የመን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለወያኔ ፋሽስቶች አሳልፋ መስጠቷን በማስመልከት የወጣ መግለጫ
ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ.ም
የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቶ መቆየቱ ማስታወቃችን ይታወሳል።
የየመን መንግሥት በህገወጥ መንገድ ያገተብንን የንቅናቄዓችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የአገሩን የረዥም ጊዜ ጥቅም ማየት የተሳነው የየመን መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይልቅ አምባገኑን ወያኔ መርጦ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል። በዚህም ሳቢያ የየመን መንግሥት ይቅርታ የማያሰጥ፤ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወዳጅ ጎረቤት ትሁትና ቀና ቢሆንም ጥቃት በሚያደርስበት የቅርብም ሆነ የሩቅ ጎረቤት ላይ ግን ቁጣውን የሚመጥን የአፀፋ እርምጃ መውሰድ ያውቅበታል።
የወያኔ ፋሽስቶች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማሰቃየት ትግላችንን ማቀዝቀዝ እንደማይችሉ ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። እንዲያውም በግልባጩ ቁጣና እልሃችን በእጥፍ ድርብ በመጨመር ትግላችንን ያጦዘዋል። ወያኔ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በውንብድና ጠልፎ መውሰዱ የትግሉን ሜዳ አስፍቶታል፤ የትግሉንም ዓይነት አብዝቶታል። ይህ ደግሞ የወያኔ ፋሽስቶችን ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፍላቸዋል።
የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህገ ወጥ እገታ ከተሰማ ዕለት ጀምሮ የፓለቲካ ልዩነት አጥር ሆኖ ሳይከልላችሁ ከጎናችን ለቆማችሁ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ዜጎች ሁሉ ምሥጋናችንን እናቀርባለን። በወገናዊ ተግባራችሁ ልባችን ተነክቷል። ከዚህ በላይ ደግሞ ለቀጣዩ ወሳኝ ፍልሚያም እንደምንቆም እና የወያኔን እድሜ እንደምናሳጥር እምነታችን አጠንክሮልናል።
ከዛሬ ጀምሮ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳርጋቸው ጽጌን ሆኗል። ዛሬ ዘጠና ሚሊዮን አንዳርጋቸው ጽጌዎች በአንድነት ተነስተዋል። በአንድ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የደረሰው ጥቃት ሰበብ ሆኖ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ የወያኔ ፋሽስቶችን ይጠራርጋል። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው ጥቃት እያንዳንዱ የወያኔ ሹም በግል ዋጋ ይከፍላል። ከእንግዲህ በምሬት የተነሳሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚወስደው እርምጃ ተጠያቂው ራሱ ወያኔ መሆኑን እውን ሆኗል። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እስር የክተት አዋጅ ታውጇል። ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለሀገር፣ ለእኩልነት ግድ ያለህ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተነስ!!!
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
0 comments:
Post a Comment