Sunday 12 January 2014

አቶ ያረጋል አይሸሹምና ሌሎች ተከሳሾች ጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተፈረደባቸው


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹምና አብረዋቸው ተከሰው የነበሩ አምስት ተከሳሾች፣ ከስድስት እስከ 15 ዓመታት የሚደርስ ጽኑ እስራትና ከ20 ሺሕ ብር እስከ 60 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ጥር 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ተፈረደባቸው፡፡
በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በሥልጣን ያላግባብ የመገልገል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሥርቶባቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ፣ ኅዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ጥፋተኛ መባላቸው ይታወሳል፡፡ 
በመሆኑም የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃና ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ በመስማት፣ አዲስ ከተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመርያ ቁጥር 2/2006 እና ከሌሎች የሕግ ድንጋጌዎችን አንፃር ፍርድ ቤቱ በመመርመር፣ አቶ ያረጋል አይሸሹም ሰባት ዓመት ጽኑ እስራትና 20 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ አቶ ያረጋል ጥፋተኛ የተባሉት በአንድ ክስ ሲሆን፣ ከሌሎቹ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን በዋና ወንጀል አድራጊነት ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል መሥራታቸው በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን  በመዘርዘር ነው፡፡ አቶ ያረጋል ክሱ በተመሠረተባቸው ወቅት የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ 
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩትና የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ወቅት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ነበሩ የተባሉት አቶ ሀብታሙ ሂካ፣ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ መባላቸውንና ካቀረቡት የቅጣት ማቅለያዎች አራቱ ተይዘውላቸው፣ 15 ዓመታት ጽኑ እስራትና 45 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ጥፋተኛ የተባሉትም በሦስት ተደራራቢ የሆኑ ሥልጣንን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል መፈጸማቸው፣ በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እንደተረጋገጠባቸው ፍርድ ቤቱ በውሳኔው በዝርዝር አስረድቷል፡፡ 
አቶ አሰፋ ገበየሁ የተባሉት ግለሰብ ደግሞ 15 ዓመታት ጽኑ እስራትና 60 ሺሕ ብር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ሲሆን፣ ለቅጣቱ መነሻ የሆነው የወንጀል ድርጊት ከሌሎቹ ተከሳሾች ጋር ግብረ አበር በመሆን በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆናቸው በሦስት ተደራራቢ ሥልጣን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል መፈጸማቸው፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ሊያስረዳ በመቻሉ መሆኑን የቅጣት ውሳኔው ያብራራል፡፡
አቶ አሰፋ የኮንስትራክሽንና ዲዛይን አክሲዮን ማኅበር የዲዛይን ስቱዲዮ ክፍል ኃላፊና የጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት ወኪል ሆነው በሚሠሩበት ወቅት፣ የወንጀል ድርጊቱን ሊፈጽሙ መቻላቸውን ውሳኔው ይጠቁማል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ጌዲዮን ደመቀ የተባሉት ተከሳሽ 14 ዓመታት ጽኑ እስራትና 60 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ መባላቸውንም በዝርዝር አስረድቷል፡፡ የጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅም ናቸው፡፡ የጋድ ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ አድገህና የኮለን ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መክብብ ሞገስ ደግሞ በአንድ ክስ ጥፋተኛ የተባሉ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ አስታውሶ፣ በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆንና በዋና ወንጀል አድራጊነት ሥልጣንን ያላግባብ የመገልገል ሙስና ወንጀል መፈጸማቸው፣ በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ እያንዳንዳቸው ስድስት ዓመት ጽኑ እስራትና 25 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በአቶ ገዛኸኝ አድገህ ላይ የተወሰነው ቅጣት በልዩነት በአብላጫ ድምፅ፣ ማለትም አንድ ዳኛ የጥፋተኛነት ፍርድ በሚሰጥበት ወቅት ‹‹በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል›› በማለት ሲለዩ፣ ሁለት ዳኞች ‹‹ጥፋተኛ ናቸው›› በማለታቸው የቅጣት ውሳኔው መሰጠቱን መዝገቡ ያብራራል፡፡ 
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ አቶ ያረጋል አይሸሹምን ጨምሮ በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የመሠረተ ቢሆንም፣ በሰባተኛነት ተካተው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የአቶ ሀብታሙ ሂካ ወንድም አቶ ኃይለ ገብርኤል ሂካ በብይን በነፃ ተሰናብተዋል፡፡
ፍርደኞቹን ለቅጣት ያበቃቸው የወንጀል ድርጊት ተፈጸመ የተባለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሠሩ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት በጀት ተይዞላቸው እንደነበር ከተገለጹት የግልገል በለስ መምህራን ኮሌጅ፣ የጣና በለስ ሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤትና የአሶሳ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም ጋር በተገናኘ ተፈጽሟል በተባለ የሙስና ወንጀል መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
ፍርደኞቹ ክልሉ በመስከረም ወር 1992 ዓ.ም. ያወጣውን የግዥ መመርያ ቁጥር 1/92 አንቀጽ 9.1 እና 2 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ እንዲሁም ከ300 ሺሕ ብር በላይ የሚፈጸም የአገር ውስጥ ግዥ በክልሉ የፋይናንስ ቢሮ መፅደቅ እንደሚኖርበት በመመርያው አንቀጽ 22.3.ሐ እና 231 1ኛ ሰንጠረዥና 23.2 ሥር የተደነገገውን ግልጽ መርህ መተላለፋቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ 
ለፕሮጀክቶቹ የተመደበው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን አቶ ያረጋልና አቶ ሀብታሙ እያወቁ፣ በግልጽ ጨረታ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን በመጋበዝ ማጫረትና ማሠራት ሲገባቸው፣ የሦስቱንም ፕሮጀክቶች ጨረታ በሕገወጥ መንገድ ለጌዲዮን አማካሪ ድርጅት መስጠታቸውን፣ የግዥ ዘዴ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ‹‹ሥራው አስቸኳይ ነው›› በማለት በውስን ጨረታ እንዲፈቀድ ማድረጋቸውን፣ ከመመርያ ውጪ የጨረታ ሰነድ ለኮንስትራክሽንና ዲዛይን አክሲዮን ማኅበርና ለጋድ ኮንስትራክሽን ድርጅት እንዲላክ ማድረጋቸውን፣ ሥራው በማጓተቱ 2,832,450 ብር ተጨማሪ ክፍያ መውጣቱንና ሁሉም ተከሳሾች በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸውና በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በሥልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

0 comments:

Post a Comment