Wednesday 7 May 2014

የዞን ዘጠኝ አባላት ሕዝብ እንዳያውቅ በዝግ ችሎት ነው ጉዳያቸው የታየው ፣ እንደገና ለ10 ቀን ተቀጠሩ


አቡጊዳ 

ዞን ዘጠኞች እንዲሁም ጋዜጠኛ አስማማዉ፣ ተስፍዳ አለም እና ኤዴም ፍርቅ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው በዝግ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል። ፖሊስ እንደገና ለ10 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠ ሲሆን ፣እስረኞቹ ጠበቃቸውን ለማየት እድል ያገኙት እዚያው ፍርድ ቤት ነበር።
ዝርዝር ዘገባዉ ዳዊት ሰለሞን እና ብስራት ወ/ሚካኤል እንደሚከተለው አቅርበዉታል፡
ዳዊት ሰለሞን
አስማማው፣ተስፋለም፣ኤዶም፣ዘላለም፣አጥናፍና ናትናኤል አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ሲደርሱ የጭንቅላታቸው ጭማቂ የሆኑ ፊደላትን በኮምፒዩተር ኪቦርድ የሚመቱቡባቸው ሁለት እጆቻቸው ካቴና ጠልቀውላቸው ነበር፡፡
ዲፕሎማቶች፣የውጪ አገር ጋዜጠኞች፣ቤተሰቦቻቸውና የሞያ አጋሮቻቸው ታሳሪዎቹ ነፍጥ ባነገቱ ወታደሮች ታጅበው ሲገቡ እጆቻቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡እስረኞቹን በፍርድ ቤት ለመወከል ስምምነት የፈጸሙት ጠበቃ አምሐ ደምበኞቻቸው ወደ ሚገኙበት ማዕከላዊ ለጥየቃ ሲመላለሱ ቢቆዩም ፈቃድ በማጣታቸው ልጆቹን የተመለከቷቸው እንደ ሁላችንም ግቢውን በረገጡበት ቅጽበት ነበር፡፡
በአንጻሩ የከሳሽ ጠበቆች(ዐቃቤ ህግ) ከተያዙበት ቅጽበት አንስተው ኬዙን ሲያጠኑና ሲያስተነትኑ መክረማቸውን መገመት አያዳግትም፡፡
ህገ መንግስቱ ለግልጽ ችሎት እውቅና ቢቸርም የጋዜጠኞቹ ጉዳይ የተሰማው በዝግ ችሎት ነው፡፡ህዝብ መረጃ የማግኘት መብት ቢኖረውም ቢያንስ ጋዜጠኞች ጉዳዩን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ፈቃድ መስጠት አለመቻሉም አሳዛኝ ነው፡፡
ጠበቃ አምሐ እንደነገሩን ከሆነ አቃቤ ህግ ክሱን ከሽብርተኝነት ጋር እንዲያያዝ አድርጓል፡፡በሁኔታው በጣም ያዘኑት ጠበቃው በቀጣዩ ቅዳሜ ማለትም ግንቦት 9/2006 ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡የአስር ቀን ቀጠሮ ለፖሊስ የተፈቀደለትም‹‹ያልያዝኳቸው ግብረ አበሮቻቸውና ያልሰበሰብኳቸው ወረቀቶች አሉ››በማለቱ እንደሆነም ጠበቃው ገልጸዋል፡፡
ደምበኞቻቸውን እርሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ሊጠይቋቸው አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ በመናገራቸውም ዳኛው ፖሊሶቹ ታሳሪዎቹ በሰው እንዲጎበኙ እንዲያደርጉ ማዘዛቸውም ተሰምቷል፡፡
ታሳሪዎቹ ከፍርድ ቤት ሲወጡ አንድ ወጣት ፎቶ ግራፍ ሊያነሳ ይሁን የእጅ ስልኩ በማንቃጨሉ ሊያናግር ወደ ፊቱ ሲያስጠጋ ፖሊሶች ‹‹ፎቶ ልታነሳ ነው ››በማለት አንድ ጥፊ አሳርፈውበት ከጋዜጠኞቹ ጋር ወደ ማዕከላዊ ወስደውታል፡፡
ብስራት ወ/ሚካለል እንዲ ዘግቧል
ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ከጠዋቱ 4፡00ሰዓት የነበረው ቀጠሮ ባልታወቀ ምክንያት ወደ 8፡00 ሰዓት ተዛውሮ ነበር፡፡ በ8፡00 ሰዓት በነበረው ቀጠሮም አጥናፍ ብርሃን፣ ኤዶም ካሳዬ እና ናትናኤል ፈለቀ በመጀመሪያው ዙር ወደ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ በ9፡00 ሰዓት ደግሞ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋዓለም ወልደየስ እና ዘለዓለም ክብረት ቀርበዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ ፖሊስ) ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቁ ለቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ በዝግ ችሎት ነው በሚል ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ጓደኛ እንዲሁም በስፍራው የነበሩ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ፣የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ችሎቱን መታደምም ሆነ መግባት በመከልከሉ ጉዳዩ በዝግ ችሎት ተከናውኗል፡፡
ቀሪዎቹ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ እና ማህት ፋንታሁን ነገ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡ የዛሬ ፍርድ ቤት ሌላ ለየት ያለው ክስተት የህግ ባለሙያ የሆነው ወጣት ኪያ ፀጋዬ ችሎቱን ለመታደም አራዳ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ፎቶ አንሰተሃል በሚል በማዕከላዊ ፖሊ ከነ ስልኩ ከታሳሪዎቹ ጋር ተይዞ ተወደስዷል፡፡ ኪያ ፀጋዬ ይህ እስከተፃፈ ድረስ አልተለቀቀም፡፡ የውስጥ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ ከነገ ጀምሮ ታሳሪዎቹን በታሰሩበት ማዕከላዊ እስር ቤት ሄዶ መጎብኘት እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡

0 comments:

Post a Comment