Monday 29 August 2016

ጎጃም ተቃውሞው ቀጥሏል – ቻግኒ ሕዝቡ መንገድ ዘግቶ አጋዚን አላሳልፍ ብሏል | የጎጃምና ጎንደር ሕዝብ በየቦታው የጎበዝ አለቆችን እየመረጠ ነው

የጎጃም ቻግኒ ሕዝብ የአማራው ሕዝብ እያደረገው ያለውን ከፍተኛ ሕዝባዊ ተጋድሎ ተቀላቀለ:: ከቻግኒ በተጨማሪ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በመሸንቲ፣ በመራዊ፣ ዳንግላና ሌሎችም ከተሞች እየተቀጣጠለ መሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል::

ከተማዋ በፌደራል ፖሊሶች ብትወረርም; የአጋዚና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ቻግኒ ከተማ እየገቡ ቢሆንም ሕዝቡ በድንጋይ እና በ እንጨት መንገዶችን በመዘጋጋት እንደተፋጠጣቸው ለመረዳት ተችሏል:: የቻግኒ ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ መንግስት አንመራም; የታሰሩት ይፈቱ; ወልቃይት የአማራ ነውና ሌሎችም ጥያቄዎችን እያሰማ ነው::

በሌላ በኩልም በተመሳሳይ በመሸንቲ; በመራዊና ዳንግላ ከተሞችም እንዲሁ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ከከፍተኛ ተቃውሞ ጋር ቀጥሏል:: በየከተማው ያለው ሕዝብ በሕወሓት መንግስት አንመራም እያለ ነው::

የትግራይ ነጻ አውጪው መንግስት የአጋዚና የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከሌሎች ክልሎች በማምጣት በጎጃምና በጎንደር ለማስፈር እየሞከረ ነው:: ሆኖም ሕዝቡ መንገዶችን እየዘጋጋ ላለማሳለፍ እየሞከረ ነው ተብሏል:: በጎጃም በርካታ የክክሉ ፖሊሶች ራሳቸውን እየሰወሩ ሲሆን ባለፉት 3 ቀናት ብቻ ከ30 በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት ትጥቃቸውን ለነዋሪዎች እየሰጡ መጥፋታቸውም በኢሳት ቲቭ ተዘግቧል::

ይህ በ እንዲህ እንዳለ ሕዝቡ በየቦታው የሚመሩትን የጎበዝ አለቆች እየመረጠ ነው:: አዴት ከተማ የጎበዝ አለቆችን መርጣ በነርሱ በኩል እየተመራች ሲሆን በቋሪትም በተመሳሳይ የጎበዝ አለቆች መመረጣቸው ይታወሳል:: በደቡብ ጎንደር አርብ ገበያም ሕዝብ ነገ ተሰብስቦ የጎበዝ አለቆችን እንደሚመርጥ መረጃዎች አመልክተዋል::



0 comments:

Post a Comment