በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት ጦማሪያን፣ ሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት)፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፉ
ብርሃኔ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ እንዲሁም ጋዜጠኞቹ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬና ተስፋለም ወልደየስ ላይ ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የሽብርተኝነት ወንጀል በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተሳታፊ በመሆን ለአመፅ ተግባር በህቡዕ መደራጀታቸውን፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው የክስ ቻርጅ ይገልጻል፡፡
እንደ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተጠርጣሪዎቹ በህቡዕ በመደራጀት፣ የአጭርና የቅርብ ጊዜ ግብ በማቀድና በመንደፍ ከግንቦት 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙት የግንቦት 7 እና የኦነግ ድርጅቶች መመርያና ሐሳብ ሲቀበሉ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ አንዷ የሆነችው ሶሊያና ሽመልስ የቡድኑ መሥራችና አስተባባሪ በመሆን ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. መቆየቷና ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በውጭ አገር አስተባባሪና የውጭ ግንኙነት ሆና ከመሥራቷም በተጨማሪ፣ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በማደራጀትና በመመልመል ስትሠራ መቆየቷን ክሱ ያስረዳል፡፡
የህቡዕ ቡድኑ ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ‹‹ሴኩሪቲ ኢን ቦክስ›› የተባለ ሥልጠና እንዲሠለጥንና እንዲደራጅ ስትመራ መቆየቷም በክሱ ተካቷል፡፡
ሌላኛው ተጠርጣሪ በፍቃዱ ኃይሉ የአገር ውስጥ የሽብር ቡድንን በመምራትና የሥራ ክፍፍል በማድረግ፣ እንዲሁም ግብ በማስቀመጥና ስትራቴጂ በመንደፍ ከሽብርተኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ሲፈጥር መቆየቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡
የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ከሆነ ተጠርጣሪ ናትናኤል ፈለቀ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን የህቡዕ ድርጅቱ የአገር ውስጥ አስተባባሪ በመሆን በሥሩ ላሉት አባላት የሥራ ክፍፍል መመርያ በመስጠት፣ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት በመፍጠር መመርያ ከመቀበሉ በተጨማሪ፣ ለአመፅ ተግባር የሚውል የተላከለትን 48,000 ብር ማከፋፈሉንም ክሱ ያብራራል፡፡
ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች በህቡዕ ድርጅቱ ውስጥ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ መሥራችና አባል በመሆን የግንቦት 7 እና የኦነግን ስትራቴጂና ዕቅድ በመቀበል በውጭና በአገር ውስጥ ባሉ የቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በውጭና በአገር ውስጥ ሥልጠና በመውሰድ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሰርና በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ሁለተኛ ክስ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎቹ በወንጀሉና በሚያስገኘው ውጤት ተስማምተው በሕገ መንግሥት ሥርዓት የተቋቋመን መንግሥት በአመፅ፣ በሁከትና በብጥብጥ ለመለወጥ በማሰብ ከግንቦት 2004 ዓ.ም. እስከተያዙበት ዕለት ድረስ በህቡዕ ተደራጅተው፣ የሥራ ክፍፍል በመፍጠር፣ ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ አመፅ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን በመበተን፣ የአመፅ ቡድኖችን በማደራጀት ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመፅና በሁከት ለመለወጥ በመሞከር ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
0 comments:
Post a Comment