“በኦሮሚያ ለተቃውሞ የወጡ ሠላማዊ ሰዎች ሲገደሉ ይህ የመጀመሪያ አይደለም” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
May 21, 2014
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ አባል ነበሩ። ከመንግሥታዊ ሥልጣናቸው ከለቀቁ በኋላም በግል ተወዳድረው ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመርጠዋል። በግል የተቃውሞ እንቅስቃሴም ተሳትፈዋል። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን በሊቀመንበርነት መርተዋል። ከአራት ወራት በፊት ግን ከፖለቲካ አባልነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀዋል። ሰሞኑን ከአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተነሱ ተቃውሞዎችን አስመልክቶ አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች በተነሳ ሰሞኑን ተቃውሞ ሰዎች ለሞት እና ለጉዳት ተዳርገዋል፤ ንብረቶች ወድመዋል ይህን ጉዳይ እንዴት ተከታተሉት?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ይህ ክስተት በጣም ያዘንኩበትና የደነገጥኩበት ነው። ምክንያቱም ተማሪዎችና ሌሎች ዜጎች የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱ ብቻ አይደለም፣ በዚህ ጊዜ ከተከሰቱ ጉዳዮች አንዳንዶቹ በጣም መጥፎና አሰቃቂ መሆናቸው ነው። ሰብዓዊ ፍጡር አያያዝ በተመለከተ መጥፎ ሁኔታዎችን እስማ ነበር። ጭካኔዎች የታዩበት ክስተት ነው። አልፎ ተርፎም ጉዳዩ ወደአልተፈለገ የብሄር ጥላቻ የወረደበትን ሁኔታ በአንዳንድ ቦታዎች ተፈጥሮ ነበር። በተለይ በአምቦ የተከሰተው ተቃውሞ ሰዎች ሲጎዱ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት አቶ ጁነዲን በነበረ ጊዜ በአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) (1995 ወይም በ1996 ዓ.ም ይመስለኛል) ረብሻ ተነስቶ በጥይት ሰዎች ሞተዋል። ያን ጊዜ በጣም የተቸነውና የገመገምነው እንዴት ለሰላማዊ ተቃውሞ ጥይት ትጠቀማላችሁ በሚል ነበር። በወቅቱ ለዚህ ጥያቄ የተሰጠው መልስ እኛ ለልማቱ በቂ ገንዘብ የለንም፣ ስለዚህ ረብሻ ሲነሳ የምናቆምበት ሌላ መንገድ የለም የሚል ነበር። አሁንም ያንኑ ነው የደገሙት። ያ ጊዜ ካለፈ 10 ዓመት ይሆነዋል፣ ከዚያ ወዲህ ፖሊስን አስታጥቀው፣ አሰልጥነው፣ ሰላማዊ ሰልፍን በሠላማዊ መንገድ የመቆጣጠሪያ መንገዶች ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ነበር። ነገር ግን አሁንም ችግሩን ለማርገብ ጥይት መመረጡ አሁንም ገና ኋላቀር ነን ወይ የሚል ነገር በውስጤ ፈጥሯል። ባለፈው ሳምንት ደምቢዶሎ አካባቢ ተማሪዎች ረብሸው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ፖሊስ አስለቃሽ ጢስ ተጠቅሞ ተቃውሞውን መቆጣጠር ችሏል። አንዳንድ ቦታ የዚህ ዓይነት የመሰልጠን ምልክቶች መታየታቸው ጥሩ ነው። ግን በአጠቃላይ ሁከትን በሠላማዊ መንገድ የመቆጣጠር ጉዳይ ገና ኋላቀር ደረጃ ላይ ነን የሚል ስሜት ነው የተሰማኝ።
በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ ሰዎች ስሜታዊ እና ግብታዊ የመሆን ጉዳይም መኖሩን ታዝቤአለሁ። አንድ ነገር ሲከሰት ተናድዶ ወደተቃውሞ የመሄድ ነገር አለ። በተቃውሞ ጊዜ ሳትዘጋጅ፣ ሳትደራጅ፣ ተቃውሞ ሲወጣ ምንድነው መፈክር ይዘን የምንወጣው፣ እነማን ይሳተፋሉ፣ በመካከል ችግር ቢፈጠር እንዴት እንቆጣጠረዋለን ተብሎ መታሰብ ነበረበት። ምክንያቱም በተፈጠረው አጋጣሚ ሰልፈኛውን የሚጎዳ ድርጊት ሊፈፀም ይችላልና። ወይንም በሰልፈኞች መካከል ሆነው በንብረት እና በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉና አስቀድሞ እነዚህ ጉዳዮች ሊታሰብባቸው ይገባ ነበር።
ሰንደቅ፡- ምን ተሰማዎት ሁኔታውን ሲሰሙ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- እጅግ በጣም ነው ያዘንኩት። የማስተርፕላኑ ጉዳይ ሲመጣ የሚያናድዱ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ተናደህ በምትወጣበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በዚህ መልኩ በስሜት ሰዎች አደባባይ ሲወጡ እንዴት ነው የምንቆጣጠረው የሚለው በመንግስት በኩል ዝግጅት ያለመኖር ነገር አይቼበታለሁ።
ሰንደቅ፡- ማስተር ፕላኑን በሚመለከት በተደጋጋሚ ከመንግስት የተሰጠው መግለጫ ሁለቱንም ክልሎች የሚጠቅም እንጂ የአንዱን መሬት ቆርሶ ወደሌላ የሚያስተላልፍ አይደለም የሚል ነው፣ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- የአዲስ አበባ አስተዳደር ይህን ቢልም፣ ባይልም ያለነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ነው። እድገት፣ ልማት ይመጣል እና ዘመናዊ የመሆን ሁኔታ ይከሰታል፣ ይሄ የማይካድ ነው።
ሰንደቅ፡- ማስተር ፕላኑ ቢኖርም፣ ባይኖርም ማለትዎ ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ! ይከሰታል። አብዛኛው ሕዝብ በአርሶአደርነት መተዳደሩን ትቶ ወደከተማ ይወጣል። ጥቂት አርሶአደሮች ይቀሩና በዘመናዊ አስተራረስ ብዙ ያመርታሉ። ትንሽ አርሶ አደሮች ብዙ አምርተው ከተማውን ይመግባሉ። አሁን አሜሪካ የእርዳታ እህል የሚሰጡን ጥቂት አርሶአደሮች ትርፍ እህል ጭምር ማምረት በመቻላቸው ነው። ይሄ የማይቀር ነው። ለምሳሌ እስከአዳማ ድረስ ይሄ ፈጣን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ቢዘረጋ ጥሩ ነበር። ሠራተኛ ከዚያ ወደዚህ ተመላልሶ መስራት ይችላል። ወደአምቦ ባቡር ቢገባ በጥቂት ደቂቃዎች አገልግሎት መስጠት ይቻላል። ይሄ ዓይነት የልማት መቀናጀት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በሒደት በትራንስፖትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ትስስሩ መጥበቁ አይቀርም። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኦሮሚያ አካባቢዎች ይገኛል። ቆቃ፣ ግልገልጊቤ፣ መልካሳ፣ ባሌ ከመሳሰሉት ከወንዞች የሚገኝ ኃይል ወደሌሎች ክፍሎች ይሰራጫል። ህዝቡ ግን አያገኝም፣ የተወሰኑ ከተሞች ብቻ ናቸው እየተጠቀሙ ያሉት። እናም ከልማት አኳያ ከሆነ ነገሩ ጥሩነው። ይህንን የሚጠላ ሰው ያለ አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- ለተቃውሞው መነሻ ታዲያ ምንድነው ይላሉ? መንግስት እንደሚለው ሁኔታውን አለመረዳት ወይንም የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ! ይከሰታል። አብዛኛው ሕዝብ በአርሶአደርነት መተዳደሩን ትቶ ወደከተማ ይወጣል። ጥቂት አርሶአደሮች ይቀሩና በዘመናዊ አስተራረስ ብዙ ያመርታሉ። ትንሽ አርሶ አደሮች ብዙ አምርተው ከተማውን ይመግባሉ። አሁን አሜሪካ የእርዳታ እህል የሚሰጡን ጥቂት አርሶአደሮች ትርፍ እህል ጭምር ማምረት በመቻላቸው ነው። ይሄ የማይቀር ነው። ለምሳሌ እስከአዳማ ድረስ ይሄ ፈጣን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ቢዘረጋ ጥሩ ነበር። ሠራተኛ ከዚያ ወደዚህ ተመላልሶ መስራት ይችላል። ወደአምቦ ባቡር ቢገባ በጥቂት ደቂቃዎች አገልግሎት መስጠት ይቻላል። ይሄ ዓይነት የልማት መቀናጀት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በሒደት በትራንስፖትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ትስስሩ መጥበቁ አይቀርም። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኦሮሚያ አካባቢዎች ይገኛል። ቆቃ፣ ግልገልጊቤ፣ መልካሳ፣ ባሌ ከመሳሰሉት ከወንዞች የሚገኝ ኃይል ወደሌሎች ክፍሎች ይሰራጫል። ህዝቡ ግን አያገኝም፣ የተወሰኑ ከተሞች ብቻ ናቸው እየተጠቀሙ ያሉት። እናም ከልማት አኳያ ከሆነ ነገሩ ጥሩነው። ይህንን የሚጠላ ሰው ያለ አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- ለተቃውሞው መነሻ ታዲያ ምንድነው ይላሉ? መንግስት እንደሚለው ሁኔታውን አለመረዳት ወይንም የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- የውጪ ኃይሎች በሁኔታው ሊጠቀሙ ይችሉ ይሆናል። በኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን ወደድንም፣ ጠላንም ገና ያልተፈታ ጥያቄ አለ። የብሔርተኝነት ጥያቄ አለ። አንዳንዱ የኢትዮጵያ አንድነት ይላል፣ ሌላው የለም፣ በተቃራኒው የአንድ ብሄር ጉዳይ ማቀንቀን ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ መነጠል አለብን የሚሉ ኃይሎች አሉ። ሁለቱም ብሄርተኞች ናቸው። ለምሳሌ አንድ ጃዋር መሀመድ የሚባል ሰው በአልጀዚራ ቴሌቭዥን ቀርቦ ሲጠየቅ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ከዚያ ነው ኢትዮጵያዊነቴ የሚመጣው ብሎ ተናግሮ ነበረ። እነኚህ የኢትዮጵያ ብሔርተኛ ደግሞ እንዴት ኦሮሞ ነኝ ይላል ብለው በጣም ተቃወሙት። ሁለተኛ የሚኒሊክ መሞት 100ኛ ዓመት መጣ። በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀነቅኑ ቡድኖች ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉ፣ ዘመናዊነትን ያመጡ እያሉ ያሞግሱ ነበር። በሌላ በኩል በሚኒሊክ ወረራ ጊዜ ግን የተፈፀሙ ችግሮች ግን ነበሩ። ፈለግንም፣ አልፈለግንም፤ አመንም፣ አላመንም የዛሬዋ ኢትዮጵያ የተመሰረተችው በአፄ ሚኒሊክ ጊዜ ነው። ያ የሆነው በወረራ ነው። አዲስአበባ የተቆረቆረችው በ1879 ዓ.ም ነው። በወረራ ስለሆነ ያንን የሚያስታውሱ ደግሞ በብሔር እና በማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች ደግሞ የአፄ ሚኒልክ ሐውልት ከአዲስ አበባ መነቀል አለበት የሚለውን አስተሳሰብ ያራምዳሉ። ቴዲ አፍሮ የተባለው ድምፃዊ የሚኒሊክ ጦርነት ቅዱስ ጦርነት ነው ብሏል በሚል እነዚህ በብሔር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች በመቃወማቸው ልጁ በበደሌ ቢራ ስፖንሰርነት ሊያካሂድ የነበረው ኮንሰርት እስከመሰረዝ መደረሱን እናስታውሳለን። ይህ ከሆነ በኋላ የኦኖሌ ሃውልት ጉዳይ መጣ። ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች በፅሁፍ የሠፈረ ታሪክ የላቸውም። የሚያስታውሱት ከአባት፣ ከአያት የተላለፈ አፈ ታሪክ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያልፉ ታሪኮች አሉ። ሚኒሊክ በ1874 እስከ 1879 ድረስ ሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎችን ከወረሩ በኋላ አርሲን መውረር አልቻሉም ነበር። እንዲያውም አርሲዎች በጦርነት ገጥመዋቸው በማሸነፍ አፄ ሚኒልክን አባረዋል። በመጨረሻ ብዙ ኃይል ካከማቹ በኋላ ነው ከአራት ዓመት በኋላ ተንቀሳቅሰው አርሲን ማስገበር የቻሉት። በወቅቱ በ1879 መስከረም ወር በተካሄደው ጦርነት በአጎታቸው ራስ ዳምጠው መሪነት ወደ 12ሺ ሰዎች መጨፍጨፋቸው ይነገራል። በዚያን ጊዜ ወታደሮቹ መጥፎ ነገሮች ማለትም ጡት መቁረጥ፣ እጅ መቁረጥ የመሳሰሉ ግፎችን ፈፅመው ነበር ይባላል። ያንን ለማስታወስ ሐውልት ቢያቆሙ እንዴት የዚህ አይነት ሐውልት ያቆማሉ፣ ይሄ ቂምና በቀልን ማስፋፋት ነው ተብሎ ተተችቷል። ይሄ ከሆነ በኋላ በቅርቡ በባህርዳር ላይ በተካሄደ ስፖርታዊ ውድድር ላይ የታየው ዘረኝነት በጣም መጥፎ እንደነበር ነው የሰማሁት። ፕሬዚዳንቱ ወደስታዲየሙ ሲገቡ የተቃውሞ ጩኸት ሁሉ ነበር ነው የተባለው። እዚያ የተነገረውን መጥፎ ነገር ሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ሰምተዋል። ይህ ቁጣ ቀስቅሷል። ይሄ ሁሉ እያለ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ይመጣል። ይህ ማስተር ፕላን በቅርቡ አዳማ ላይ ውይይት ተካሂዶበታል አሉ። የተሳተፉት የአዲስአበባና የኦሮሚያ ሰዎች ናቸው። ያን ጊዜ ተቃውሞ ነበር። ኤክስፐርቶቹ ተቃውሞውን በማውገዝ ይሄ ጠባብነት ነው፣ ብትፈልጉም፣ ባትፈልጉም ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ይሆናል የሚል አስተያየት ሰጡ መባሉንም ሰምተናል።
ሰንደቅ፡- ከማስተር ፕላኑ ትግበራ በፊት ግን ኦሮሚያ ከአዲስአበባ ማግኘት ያለባት ጥቅም ጉዳይ መመለስ አልነበረበትም?
ዶ/ር ነጋሶ፡- በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በተመለከተ ሰፍሯል፣ ለዚህም ሕግ ይወጣል ይላል። እንግዲህ ተመልከት፤ ሕገመንግስቱ ከወጣበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ሲቆጠር 19 ዓመት ነው። 19 ዓመት ሙሉ ይሄ ሕግ አልወጣም። እንዲያውም በ1998 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለፌዴሬሽን ም/ቤት ስለዚህ ጉዳይ በደብዳቤ ጠይቆ ፅፎ ነበር። በሕገመንግስቱ ላይ የኦሮሚያ ጥቅምን በሚመለከት ሕግ ይወጣል የሚለው ምን ማለት እንደሆነ እንዲተረጎምና ሕጉ እንዲወጣ ብሎ ጠይቆ ነበር። ያውም ይህ ጥያቄ የቀረበው ሕገመንግሥቱ ከወጣ ከ10 ዓመት በኋላ ነው። መልስ ግን አልተሰጠውም።
ሰንደቅ፡- ሕገመንግሥቱን ካረቀቁ ኢትዮጵያዊያንም አንዱ እንደመሆንዎ መጠን በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ኦሮሚያ በአዲስአበባ የሚኖረውን አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ልዩ ጥቅም እንደሚጠበቅለትና ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን ደንግጓል። በወቅቱ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ታሳቢ ያደረገው ምንድነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ይህንን በተመለከተ ነገሩን እንደገና ለማስታወስ፣ የሕገመንግሥቱ ቃለጉባኤ አንብቤአለሁ። ልዩ ጥቅም ሲባል የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ቢሮዎችን ለመስራት ቢፈልግ መሬት በነፃ የማግኘት ጉዳይ፣ ህንጻዎች ካሉ በነፃ የማግኘት ጉዳይ ይመለከታል።
ሰንደቅ፡- ግብርን ይመለከታል?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ግብርን አይመለከትም። ያን ጊዜም ይሄ ጉዳይ ተነስቶ በግልፅ ግብርን እንደማይመለከት መልስ ተሰጥቶበታል።
ሰንደቅ፡- የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር ሆነው በአንድ ወቅት እንደመስራትዎ፣ በተለይ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም በሚመለከት ከፍተኛ አመራሩ በግልፅ የሚወያይበት፣ ጥቅሙን ለማስከበር የሚሞክርበት እድል ነበረው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበርኩበት ወቅት የኦህዴድ የሥራ አስፈፃሚ አባል ነበርኩ። በዚያ ላይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ይሄ ሕግ እንዲወጣ ጠይቀናል። ጉዳዩም ያስጨንቀን ነበር። በወቅቱ እኔ የካቢኔ አባል ስላልነበርኩኝ፣ በመንግሥት ጉዳይ ስለማልገባ በምሳተፍባቸው የኦህዴድ እና የኢህአዴግ መድረኮች ላይ ጉዳዩ በተደጋጋሚ ተነስቷል። ይሄ ብቻ አይደለም፤ አቶ ዓሊ አብዶ የአዲስ አበባ ከንቲባ ነበሩ። ያን ጊዜም የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ድንበር መካለል አለበት፣ አሁን ካልተካለለ ኋላ ችግር ያመጣል ብለን እንሞግት ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ዓሊ አብዶ እና አቶ ሐሰን ዓሊ ቶሎ ብለው ኮሚቴ አቋቁመው እንዲያስፈፅሙ በኦህዴድ ደረጃ ተወስኖ ነበር።
የደርግ ማስተር ፕላን የትናየት ይደርስ ነበር። አሰላ፣ አምቦ፣ ፍቼ፣ ደብረብርሃን ይደርስ ነበር። በሽግግር ጊዜ የማስተር ፕላን ክለሳ ጉዳይ መጣ። በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ አዲስ አበባ በጣም ትንሽ ነበረች። ይህም አይሆንም ቢያንስ እስከ ለገጣፎ፣ በዚህኛው እስከአቃቂ፣ በሌላ በኩል እስከ ቡራዩ እንዲወሰን አስተዋፅኦ አድርገናል።
ሰንደቅ፡- ሕገመንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ አለመከበር ወይንም ዝም መባሉ አሁን ለተፈጠረው ችግር እንደአንድ መንስኤ መውሰድ ይቻላል?
ዶ/ር ነጋሶ፡- በትክክል። 19 ዓመት ሙሉ አንተ ባለቤቱ ካላስታወሰ ማነው የሚያስታውሰው? የኦሮሚያ ክልል ሕገመንግሥቱ ከወጣ ከ10 ዓመት በኋላ በደብዳቤ ጠይቆ ምላሽ አላገኘም። ከዚያ ወዲህ በተግባር ያየነው ነገር የለም።
ሰንደቅ፡- ለዚህ ችግር ኃላፊነት የሚወስደው ማነው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ክልሉን የሚመራው ኢህዴድ ራሱ ነው። የልዩ ጥቅም ማግኘት ብቻ አይደለም። ጉዳዩ በሕገመንግሥቱ ውይይት ጊዜ ተነስቷል። አዲስ አበባ የኦሮሚያም ዋና ከተማ ናት ሲባል የተቃወመ ሰው አልነበረም። ይሄ በኦሮሚያ ሕገመንግሥት ውስጥ ሰፍሯል። እና ባልሳሳት በ1995 ወይም በ1996 ዓ.ም ይመስለኛል የኦሮሚያ ዋና ከተማ ወደአዳማ እንዲዛወር ተደረገ። ያኔ እነአቶ ቡልቻ ሁሉ መስቀል አደባባይ ለተቃውሞ ወጥተው ተደብድበዋል። በወቅቱ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተቃውሞ ተነስቶ ጉዳት ደርሷል። ወደ 300 የሚሆኑ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታቸው ተባረዋል፣ አንዱ የወንድሜ ልጅ ነበር። ያንን ካደረጉ በኋላ ቅንጅት ሲያሸንፍ ኦሮሚያን ህዝብ ለማጓጓት ተብሎ መቀመጫው ወደአዲስ አበባ እንዲመለስ ተደረገ። ይህ ብቻ አይደለም፤ የተገቡ ቃሎችም ነበሩ። በአዲስ አበባ ለኦሮሞዎች የባህል ማዕከል እንዲሰራ፣ (አሁን ስታዲያም አካባቢ እየተሰራ ያለው ነው)፣ በተመሳሳይ በየክፍለ ከተማው የባህል ማዕከል እንደሚሰራ፣ ለሥራ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡና ሌሎችም ልጆቻቸው በኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማር ለሚፈልጉ በየአስሩ ክ/ከተሞች አንድ፣ አንድ ት/ቤቶች ይሠራሉ ተብሎ ተወስኖ ነበር። ያ እስከአሁን አልተደረገም። የባህል ማዕከሉም ዘንድሮ ዘጠነኛ ዓመቱ ነው፣ አልተጠናቀቀም። በየክፍለከተማው ይሠራሉ የተባሉትም አልተሠሩም። ይህንን ተከታትሎ የኦሮሚያ ጥቅም እንዲከበር አለመደረጉን በተመለከተ ክልሉን የሚመራው ኦህዴድ ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል።
0 comments:
Post a Comment