Saturday, 24 May 2014

ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር ፤ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ – ግንቦት ፲፩/2ዐዐ6 ዓ.ም

                                    10298794_640348846050053_3108728034139348229_n
የአንድነት የድጋፍ ማህበር በሰሜን አሜሪካ በቅርቡ የተካሄደውን የንፁሐን ዜጐች ግድያና ማሰቃየት እንዲሁም ዜጎችን አገራችሁ አይደለም ተብለው ከቅያቸው የማፈናቀሉን ተግባራት በእጅጉ ያወግዛል፡፡ የአምቦ እና የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች አገዛዙ ያወጣውን የአዲስ አበባ ማስተር ኘላን በመቃወም ሠላማዊ ተቃውሞ በማሰማታቸው የአካባቢው ባለስልጣናትና የመንግስት ታጣቂዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀም በንፁሐን ዜጐች ላይ የጦር መሣሪያ በመተኮስ የብዙ ሰው ሕይወት አጥፍተዋል፡፡ የቀሩትንም ቢሆን ወደ አልታወቀ ስፍራ በመውሰድ እጅግ በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡ይህ ዓይነቱ ፋሽስታዊ ድርጊት በጥብቅ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ አሁንም፣ ወደፊትም፣ ይኖራሉ፡፡ የባህል፣ ቋንቋ እና ኃይማኖት ልዩነቶች ሳይለያያቸው ተጋብተውና ተወዳጅተው በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሠላም እንዳልኖሩ፧ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በአገዛዙ ባለስልጣናትና በየመገናኛ ዘዴዎች የሚያራግቡትን ሕዝብን የመወንጀልና በቋንቋ ልዩነት አስታኮ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚደረገውን ክፋ የጥፋት ተግባር ማህበሩ አጥብቆ ያወግዛል፡፡
ህውሃት መራሹ መንግስት በስልጣን ላይ ለመቆየት ኳለው ምኞት፤ የአካበቢ ምስለኔዎችን በመመልመል እና ለጥፋት በማሰልጠን ብአዴን፤ ኦሆዲድ ወዘተ እያለ በማደራጀት፤ የአካባቢ ካድሬዎች በሕዝቡ ላይ የሚፈጽሙትን ግድያና ጭቆና በአስቸኳይ እንዲያስቆም ማህበሩ ይጠይቃለ፡፡ ሠልፈኞቹ የአዲስ አበባ አካባቢ ኦሮምኛ ተናጋሪ አርሦ አደሮችን ከይዞታቸው መፈናቀል አሳስቧቸው ተቃውሞ ማድረጋቸው ተገቢ የሆነ ፍትሐዊ ጥያቄ ነው፡፡ ህገ መንግስታዊ መብትም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ህወሃት/ኢህአዴግ ያሰለጠናቸዉ ወታደሮች ያለርህራሄ ህፃናትን እንኳ ሣይለዩ በጅምላ ግድያ ንፁሃን ዜጐችን ጨፍጭፈዋል፡፡ ይህን አረመኔያዊ እኩይ ስራ ያዘዙትም ሆነ የፈጸሙት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማህበሩ ይጠይቃል፡፡
የአንድነት የድጋፍ ማህበር በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ጭቁን አርሦ አደሮችና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች የመሬት ይዞታ መነጠቅ ማህበሩን እጅግ ያሳስበዋል፡፡ ህወሃት/የኢህአዴግ መንግስት መሬት አይሸጥም አይለወጥም እያለ በሌላ በኩል ወገኖቻችን ከገጠር እስከ ከተማ ለዘመናት ይዘውት ከቆዩት ይዞታቸው በኃይል በማፈናቀል፣ በዘመኑ ባለስልጣናት እና በሙስና በተቀነባበረ መልኩ ለውጭ ባዕዳን በኢንቨስትመንት ስም የሃገሪቱን ሃብት መሸጥ በሰፊው ተያይዞታል፡፡ አገዛዙ ይህን ዓይነት እጅግ ከፍተኛ ወንጀል ቆም ብሎ እንዲያስብ ማህበሩ ይጠይቃል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ የከተማውና የገጠሩ ሕዝብ የመሬት ባለቤት እንዲሆን እይፈልግም። ምከንያቱም ካድሬዎቹ እኛን ካልደገፋችሁ መሬት እንቀማችኋለን እያሉ በማስፈራራት ሳይወዱ በግድ የምርጫ ድምፅ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ አገዛዙ የከተማ ቦታን እና የገጠር መሬትን ለምርጫ ድምፅ ማግኛ ዋስትና እየተቀጠመበት ይገኛል፡፡ የዘመኑ ባለስልጣኖች የከተማ ቦታን በህገ ወጥ መንገድ በመቸርቸር ከፍተኛ ገንዘብ ማካበቻ አድርገውታል፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወደ አዲስ አበባ ክልል እንዲሆን ህወሃት/የኢህአዴግ ሲወስን የለመደውን መሬት የመሸጥ ተግባር ለመቀጠል እንጂ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ለልማት ነው ቢባል እንኳን የአርሦ አደሮች ሙሉ መብት እና ፍላጐት ተሟልቶ እንጂ፣ እንደማይጠቅም እቃ ዜጎንች በማፈናቀልና ቤተሰቦቻቸው የጐዳና ተዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ሊሆን አይገባም፡፡ የአንድነት ድጋፍ ማህበር በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ሃብት ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ለዘመኑ ባለስልጣኖች አለመሆኑን ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ ጭቁን አርሦ አደሮች በይዞታቸው የመገልገል ሃብት የማፍራት መብታቸው ያለገደብ እንዲክበርላቸው ያሣስባል፡፡
መሬት የጭቆና መሣሪያ መሆኑ እንዲቀር፣ ዜጐች በይዞታቸው ሙሉ መብት እንዲኖራቸው፣ መንግስት የሃገሪቱን መሬት ለባለስልጣናት እና ለውጪ ዜጐች በህገ ወጥ መንገድ መሸጥና ማከራየት ባስቸኳይ እንዲቆም ማህበሩ ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በዘርና በኃይማኖት ሣይከፋፈል በአንድነት በመነሳት አገዛዙን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ መሰረታዊ የዴሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡ በአምቦና በሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች በጅምላ የታሠሩ እና በስቃይ ላይ ያሉ ተማሪዎች ባስቸኳይ ግድያ የፈጸሙት እና ያዘዙት ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማህበሩ ይጠይቃል፡፡ ዜጎች የፈለገ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋ ፣ ጾታ ይኑራቸው፣ በማናቸውም የአገሪቷ መሬት ያለ ፍርሃትና ያለሰቀቀን የመኖር፣ የመስራት፣ የመነገድ መብታቸው መረጋገጥ አለበት።
ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር
ዋሽንግተን ዲሲ

0 comments:

Post a Comment