በዛሬው እለት ማለትም 09/09/2006 ዓ.ም በጠዋቱ ፈረቃ የአንድነት ፓርቲ መሰረታዊ መርሆዎችና ፓርቲው የሚመራበት ርዕዮት አለም፤የመሬት ፖሊሲ፤ፌደራሊዝም እና የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ፕሮግራሞችና የአንድነት ፓርቲ ርዕዮት አለምን በንፅፅር ያቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ ኃላፊው በመቀጠል የኢህአዴግ እና የአንድነት ፓርቲ ፕሮግራም መሰረታዊ ልዩነቶችን በማነፃፀር ለሰልጣኞች አስረድተዋል፡፡ ፓርቲው አሁን ያለበትን ደረጃ በተሻለ ሁኔታ አስቀጥሎ እንዲዘልቅ የየወረዳው ህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡የመንግስትነት ሃላፊነትን ህዝቡ ሰጥቶን በፕሮግራሙ ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረግባቸው ቢጠየቅ የፓርቲው አቋም ምን ይሆናል ተብለው በተሳታፊዎች የተጠየቁት ሀላፊው‹‹ህዛባዊ አላማን ያነገብን እንደመሆናች መጠን ለህዝብ ጥያቄ በመቃብራች ላይ ካልሆነ በቀር አንልም ››በማለት ተሳታፊውን ፈገግ ያሰኘ ምልሽ ሰጥተዋል መልሰዋል፡፡
የከሰዓቱን መርሀ ግብር በመሰረታዊ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችና ተልዕኮዎች ዙሪያ ስልጠና የሰጡት የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው የህዝብ ግንኙነት ምንነትና በአለማቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ትንታኔ ያቀረቡ ሲሆን በሀገራችን ያለው የህዝብ ግንኙነት ሙያ ክብር የተሰጠው ባለመሆኑ ከሳይንሳዊ ትንታኔ አንፃር ያለው ቦታ አናሳ ነው ብለዋል ፡፡ እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ የህዝብ ግንኙነት ሙያ ለአንድ ተቋም ራሱን ችሎ መቆም የጀርባ አጥንት በመሆኑ እያንዳንዱ የዚህ ስልጠና ተሳታፊ የሰለጠነና ዘመኑን የዋጀ አስተምህሮ ላይ ራሱን በማስደገፍ በእውነትና በእውቀት የተደገፈ የህዝብ ግንኙነት ስራን መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ስልጠናውን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ግንኙነት ከፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ጋር በጋራ በመተባበር ሲሆን ስልጠናው በመላ ሀገሪቱ ባሉት አደረጃጀቶች ቀጣይነት እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
0 comments:
Post a Comment