Tuesday, 27 May 2014

የቅድመ ምርጫ አፈናው በውይይት እንዲተካ እንጠይቃለን!! – ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
                                         UDJ-SEAL
እንደሚታወቀው የግንቦት 2ዐን 23ኛ ዓመት ለማክበር ጉድ ጉድ እያለ የሚገኘው ገዥ ፓርቲ ወደ ጠቅላይ አምባገነን ፓርቲነት ከተለወጠ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም ሀገሪቱን ከመቆጣጠራቸው በፊት በርካቶች ስለ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ሰብአዊ መብት መከበርና ዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን ክቡር ህይወታቸውን እንዲገብሩ ተደርጎ በተገኘ የዜጎቻችን መስዋእትነት መንበረ ሥልጣኑን ቢጨብጡም በተግባር ዋጋ የተከፈለበትን ዓላማ ለማሳካት አልቻሉም፡፡
እንዲሁም የህዝቦችን ነፃነት በጉልበት በመቀማት፣ ሰብአዊ መብትን በመጋፋት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማስመሰያነት በንድፈ ሃሳብ አስፍረው በተግባር በዜጎችዋ ግፍ በመፈፀም ነፃነውን ፕሬስ እንደጠላት በማየት፣ ተቀናቃኝ ኃይሎችንና የፖለቲካ መሪዎችን በማሰርና በማፈን፤ በነፃነት የመደራጀት መብትን በመጨፍለቅ በአጠቃላይ ፍፁም አምባገነን የሆነ ስርዓት በመዘርጋት ላይ ነው፡፡
ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመሻሻልና የሁነቶች የመማሪያ ባህሪ ሊኖረው አልቻለም፡፡ ይልቁንም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ውጭ የሆኑትን በጅምላ በመፈረጅና በተናጠል ግለሰቦችን ከፖለቲካው አውድ በማስወገድየእድሜ ልክ ገዢ የመሆን ሕልም ውስጥ ወድቋል፡፡
ፓርቲያችን አንድነትም ለሀገራችን የሚጠቅመው ይህ ያለመቻቻልና የጥፋት ጎዳና ሳይሆን የመነጋገር፤ እንዲሁም አሸናፊ የሆነው ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያኝና የዜጎች መብት ለስልጣን ሲባል ሳይሸራረፍ እንዲከበር በሠላማዊ ትግል አቅጣጫ መግፋት ተገቢ መሆኑን በጽናት ያምናል፡፡ የአመራር አባሎቻችንም ሳይገድሉ እየሞቱ፤ ሳይደበድቡ እየተደበደቡ፤ ሳያስሩ እያታሰሩ ለህዝቡ የሚገባው ነገር እንዲደረግ ያለመታከት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አንድነት ህጋዊ መስመር በመከተልና በጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥም ቢሆን ዓላማውንና ግቡን ፍፁም ሠላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ለህዝቡ ማድረስ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንዳለም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በህዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነትም እጅግ ጨምሯል፡፡ ነገር ግን ተቀባይነታችን በጨመረ ቁጥር በስጋት ባህር የሚዋኘው ገዢ ፓርቲ በአመራሮቻችንና አባሎቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው ግልጽ በደልና በማናለብኝነት በጠራራ ፀሐይ ለመደብደብ የሞራል ችግር በሌለባቸው የደህንነት ሠራተኞችና ሆድ አደር ግለሰቦችን በማሰማራት እየተፈፀመ ያለው ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር የሆኑት የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ስዩም በጠራራ ፀሀይ ታፍነው እንቅስቃሴያቸውን የማያቆሙ ከሆነ እንደሚገደሉ የተነገራቸው ሲሆን፤ የአዲስ አበባ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በጠራራ ፀሐይ ወደቤታቸው ሲገቡ ከኋላቸው በድንጋይ ተመትተው ሲወድቁ ሞቱ ብለው ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡ እንዲሁም የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የመሀል ቀጠና አደራጅ አቶ ደረጀ ጣሰውን የማይታወቁ ግለሰቦች እንፈልግሀለን በማለት በመኪና አፍነው ለመውሰድ ትግል ሲያደርጉ ባሰሙት ጩኸት ህዝቡ ያስጣላቸው ቢሆንም አይናቸውን በቦክስ በመመታታቸው በከፍተኛ ህክምና ሊተርፉ ችለዋል፡፡ አንድነት ላይ እየተፈፀመ ያለው የአደባባይ አፈና በዚህ የሚያበቃ አይደለም፡፡ በቅርቡ አንድነትን የተቀላቀሉት አቶ አስራት አብረሃምም በኦሮሚያ ፖሊሲ ታፍነው እስካሁን ያሉበት አይታወቅም፡፡ ይህ በአዲስ አበባ አመራሮች የተፈፀመ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ አባሎቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን አፈናና እስራት ለመዘርዘር ከባድ ነው፡፡ ለአብነትም በወላይታ ሰዶ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በሆኑት የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊው አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም የዞኑ የምክር ቤት አባላት፣ በደሴ ከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ በአቶ አዕምሮ አወቀ ላይ የተፈፀመው ውንብድና፣ ድብደባ እስራትና አፈና ጠቋሚ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
በአመራሮችና አባላት ላይ ከሚፈፀመው አፈናና ክትትል በተጨማሪ የፓርቲውን ስም ለማጥፋትና ተቀባይነት ለማሳጣት አይጋ-ፎረምን የመሳሰሉ የሥርዓቱ ቀላጤ ሚዲያዎች ፀረ-ሠላም ከሚሏቸው ኃይሎችና አሸባሪ ብለው ከፈረጁአቸው አካላት ጋር ግንኙነት እንዳለን የሚያስመስል የልቦለድ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ፓርቲያችን ጠንክሮ መውጣቱን ሲሆን ከዚህ በኋላ በአፈና፣ በድብደባና በእስር እንዲሁም በፍረጃ አንድነትን ወደ ኋላ መመለስ እንደማይችል ለማረጋገጥም እንወዳለን፡፡
ይልቁንም ገዢው ፓርቲ ካለፈው ስህተቱ በመማር፣ ከስለላ፣ ከፍረጃና ከአፈና በመላቀቅ ወደ ውይይት እንዲምጣ አሁንም ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአፈናና በጉልበት አሁንም ቀጣዩን ምርጫ ለመቀልበስ መሯሯጥ ባለዕዳ የሚያደርገው ገዢውን አካል መሆኑን ለማስገንዘብም እንወዳለን፡፡
የ23ት አመቱ የግንቦት 2ዐ ፍሬ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ቢኖር ይህ አስከፊ ስርዓት ያነበረው ጭቆናና በደል እስር እንግልትና በተጽእኖ ከሀገር መሰደድ ከሦስት ሺ ዓመታት በላይ የተገነባው አብሮነት አደጋ ላይ መውደቁ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ የነፃነት ቀን ነው በሚሉት በግንቦት 2ዐ ዋዜማ እንኳ የዞን 9 ጦማሪዎች በማእከላዊ መከራ እየተቀበሉ ሲሆን የእስር እርምጃው ቀጥሎ ደራሲ አስራት አብርሃም ታፍኖ ከመሰወሩ ባሻገር የዕንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በተጨማሪ ወደ እስር ተግዟል፡፡ ይህም የግንቦት 2ዐ ፍሬ መሆኑ ነው፡፡
ምን አልባትም ሥርዓቱ የምርጫ 97 ሽንፈትን ተከትሎ በግብታዊነት ወደ መሰረተ ልማት ማስፋፋት በማተኮር አንዳንድ ቁሳዊ ልማት ለማሳየት ቢጣደፍም ማህበራዊ ልማትን ቀብሮ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን እረግጦ፤ ልማት አስመዝግቤአለሁ እያሉ አገዛዝን በኃይል ለማስቀጠል መሞከር የከፋ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ፓርቲያችን ዛሬም የዚችን ሀገር ዘርፈ ብዙ ችግር በኃይል ለማዳፈን ከመሞከር ወደ ውይይት እና ብሔራዊ መግባባት ማዘንበል ጠቃሚ መሆኑን አበክሮ ይገልፃል፡፡
ድል የሕዝብ ነው!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ግንቦት 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ

0 comments:

Post a Comment