እነ በቀለ ገርባ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል
‹‹ፍ/ቤቱ ገለልተኛ ነው ብዬ ስለማላምን ቃሌን አልሰጥም›› አቶ በቀለ ገርባ
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ አመራሮችና አባላት በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጉዳያቸውን ለሚያየው ችሎት ገልጸዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ነሐሴ 5/2008 ዓ.ም መዝገቡን የቀጠረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ ችሎቱ ተከሳሾችን አንድ በአንድ በስማቸው እየጠራ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳ አያኖ የቀረበባቸውን ክስ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም ተብለው ሲጠየቁ፣ ‹‹ይሄ ክስ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ በመቃወሚያ ላይ ይህን ገልጫለሁ፡፡ እኔ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚታገል ፓርቲ አባል ሆኜ ስታገል የኦነግ አባል ሆነሃል ተብዬ መከሰስ የለብኝም፡፡ ይህ የምታገልለትን ህዝብ እንደመወንጀል ይቆጠራል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ አሸባሪ ከተባለ እኔም አሸባሪ ነኝ፡፡ ይህ በደል ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እዚህ ቆሜ ቃሌን መስጠት አያስፈልገኝም›› በማለት ተናግረዋል፡፡
2ኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ‹‹እኔ የምታገልለት ህዝብ በመንግስት ጦር እያለቀ ባለበት ሰዓት እኔ እዚህ ቆሜ ቃሌን መስጠት አልፈልግም፡፡ ይህ ፍ/ቤትም ህገ-መንግስቱን የጣሰ ውሳኔ ስላሳለፈብኝ ለዚህ ፍ/ቤት ቃሌን መስጠት ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ድጋሜ እዚህ ፍርድ ቤት መቅረብም አልፈልግም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ አዲሱ ቡላላም በተመሳሳይ ቃላቸውን ለመስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የደረሰን በክስ መልክ የቀረበ ድረሰት ግልጽ አይደለም፡፡ በባህላችን ውሻ እንኳ ዝም ተብሎ አይነካም፡፡ ከተነካም ባለቤቱን መናቅ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ ለኦሮሞ ህዝብ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እታገላለሁ፡፡ የተሰጠኝ ድርሰት ግን የኦነግ አባል ሆነሃል የሚል ነው፡፡ እኔ የኦፌኮ አባል እንጂ የኦነግ አባል አይደለሁም፡፡ ስለዚህ በፍ/ቤቱ ወንጀሉን ፈጽመሃል አልፈጸምህም ተብዬ ስጠየቅ ያሳፍረኛል፡፡ ከዚህ በኋላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር እዚህ ችሎት መቅረብ አልፈልግም፡፡ ውሳኔያችሁን ልትልኩልኝ ትችላላችሁ›› በማለት ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡
የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ታደለ ተገኝ ተከሳሾቹ በአጭሩ ድርጊቱን ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው ብቻ መልስ እንዲሰጡ፣ ሌላ ረጂም ንግግር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡
ከማሳሰቢያው በኋላ፣ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት የኦፌኮ ም/ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ፣ ‹‹በክስ መቃወሚያችን ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለበት ቦታ እንዳኝ ብለን ጠይቀን ይህ ችሎት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ጥያቄያችን ህገ-መንግስታዊ ነበር፡፡ ግን አልተቀበላችሁትም፡፡ ስለዚህ ይህ ፍ/ቤት ገለልተኛ ነው ብዬ ስለማላስብ ቃሌን ለመስጠት አልፈልግም፡፡ ካሁን በፊትም የሀሰት ማስረጃ ቀርቦብኝ ስምንት አመት ፈርዶብኛል፡፡ የዚህንም ውሳኔ ባለሁበት ልትልኩልኝ ትችላላችሁ›› ብለዋል፡፡
ከ5ኛ ተከሳሽ ጀምሮ እንዲሁ በተመሳሳይ ቃላቸውን እንዲሰጡ እየተጠየቁ በአብዛኛው ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተከሳሾች መካከል 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ብቻ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም›› የሚል ቀጥተኛ የክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ 13ኛ ተከሳሽ በበኩሉ የዝምታ ምላሽን ሰጥቷል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ ‹‹ክሱ ንቀትና ጥላቻ የታጨቀበት ስለሆነ መልስ አልሰጥም›› ሲል ቀሪዎቹ ክሱ ግልጽ አይደለም፣ ፍርድ ቤቱም ገለልተኛ ነው ብለን አናምንም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር 11ኛ እና 19ኛ ተከሳሾችን ‹‹በስራ ጫና ምክንያት ቆጥረን አረጋግጠን ማቅረብ አልቻልንም›› የሚል መልስ በሰጠበት ምክንያት ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ ይህን በተመለከተ ጠበቃቸው በሰጡት አስተያየት ደበኞቻቸው ላይ የደህንት ስጋት ተጋርጦባቸው ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው ፍ/ቤቱ ይህንኑ ስጋታቸውን እንዲመዘግብላቸው አሳስበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ አስተዳደሩ በነገው ዕለት እንዲያቀርባቸው በማዘዝ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል ቀጠሮ ይዟል፡፡
ፍ/ቤቱ ዛሬ የቀረቡት ተከሳሾች ቃላቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ከመዘገበ በኋላ ‹‹ወንጀሉን አልፈጸምንም›› እንዳሉ ተቆጥሮ ክደው እንደተከራከሩ በመመዝገብ ያለ አቃቤ ህግ አሳሳቢነት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በሚል ከህዳር 02-16/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ የሰው ምስክሮች በርካታ በመሆናቸው ተከታታይ የቀጠሮ ቀናትን መስጠቱን ገልጹዋል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ተከሳሾቹ ዳኞች ወደ ችሎት ሲገቡም ሆነ ችሎቱ ጉዳያቸውን ሲያይ በችሎቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ ከመቀመጫቸው ሳይነሱ ቀርተዋል፡፡
0 comments:
Post a Comment