Thursday, 29 May 2014

በቡራዩ ኦሮሚያ ፖሊስ የታፈነው አስራት አብርሃም “ፍትህ እፈልጋለሁ” አለ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) ባለፈው ሳምንት በቡራዩ የኦሮሚያ ፖሊስ ከታሰረ በኋላ፤ ፖሊስ “የት እንዳለ አላቅም” ማለቱ ይታወሳል። በወቅቱ ታስሮ የነበረው አስራት አብርሃም፤ አሁን በህይወት መኖሩ ተረጋግጧል። ከአገር ቤት ባስተላለፈውም መልእክት “ፍትህ እፈልጋለሁ” የሚል አጭር ጽሁፍ ልኳል። ከዚህ የሚከተለው ነው።

Asrat Abraha
Asrat Abraha
ቡራዩ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ “አስራት አብርሃም የሚባል ሰው አላሰርኩም” እያለ ሲምል ሲገዘት ሰንብቶ በኋላ ከየት አምጥቶ ወደ ፍርድ ቤት ሊያቀርበኝ እንደቻለ በህግ መጠየቅ እፈልጋለሁ። አንድን ሰው ወንጀል ካለበት አስሮ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንጂ ይዞ መሰወር ከባድ ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑ መታወቅ አለበት።
እኔ ደግሞ እስረኞች ለመጠየቅ በሄድኩበት ፖሊስ ጣቢያ ነው የተያዝኩት፤ ከፖሊስ ጣቢያ አውጥተው በማይታወቅ ቦታ ያሰሩኝ፤ ቤተሰብና የፓርትዬ የአመራር አባላት እኔን ለመጠየቅ ሲመጡ ደግሞ “እኛ ጋ የለም፤ አላሰርነውም” በማለት የፈለጉትን ሰው ማሰርና ደብዛውን ማጥፋት እንደሚችሉ ያሳዩበት አጋጣሚ ነው። በዚህ ላይ የፖሊስ ጣቢያው ኮማንደር ተስፋስላሴ ነገራ በራሱ ቢሮ ውስጥ እንድደበደብ አድርጓል። ይሄ ነገር በእኔ ላይ የተጀመረ ነው ብዬ አላስብም፤ እንደሚታወቀው በዚህች ሀገር በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰዎች በየጊዜው ደብዛቸው እንደሚጠፋ ነው የሚነገረው፤ በየከተማው የምናየው “የአፈልጉን” ማስታወቂያዎችም አለምክንያት አልበዙም። ምን ይታወቃል በመንግስት የድህንት ኃይሎች ታፍነው ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርጎ ቢሆንስ!
ስለዚህ እኔ ይህን ጉዳይ ከዳር ለማድርስና በዚያም በሀገሪቱ ያሉት የህግና የሰብአዊ መብት ተቋማት ለመፈተሽ በህግ ሊሄድበት እያሰብኩ ነው። በመሆኑም የህግ ድጋፍ የሚያደርግልኝ ግለሰብም ሆነ ተቋም እፈልጋሁና ሞያውና እድሉ ያላችሁ ሁሉ ሞያዊ ድጋፍ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ፤ ይሄ ነገር ዝም ብለን ካፍነው በዚሁ ሊቆም አይችልም፤ በሌሎችም ላይ ሊቀጥል የሚችል ጉዳይ ነው። በአግባቡ መወገዝና በሰብአዊ ተቋማት ሁሉ መታወቅ አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ፤ እኔ ደግሞ አቅሜን የፈቀደው ሁሉ ይሄ ነገር ዳር ለማድረስ ወደኋላ አልልም። በዚህ ጉዳይ ላይ ከጎኔ የሚቆሙ ወገኖች እንደሚኖሩ ተስፋ አደርጋለሁ።

0 comments:

Post a Comment