Thursday, 22 May 2014

ይሻል መጣ ብዬ ምርኩዝ አስጨበጨ መንገድ ያሳየሁት፣ ለካ ሌላም አይደል ‘ደርጉ’ን ኖሯል እና ‘ኢህአዲግ’ ነው ያልኩት

DERG
ይሻል መጣ ብዬ ምርኩዝ አስጨበጨ መንገድ ያሳየሁት፣
ለካ ሌላም አይደል ‘ደርጉን’ ኖሯል እና ‘ኢህአዲግ’ ነው ያልኩት።
የደርግ እና የኢህአዲግ መመሳሰል ታወሰኝ እና  የኢትዮጵያ ገበሬ ምን ብሎ ያስብ ይሆን? እያልኩ ሳስብ የመጣልኝ ግጥም ነው።
በ 1967 ዓም የንጉሱን ስርዓት ከስልጣን ሲወርዱ በትረ መንግስቱን የተረከበው ደርግ የኢትዮጵያ ሰራዊት አካል በመሆኑ እና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት ላይ የማይደራደር ቢሆንም በአገዛዙ አምባገነንነት ኢህአዲግ ደርግን ተስተካክሎታል ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ረቀቅ ባሉ ተንኮሎች ”ደርግ የዋህ አልነበር እንዴ!” የሚሉ ድምፆች እንዲበራከቱ እያደረገ ነው። በደምሳሳው ስንመለከተው አይመስልም።ወደ ዝርዝር ነገሮች ስንገባ ግን ኢህአዲግ በትክክል የደርግ አምባገነናዊ አገዛዝ ግልባጭነቱ ፍንትው ብሎ ይታየናል።
እስኪ እነኝህን ነጥቦች እንመልከት -
ደርግ ስልጣን ለሕዝብ እመልሳለሁ ብሎ ምሎ ተገዝቶ መልሶ መለዮውን እያወለቀ ስልጣኑን ያዘ።”ሕዝባዊ መንግስት አሁኑኑ” ያሉትን ገደለ። ኢህአዲግም ስልጣንን ለሕዝብ እሰጣለሁ ብሎ ምርጫ አደረገ ተሸነፈ።”ድምፃችን ተሰረቀ” ብለው አደባባይ የወጡትን አያሌዎችን በአደባባይ ገደለ።
ደርግ ልማቱ እየተፋጠነ ነው። ”እየተዋጋን እናመርታለን” ይል ነበር። ኢህአዲግም ”እድገታችን ሁለት አሃዝ ነው” ፀረ ሰላም ኃይሎችን በአንድ በኩል እየተዋጋን ምርታማነትን እንጨምራለን” ይላል።
ደርግ ሕዝቡን በዘር ሳይለይ አኢወማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር)፣ አኢሴማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር) እና ኢገማ (ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር) እያለ ያደራጅ ነበር።
ኢህአዲግ/ወያኔ ረቀቅ አደረገው። በቋንቋ እየሰነጠቀ አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣ሱማሌ እያለ አደራጀው። የኢህአዲግ የከፋ የሚያደርገው  ማህበራትን ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶችን ነው በጎሳ የሚያደራጀው።
ደርግ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ጤፍ አምራች ገበሬዎች ምርታቸውን በአህያ ጭነው አዲስ አበባ ወፍጮ ቤቶች ድረስ አምጥተው እንዲሸጡ ይፈቅድ ነበር (ጅንአድ ከገበሬው መግዛቱን ሳንዘነጋ)። ኢህአዲግ ገበሬዎቹ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ማገድ ብቻ አይደለም ከመሬታቸው ካለ በቂ ካሳ (ይሰመርበት ካለ በቂ ካሳ) ልቀቁ አለ።
ደርግ የብሔር በሄረሰቦች ኢንስቲትዩት መስርቶ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦችን ባህል፣ወግ፣ ቋንቋ በምሁራን እንዲጠኑ ያደርግ ነበር። ኢህአዲግ ብሔር ብሔረሰቦች በዓመት አንዴ ሞቅ ያለ ዘፈን እየከፈተ በቲቪ እንዲደንሱ በማድረግ እና አብዝቶ ስለነሱ በማውራት ደርግን አስንቆታል።
ደርግ የድሀውን ሕዝብ የኑሮ ችግር ለመደገፍ በእየቀበሌው ከክብሪት ጀምሮ እሰክ ኩንታል ጤፍ እና የተማሪዎች ደብተር ሳይቀር በቅናሽ ዋጋ እንዲዳረስ ያደርግ ነበር። ኢህአዲግ በዘመኑ የኑሮ ውድነቱ ጣርያ ደርሶም እራሱ ”ኑሮ ተወደደ” ብሎ መናገር የሚያሳስር መሆኑን በተግባር አሳየ።(ባለፈው ሰሞን ኑሮ ከበደን ያሉ ሴቶች የደረሰባቸውን ማሰብ በቂ ነው)
ደርግ አንድ ሰው ከቦታ ወደ ቦታ ሲሄድ ስሙ እና ፎቶው ያለበት መታወቅያ እንዲይዝ ያስገድድ ነበር። ኢህአዲግ ግን ስምና ፎቶ ብቻ ሳይሆን ‘ብሔር’ የሚል ጨምሮ ሕዝቡን ለያየው።
ደርግ አዋጅ ሲያወጣ አዋጁን ለምሳሌ የሰዓት እላፊ፣የመሰብሰብ ነፃነት ወዘተ ሲያግድ በራድዮ እና በቲቪ እንዲነገር ለጋዜጠኞች ይሰጥ ነበር።ኢህአዲግ እራሳቸው አቶ መለስ ”ከዛሬ ጀምሮ ከቤት ውጭ የሚደረግ ስብሰባ ተቃውሞ በሕግ ተከለክሏል” ብለው ሲናገሩ አሰማን።(ግንቦት 7/1997 ዓም አቶ መለስ በምርጫ ሲሸነፉ ያወጁትን አዋጅ አስታውሱ)።
ደርግ የኢትዮጵያ ዳር ድንበርን ሳያስደፍር ሲጠብቅ ኖረ።ኢህአዲግ ከባህር በር እስከ ኢትዮ-ሱዳን ድንበር ድረስ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሰጠ።Eprdf
ደርግ ሕዝብ ሁሉ ማንበብ እና መፃፍ መቻል አለበት ብሎ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ጀመረ። ኢህአዲግ ሕዝብ ሁሉ እስከ ቤተሰብ ወርዶ አንድ ለ አምስት መጠርነፍ (እንደ እርሱ አጠራር መደራጀት) አለበት ብሎ አንዱ ሌላውን እንዲሰልል አደረገ።
ደርግ ባለስልጣናቱ ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ ብዙዎቹ ባለስልጣናት እና የጦር መሪዎች በመንግስት ቤት ውስጥ እንዲኖሩ አደረገ። ኢህአዲግ ባለስልጣናቱ ሁለት እና ሶስት ቪላ እና መኪና እንደ ግምሩክ ባለሥልጣኑ ያሉት ደግሞ አልጋቸው ስር  ’የፎረክስ’ ቢሮ እስኪመስል ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ የውጭ ምንዛሪዎች የሚይዙ ሆኑ።
ደርግ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁትን በሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ሥራ ይቀጥር ነበር። ኢህአዲግ ዩንቨርስቲ የጨረሱ ተማሪዎችን ሲመርቅ ገና ከዩንቨርስቲ እያሉ የስነ ልቦና ዘመቻ ይከፍትባቸዋል።ከምረቃ በኃላ ኮብል ስቶን እንደሚሰሩ ያረዳቸዋል። (አቶ ጁነዲን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነው ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተመራቂዎች የተናገሩትን እናስታውስ)።
ደርግ መብራት፣ውሃ እና ስልክ ከመቋረጡ በፊት በራድዮ እና በቲቪ ለምን፣መቼ እና ለምን ያህል ሰዓት እንደሚቋረጥ ይገልፅና ደንበኞቹን ከባድ ይቅርታ ይጠይቅ ነበር። ኢህአዲግ መብራት እና ውሃ ለሰዓታት አይደለም ለቀናት  ሲቆም ይቅርታ ሲያልፍም አይነካው። ለምሳሌ አዲስ አበባ አንድ ሚልዮን ህዝቧ ውሃ አለመኖሩ ብዙ አስጊ የሚባል አለመሆኑን የገለፁት የኢህአዲግ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።”ውሃ የማያገኘው ሕዝብ 25% ብቻ ነው” ነበር ያሉት አቶ ኃይለማርያም ለጋዜጠኞች ሲመልሱ።
ደርግ ሕዝብ በግዳጅ ሰልፍ እንዲወጣ ያደርግ ነበር። ኢህአዲግ ሕዝብ ከኖረበት ቦታ ተባሮ እንዲወጣ በባለስልጣናቱ ሲደረግ እንዳለየ ለመምሰል እንደ አቶ መለስ ስለምፈናቀሉት ወገኖች ሲጠየቁ ደግሞ ነዋሬውን ”ድሮም ሞፈር ሰበር ነው” ሲሉ ተናገሩ። (እዚህ ላይ ከጉርዳ ፈርዳ፣ ሐረር ጋምቤላ እና ሌሎች ቦታዎች የተፈናቀሉትን አስቡ።)
እንዲህ እንዲህ እያልን ደርግ ተመልሶ በከፋ አገዛዙ መመለሱን እና በአንዳንዶቹማ ይብሱን ደርግ የተሻለባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።
ይሻል መጣ ብዬ ምርኩዝ አስጨበጨ መንገድ ያሳየሁት፣
ለካ ሌላም አይደል ደርጉን ኖሯል እና  ’ኢህአዲግ’ ነው ያልኩት።

0 comments:

Post a Comment