Tuesday, 9 August 2016

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየተፈጸመ ያለን ግድያ በመቃወም ሰልፍ አደረጉ

ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆነ ኢትዮጵያውያን በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየተፈጸመ ያለን ግድያ በመቃወም ዛሬ ማክሰኞ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
እየተፈጸመ ያለውን ግድያና እስራት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ጥያቄን ሲያቀርቡ ያረፈዱት ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ መንግስት ከአምባገነን መንግስታት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆም አሳስበዋል።

የአሜሪካ መንግስት በየአመቱ በኢትዮጵያ ስለሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርትን ቢያወጣም የወሰደው እርምጃ የለም በማለት ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያላቸውን ቅሬታ አቅርበዋል።
ግድያ ይብቃ” “የዜጎች መብት ይከበር” “ወልቃይት ጎንደር ነውየሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ መንግስት ህጻናትና ሴት እናቶችን የሚገድል መንግስት ከመደገፍ እንዲታቀብ ጠይቀዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ ከተማና ዙሪያ በሚንቀሳቀሰው ግብረ ሃይል በተጠራው በዚሁ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የታደሙ ሰልፈኞች በሃገሪቱ በመፈጸም ላይ ያለው ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎችን በፎቶና በምስል በማስደገፍ አቅርበዋል።
የአሜሪካ መንግስት በሽብር ተግባር ላይ ከተሰማራ መንግስት ጎን መቆሙም በማብቃት ከህዝቡ ጎን እንዲቆም ሲሉ የሰልፉ አስተባባሪዎች ለአሜሪካ ባለስልጣናት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የሰልፉ ታዳሚዎች ሲያሰሙ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉ ባለስልጣን ከአስተባባሪዎቹ የቀረበን ጥያቄ በአካል በመገኘት ተቀብለዋል።

ከባለስልጣኑ ጥያቄያቸውን ያቀረቡ የግብረ ሃይሉ አባላት አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትኩረት እንድትሰጥና አምባገነን ያሉትን መንግስት ከመደገፍ እንድትታቀብ አሳስበዋል።
ርካታ ኢትዮጵያውያን በተሳተፉበት በዚሁ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ሰልፈኞች በተደጋጋሚ ለሚፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግስት ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ተናግረዋል።



0 comments:

Post a Comment