አዲስ ጉዳይ መጽሄት ዛሬ እንዳሳወቀው ከሆነ; ላለፉት 3 አመታት የመጽሄቱ ፎቶግራፍ አንሺ የሆነችው አዚዛ መሃመድ አርብ እለት በስራዋ ላይ እያለች በፖሊስ ተይዛ በ እስር ላይ መሆኗን የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ዝግጅት ክፍል እንዲህ በማለት በዝርዝር ሁኔታውን ገልጿል:: ላለፉት ሶስት ዓመታት በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ በፎቶ ጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ያለችው ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ አርብ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም አንዋር መስጂድ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት በተመለከተ ፎቶ ዘገባ ለመስራት ወደስፍራው በተንቀሳቀሰችበት ወቅት በጸጥታ ሃይሎች ተይዛ ታስራለች።
የአዲስ ጉዳይ ባልደረቦች የአዚዛ ስልክ ዝግ መሆኑን ተከትለው በጸጥታ ሃይሎች ተይዛ ታስራ ሊሆን እንደሚችል ባደረባቸው ጥርጣሬ በተለያዩ የፖሊስ ጣቢያዎች ፍለጋ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ቀድሞ 3ኛ ተብሎ በሚጠራውና ወደሰሜን ሆቴል በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ላይ እንደምትገኝ ማረጋገጥ ችለዋል።
ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ አርብ እለት እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት ድረስ በመስጊድ አካባቢ በሥራ ላይ እንደነበረችና ከዚህ ሰዓት በኋላ ግን ስልኳ ዝግ እንደሆነ ነው አዲስ ጉዳይ የተገነዘበው።የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ባልደረቦች የአዚዛ መሐመድ በእስር ላይ መሆን በእለቱ ሊፈልጓት ለሄዱት የመጽሄቱ አባላት አረጋግጠዋል።ቅዳሜ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርባ እንደነበር ቢናገሩም ፎቶ ጋዜጠኛዋ የተያዘችበትን ምክንያት ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የአዚዛ መሃመድ መርማሪ ፖሊስ ለአዲስ ጉዳይ ባልደረቦች “ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ክፍለከተማ ምድብ ችሎት መቅረቧንና ፖሊስ በጠየቀው የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ምክንያትም ለሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም መቀጠሯን” ተናግረዋል።አዲስ ጉዳይ በስም ወደተጠቀሰው ፍርድ ቤት በመሄድ ጉዳዩን ሲያጣራም መርማሪው የተናገሩት ትክክል መሆኑንና አዚዛ ከሌሎች ብዛት ካላቸው ግለሰቦች ጋር ለተባለው ቀን በቀጠሮ እንድትቀርብ ችሎቱ መወሰኑን መገንዘብ ችሏል።እንደፖሊስ ሁሉ የፍርድ ቤቱ ሰራተኞችም አዚዛ የተጠረጠረችበትን ወንጀል ለመግለጽ ፍቃደኛ አልነበረም።
አዲስ ጉዳይ መጽሄት አዚዛ መሃመድ በዕለቱ ሙያዋ ከሆነው የፎቶ ጋዜጠኝነት ሥራዋ ውጪ በየትኛውም የወንጀል ተግባር ላይ ተሳታፊ ሆናለች የሚል እምነት የለውም።አዚዛ መሃመድ ከባህሪዋ እና ለሙያዋ ካላት ፍቅር አኳያ በምትሰራበት አዲስ ጉዳይ መጽሄት የምትታወቀው ዘወትር የታዘበቻቸውንና ለዜና ይሆናሉ ብላ የምታስባቸውን ማናቸውንም ክስተቶች በፎቶግራፍ በማስቀረት የጋዜጠኝነት ተግባሯን ህጋዊነትን በተከተለ መንገድ ብቻ በማከናወኗ ነው።
በአብዛኛው ጥበባዊ በሆኑ ዝግጅቶች ላይ የፎቶ ጋዜጠኝነት ስራዋን የምታከናውነው አዚዛ የፎቶ ጋዜጠኝነት ሙያዋ የሚጠይቀውን የረጅም ጊዜ ትምህርት ከመውሰዷ ባሻገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነጥበብ ትምህርት ቤትም የስዕል ትምህርት ተከታትላለች።
በባህሪዋ እውነተኛ እና ስነምግባር ያላት ባለሙያ መሆኗን ዝግጅት ክፍሉም ይሁን በስራ አጋጣሚ አዚዛን የሚያውቋት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባልደረቦችም ምስክርነታቸውን የሚሰጡላት ፎቶ ጋዜጠኛ ናት።
የአዲስ ጉዳይ መጽሄት በፎቶ ጋዜጠኛ ባልደረባው ላይ ምርመራ በማካሄድ ላይ እንደሆነ የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ክፍል አዚዛ በፖሊስ የተያዘችበትን ምክንያት በተመለከተ ዝግጅት ክፍሉ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪም በሃገሪቱ ህገመንግስት መሰረት የተያዙ ሰዎች የሚኖራቸውን መብት በማክበር ከስራ ባልደረቦቿ እና ከቤተሰቦቿ ጋር እንድትገናኝ እንዲያደርግ እንዲሁም የሚደርስባትን መጉላላት ለማስቀረት በተቻለ ፍጥነት የተያዘችበትን ምክንያት በማጣራት ከወንጀል ነጻ መሆኗን አረጋግጦ በነጻ ትለቀቅ ዘንድ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥያቄ ያቀርባል።
የአዲስ ጉዳይ መጽሄት በፎቶ ጋዜጠኛ ባልደረባው ላይ ምርመራ በማካሄድ ላይ እንደሆነ የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ክፍል አዚዛ በፖሊስ የተያዘችበትን ምክንያት በተመለከተ ዝግጅት ክፍሉ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪም በሃገሪቱ ህገመንግስት መሰረት የተያዙ ሰዎች የሚኖራቸውን መብት በማክበር ከስራ ባልደረቦቿ እና ከቤተሰቦቿ ጋር እንድትገናኝ እንዲያደርግ እንዲሁም የሚደርስባትን መጉላላት ለማስቀረት በተቻለ ፍጥነት የተያዘችበትን ምክንያት በማጣራት ከወንጀል ነጻ መሆኗን አረጋግጦ በነጻ ትለቀቅ ዘንድ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥያቄ ያቀርባል።
0 comments:
Post a Comment