Friday, 5 August 2016

እነ በቀለ ገርባ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተድርጓል


*‹‹ይህ ህገ መንግስት በሦስት ዳኞች ውሳኔ አይፈርስም፤ ህገ መንግስቱ የኔም ነው፡፡ የመጠበቅ ኃላፊነት አለብኝ›› በቀለ ገርባ

በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገው የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተድርጓል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሐምሌ 29/2008 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የዋለው ችሎት ተከሳሾቹ ግንቦት 26/2008 ዓ.ም ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የተሰጠውን ብይን በንባብ ያሰማ ሲሆን፣ መቃወሚያቸው ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ሆኗል፡፡

ተከሳሾቹ በመቃወሚያቸው ተፈጸመ የተባለው ወንጀል የተፈጸመው ኦሮሚያ ክልል በመሆኑ ጉዳያቸው በኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት መታየት ይገባዋል በሚል የሥረ ነገር የዳኝነት ስልጣንን (Judicial jurisdiction) በተመለከተ ያቀረቡትን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ የጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 31 የሽብር ክሶችን የማየት ስልጣን የፌደራሉ ፍ/ቤት መሆኑን እንደሚደነግግ በመጥቀስ መቃወሚያቸው ውድቅ መደረጉን በብይኑ ላይ አመልከቷል፡፡

የቀረበባቸው ክስ የክስ አቀራረብ ደረጃን ያላሟላና ግልጽነት የሌለው መሆኑን በሚመለከት ላቀረቡት አቤቱታ ፍ/ቤቱ ክሱ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀቱን ገልጾ የተከሳሾች የወንጀል ተሳትፎ ደረጃን በተመለከተ ግን በማስረጃ መስማት ወቅት የምናየው ይሆናል በማለት ፍርድ ቤቱ መቃወሚያቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

መንግስት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከመልካም አስተዳደር ችግር የመነጨ መሆኑን አምኖ ይቅርታ የጠየቀበት ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ምክንያት እኛን በወንጀል የሚያስጠይቀን የህግ አግባብ የለም በሚል በተከሳሾች የቀረበውን መቃወሚያም ‹‹…ንብረት ማውደምና የሰው ህይወት ማጥፋት…››ን ጠቅሶ አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ በህግ መታየት እንዳለበት ፍ/ቤቱ መገንዘቡን ጠቅሶ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ፍ/ቤቱ ሌሎች የተከሳሾች መቃወሚያዎችንም እንዳልተቀበላቸው በብይኑ ላይ ገልጹዋል፡፡

ተከሳሾች ብይኑን ተከትሎ ያሰሙት ተቃውሞ

ተከሳሾች በፍርድ ቤቱ የተሰጠው ብይን በንባብ ከተሰማ በኋላ ሀሳባቸውን ለመግለጽ እጃቸውን በማውጣት ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱ በበኩሉ ‹‹ጊዜ የለንም፣ አሁን ልንሰማችሁ አንችልም›› በማለት የተከሳሾችን አቤቱታ ሊያልፈው ሞክሯል፡፡ ሆኖም አቶ በቀለ ገርባ ከተቀመጡበት በመነሳት ‹‹ዜጎች ነን፣ በትልቅ ወንጀል ተከሰናል፡፡ አድበስብሶ ማለፍ አይቻልም፡፡ ፍርድ ቤቱ በግልጽ ሀሳባችንን እንድንናገር ካልፈቀደ ማን ሊፈቅድልን ነው? ስለሆነም እንናገር ስሙን፡፡ የማትሰሙን ከሆነ ግን ውሳኔያችሁን እዚያው እስር ቤት ልትልኩልን ሲገባ እዚህ መቅረባችን ትርጉም የለውም›› በማለት ማሳሰባቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ አቶ በቀለ እንዲናገሩ ለመፍቀድ ተገድዷል፡፡

በዚህም አቶ በቀለ ገርባ ፍ/ቤቱ በሰጠው ብይን ላይ በተለይ የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ ጥያቄ አዘል ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
‹‹ህገ መንግስቱ የፌደራል ፍ/ቤት በክልልም ማቋቋም አለበት ይላል፡፡ አሁን የተሰጠው ውሳኔ ግን ይህን ያልተገነዘበ ነው፡፡ ይሄ ህገ መንግስት በሦስት ዳኞች ውሳኔ ሊፈርስ አይችልም፡፡ ህገ መንግስቱ የእኔም ነው፤ የመጠበቅ ኃላፊነት አለብኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉም እንዲጠብቀው አደራ እላለሁ፡፡

በህገ መንግስቱ መሰረት በክልል በቋቋም የነበረባቸው የፌደራል ፍ/ቤቶች አልተቋቋሙም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የክልል ፍ/ቤቶች በውክልና ሊዳኙ በተገባ ነበር፤ ይህ አልሆነም፡፡ እናም ይህ የክልሎችን ስልጣን መሻር ነው፡፡ የዛሬውን ውሳኔያችሁን ኤርትራን ከፌደረሽኑ ለመገንጠል ከተደረገው ውሳኔ ታሪክ ጋር ነው የማገናኘው፡፡ ይህ ህገ መንግስት በብዙዎች ደም ነው የተጻፈው›› በማለት በእጃቸው የያዙትን ህገ መንግስት ወደ ዳኞች እያሳዩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ‹‹ውሳኔው ክልሎች ያገኙትን ስልጣን የነጠቀ ነው፡፡ እኛ የምንታገለው ህግን ለማስከበር ነው፡፡ ለዚህም የኦሮሞ ህዝብ ከጎናችን እንዲሆን ጥሪ አስተላልፋለሁ›› ብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰብሳቢ ዳኛው አቶ ታደለ ተገኝ ‹‹እኛ አቤቱታ ነው የምንሰማው፡፡ መልዕክት ማስተላለፍ አይቻልም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይህን የዳኛውን ንግግር ተከትሎም አቶ በቀለ ገርባ ‹‹የሰጣችሁት ውሳኔኮ ፖለቲካዊ ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ሌሎችም ተከሳሾች አቤቱታና ጥያቄዎች እንዳሉዋቸው ቢገልጹም ፍ/ቤቱ ጊዜ የለንም በሚል ለማስተናገድ ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ በሌላ በኩል ግን ችሎቱ መሰየም ከነበረበት ሰዓት እጅግ ዘግይቶ ከቀኑ 9፡30 ነው የተሰየመው፡፡ በዚህም ዳኛው ጊዜ የለንም ሲሉ ተከሳሾች ዳኞች ራሳቸው ዘግይተው መሰየማቸውን አስታውሰዋቸዋል፡፡

ፍ/ቤቱ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለነሐሴ 5/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተጠናቅቋል፡፡ የችሎቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ተከሳሾች በህብረት የተቃውሞ መዝሙር በኦሮምኛ አሰምተዋል፡፡ ‹‹ህዝባችን እየሞተ፣ እየተበደለ እንዴት ዝም እንላለን…እንታገላለን እንጂ ዝም አንልም…›› የሚል ይዘት ያለው የተቃውሞ መዝሙሩን ከችሎት ወጥተው መኪና ውስጥ እስኪገቡ ድረስ ሲዘምሩት ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት

0 comments:

Post a Comment