“ከዚህ በኋላ የዚህ ችሎት አባል አይደለሁም በቃሪዛ ያመጡኝ እንደሆነ እናያለን፣ይህ ችሎት ፍርድ የሚሰጥ እንጅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሴሚናር አይደለም” አቶ በቀለ ገርባ
“ከዚህ በኋላ የዚህ ችሎት አባል አይደለሁም በቃሪዛ ያመጡኝ እንደሆነ እናያለን፣ይህ ችሎት ፍርድ የሚሰጥ እንጅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሴሚናር አይደለም” አቶ በቀለ ገርባ
“ሀጎስና ተክላይ /የአንድ ቤተሰብ አባሎች/ የኦሮሞን ህዝብ እያሰቃዩት ነው፣ይህ ድርጊት አብሮ አያኖረንም” አቶ ደጀኔ ጣፋ
እነ አቶ በቀለ ገርባ ለብይን ተቀጠሩ!!!
(በሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ)
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮችን ማለትም አቶ በቀለ ገርባ፣አቶ ደጀኔ ጣፋ፣አቶ አዲሱ ቡላላና አቶ ጉርሜሳ አያኖን ጨምሮ በ22 ተከሳሾች ላይ የፌደራል ዐ.ህግ ለመሰረተው የሽብር ክስ በማስረጃነት ያቀረበውን የሲዲ ማስረጃ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በፍርድ ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ እንዲያመጣ ትዕዛዝ ቢሰጥም ትርጉሙን ባለማቅረቡ ያላቀረበበትን ምክንያት ሃላፊው ቀርበው እንዲያስረዱና ተርጓሚ ባለሙያ ይዘው ለዛሬ ሚያዚያ 05 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲቀርቡ በድጋሜ ትዕዘዝ መስጠቱ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን ዛሬም የሚመለከተው የኢቢሲ ሃላፊም ሆነ ተርጓሚ ባለሙያ አልቀረበም፡፡ በምትኩ የቀረቡት ጉዳዩን ለማስረዳት እደተላኩ የገለፁ ፀጋልዑል የተባሉ ግለሰብና ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ናቸው ፡፡አቶ ፀጋልዑል ኢቢሲ የባለሙያ እጥረት እንዳለበትና በስራ መደራረብ ምክንያት ተርጉመው መቅረብ እንዳልቻሉ በመግለፅ ሌላ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ይህንን የኢቢሲ ምላሽ ተከትሎ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የተከሳሾች ጠበቆች የዛሬው ትዕዛዝ ለመጨረሻ በሚል እንደተሰጠና የደንበኛቻቸውን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን የሚያሳጣ በመሆኑ ማስረጃው ታልፎ በቀረበው ማስረጃ መሰረት ውሳኔ ይሰጥልን ብለዋል፡፡
አቶ በቀለ ገርባ ይህ ስርዓት በዜጎች ሲቃይ የሚደሰት ስርዓት ነው እኛም የምንታገለው ለዚህ ነው፣የዘገየ ፍትህ እንደተከለከለ ይቆጠራል፣በትርጉም ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ የሚሰጥ ከሆነ ከዚህ በሁዋላ የዚህ ችሎት አባል አይደለሁም፣ በቃሬዛ ያመጡኝ እንደሆን እናያለን፣ከዚህ በፊትም በፍርድ ቤቱ እምነት እንደሌለኝ ተናግሬ አልመጣም ብየ ነበር በዚህም ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅፎብኛል፣ይህ ፍርድ የሚሰጥበት እንጅ አንዱ ተቋም ሌላኛውን የሚያስተምርበት ሲሚናር አይደለም አሁኑኑ ውሳኔ ይሰጠን በማለት ተናግረዋል፡፡
አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ቀድሞውንም በችሎቱ እምነት የለኝም፣አንድ ዱርዬ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤቴ ገብቶ ነው የያዘኝ፣ይህንን ሁሉ የተማረ የኦሮሞ ወጣት አስረው የአንድ ቤተሰብ አባላት/ሀጎስና ተክላይ/ ይጫወቱበታል፣ ይኸ አብሮ አያኖረንም፣እናንተ ዳኞች ከጀርባችሁ ችግር እንዳለባችሁ ይገባናል የኢትዮጵያ ህዝብ ባይኖር እኛንም ይጨርሱን ነበር፣ ትክክለኛውን ፍትህ ሰጥታችሁ ለሚደርስባችሁ ጉዳት የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችሁ ይቆማል በማለት ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ኢቢሲ የሲዲ ማስረጃውን ተርጉሞ ከሚያዚያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም በፊት ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ የተከሳሽ ጠበቆችም ጉዳዩን ተከታትለው በቀረበው ትርጉም ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ችሎቱን የሰብዓዊ መብት ጉባዬ/ሰመጉ/ ተወካዮች፣ጋዜጠኞች፣የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች፣የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ፣ አቶ አለሙ ጌዴቦ/የርዕዮት አለሙ አባት/ እና የተከሳሾች ቤተሰቦች ተከታትለዋል፡፡
0 comments:
Post a Comment