዋበላ ባልቀረቡበት፤ እንዲሁም አንድም የመርማሪ ቡድኑ አባል ባልተገኘበት ከመዝገቡ ጋር ተያያዞ በቀረበ ወረቀት አማካኝነት ብቻ መዝገቡ መዘጋቱንና ወደመደበኛ ክስ ለመግባት ዐቃቤ ሕግ ክስ እስኪመሰረት እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
መርማሪ ቡድኑ መዝገቡን አጠናቅሮ ከቀረበለት የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ በቀጣዮቹ አስራ አምስት ቀናት ውስጥ ክሱን መስርቶ በፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚኖርበት የአሠራር ሂደት መኖሩን የጠቆሙት ጠበቃ አመሃ መኮንን፤ ደንበኞቻቸው መቼና የት እንደሚቀርቡ አሁን ድረስ አለማወቃቸውን አስረድተዋል። ደንበኞቼን በሙሉ ማግኘት አልቻልኩም። ለዚህም እስረኞቹን ለመጐብኘት ከዕረቡና ከአርብ ቀን ውጪ ክልክል መሆኑና በአንድ ቀን አንድ ሰው አንድ ደንበኛን ብቻ የማግኘት ገደብ መኖሩን እንደመሰናክል በመጥቀስ አሠራሩ ችግር እንዳለበትም አክለው ገልፀዋል።
     “ደንበኞቼ አሁን ያሉበት ሁኔታ ሕገ-ወጥ ነው” የሚሉት ጠበቃው፤ ለዚህም የጊዜ ቀጠሮውን ሲሰማ የነበረው ፍርድ ቤት ታስረው ይቆዩ የሚል ትዕዛዝን ባልሰጠበት፤ አልያም ክስ ተመስርቶባቸው ክሱን የሚሰማው ፍርድ ቤት በእስር ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተሉ ባላለበት ሁኔታ ውስጥ ከቅዳሜው 4 ሰዓት እና ከሰኞው 8 ስዓት ጀምሮ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ታስረው የሚቆዩበት ሁኔታ ሕጋዊ መሠረት የለውም” ሲሉ አስረድተዋል። ከዚህ ቀጣይ እርምጃቸው የሚሆነው አካልን ነፃ የማውጣት ክስ በመመስረት ደንበኞቻችን ነፃ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።
Source-sendek

0 comments:

Post a Comment