Tuesday 20 May 2014

ትናንት በተካሄደ ሌላ ችሎት ካሁን ቀደም በነጻ ከተለቀቁት ሙስሊሞች ሁለቱ እንዲከላከሉ ተወስኖባቸዋል!

(EMF) የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከታሰሩ አመት አለፋቸው። እነዚህ መፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ሲነሱ የነበሩትን በርካታ ጥያቄዎች ወደ መንግስት አካላት ወስደው፤ የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ በአግባቡ ለመንግስት ለማቅረብ ብሎም በጥያቄ አቅራቢዎቹና እና በከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል መግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው – ዋና አላማቸው። ሆኖም መንግስት እነዚህኑ መፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት በሙሉ “አሸባሪዎች” ተብለው ከታሰሩ በኋላ “ብጥብጥ አስነስታችኋል፤ አሳድማችኋል” በሚሉ ልዩ ልዩ ክሶች አሁንም በ እስር ላይ ናቸው። ባለፈው ታህሳስ 23 በዋለው ችሎት ከህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር ታስረው ከነበሩት ውስጥ 10 በነፃ መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡ በነፃ ከተሰናበቱት ውስጥ አራቱ ይግባኝ ተጠይቆባቸው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ ትላንት በዋለው ችሎት አቶ አሊ መኪ እንዲሁም ሀጅ አብዱረህማን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው መሆኑን ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው ዘግቧል።
የጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው ዘገባ ዛሬም ቀጥሏል። ችሎቱ ዛሬም የቀጠለ መሆኑን ነው ዘገባው የሚያብራራው። “ከትናንት የቀጠለው ችሎት ዛሬም ምስክሮችን መስማቱን ቀጥሏል፡” በማለት ዘገባውን ጀምሯል – የሱፍ። ሙሉውን ዘገባ ከዚህ በታች ያንብቡ።
በትናንትናው እለት በጠዋቱና በከሰአቱ ችሎት ተማሪ አቡበከር መሀመድ ምስክርነቱን መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በአወሊያ ተቃውሞ አነሳስ ዙሪያም የነበረውን ነገር ቀድመውት እንደነበሩት መስካሪዎች በትክክል አስቀምጧል፡፡ በተለይም ተማሪዎች ገና ተቃውሟቸውን ማሰማት ሲጀምሩ መጅሊስ ቢሮ ጠርተው ያነጋገሯቸው አቶ አህመዲን አብዱላሂ ጨሎ ግድ የለሽነታቸውን ሲገልጹ ‹‹እንኳን እናንተ ይቅርና አዲስ አበባ ህዝብ በሙሉ ጨርቁን ጥሎ ቢያብድ ግድ አይሰጠንም›› ማለታቸውና 3 አመት ተምረው ሊመረቁ 3 ወር የቀራቸውን ተማሪዎች ከማባረር እስኪመረቁ እንዲጠብቁ ሲለምኗቸው ‹‹እንኳን 3 ወር ቀርቶ 1 ቀን እንኳ ቢቀራችሁ አትመረቁም›› ብለው መመለሳቸው ለሰሚው ሁሉ የሚያሳዝን ሆኖ ነበር፡፡
ተማሪዎች የተቃወሙት በወቅቱ የነበረውን የአህባሽን አስተሳሰብ አስገድዶ የመጫን እርምጃ መሆኑን በዝርዝር የገለጸው ተማሪ አቡበከር አቶ አህመዲን በግልጽ ‹‹የእኛን አስተሳሰብ አህባሽን ካልተቀበላችሁ አብረን አንቀጥልም›› ብለው በዚሁ ስብሰባ ላይ ቁርጡን እንደነገሯቸው አስረድቷል፡፡ የካሪኩለሙ መቀየር ዓላማም ይኸው የአህባሽ አስተሳሰብ ጠመቃ መሆኑን የተረዱትም በዚህ ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡
በተለይም ተማሪው ለጥያቄው መልስ በሚፈልግበት እና ቁጣውን በሚገልጽበት ወቅት የመጅሊሱ ጸሀፊ አቶ አልሙሀመድ ሲራጅ ‹‹እናንተ ምንም አያገባችሁም! ምንም አታመጡም! አርፋችሁ ተቀመጡ!›› ማለታቸውና ተማሪዎች ላይ አብረዋቸው ከመጡት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ጋር ማፌዛቸው ተቃውሞውን ማቀጣጠሉን ተናግሯል፡፡
ተማሪ አቡበከር ከሰዓት በዋለው ችሎትም ከዓቃቤ ህግ ለቀረቡለት መስቀለኛ ጥያቄዎች በጥሩ ሁኔታ መልስ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና በታህሳስ 23 በነጻ እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው 10 ሙስሊሞች መካከል አራቱ ላይ በአቃቤ ህግ የቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ ሁለቱ ላይ ‹‹ይከላከሉ›› የሚል ብይን ተሰጥቷል፡፡ ነጻ ተብለው ከተፈቱ በኋላም ፍርድ ቤት ሲያመላልሳቸው ከከረመ በኋላ የይከላከሉ ብይን የሰጠባቸው ሁለት የቀድሞ ታሳሪዎች ጀግኖቻችን ወንድም አሊ መኪ እና ሐጂ ዐብዱረህማን ዩሱፍ ሲሆኑ ከቀሪዎቹ ታሳሪዎቻችን በተለየ ችሎት ጉዳያቸው ሊታይ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

0 comments:

Post a Comment