Thursday, 18 August 2016

የትግሬ-ወያኔ የዐማራ እና የኦሮሞ ነገዶችን ሕዝብ ጨርሶ ለማጥፋት ያቀደው ሚስጢራዊ አዲስሤራ – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

ማክሰኞ ነሐሴ ፲ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. ቅፅ ፬ ፣ ቁጥር ፳፪


ላለፉት 25 ዓመታት የትግሬ-ወያኔ በሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍና በደል ከመጠን በላይ በመሆኑ፣ ሕዝቡን ለእምቢተኝነት አነሳስቷል። ይህ ግፍና በደል መጠን የለሽ በመሆኑ፣ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ በተለይም በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ በወሎ፣ በሐረርጌ፣ በአርሲና በወለጋ ክፍለ-ሀገሮች የሚኖረው ሕዝብ፣ የትግሬ-ወያኔ “ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዕኩልነት» ሲል “አመጣሁት» ያለውን “ሕገ-መንግሥት» የማይቀበለው መሆኑንና፣ የዚሁ “ሕገ-መንግሥት» ተብየ መገለጫ የሆነውን ሠንደቅ ከተሰቀለበት በማውረድ፣ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ፣ የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ሠንደቅ ከፍ-ብላ እንድትውለበልብ እያደረገ መሆኑ በግልጽ ተስተውሏል። ይህም የትግሬ-ወያኔ አመጣሁት ያለው ዕኩልነትና የነገዶች አንድነት ውሸት መሆኑን፣ ባንፃሩ ግን የትግሬ-ወያኔ የውስጥ ቅኝ ገዥ ኃይል እንደሆነ፣ በተከታታይ በተደረጉት የሕዝባዊ እንቢተኝነት ሰላማዊ ሰልፎች በግልጽ ታይቷል።

ይህ የሕዝብ አመጽ ያርበደበደው የትግሬ-ወያኔ ቡድን፣ የሚይዝ የሚጨብጠውን በማጣቱ፣ የእርሱ ምርኮኛ የሆነውንና በጥቅማጥቅም የገዛውን የትግራይ ትውልድ በነቂስ አስታጥቆ፣ በዐማራና በኦሮሞ ነገዶች ሕዝብ ላይ ለመዝመት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስተማማኝ ከሆኑ የውስጥ ምንጮቻችን ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። የትግሬ-ወያኔ ከሚያደርገው ሠፊ የጥፋት ዝግጅቶች ውስጥ፣ የትግራይን ትውልድ “በትግልህ ያገኘኸውን ልዩ መብትና ነፃነት፣ ትምክተኞች፣ ነፍጠኞች፣ የድሮው ሥርዓት አራማጆችና ዐማሮች ሊነጥቁህ ነውና ዐማራን ለማጥፋት ዝመት፣ ተንቀሳቀስ» በማለት፣ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በጠለምት፣ በአርማጭሆ ነዋሪዎች ላይ ክተት አውጇል። በአጠቃላይም በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋና በወሎ የዐማራ ነገድ ሕዝብ ላይ መጠነ ሠፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም ዝግጅቱን አጠናቋል። በመሆኑም ሰሞኑን በጎጃምና በጎንደር የተለያዩ ከተሞችና ገጠሮች ቅጥር የነፍሰ ገዳይ ቡድኖችን በማሰማራት ሌሊት ሌሊት ወጣቱን እየፈነ ወደ ማሰቃያ እስር ቤቶቹ እያስገባ መሆኑ ታውቋል።

ይህ ድርጊቱ ፍላጎቱን ሙሉ በሙሉ ሊሳካለት እንደማይችል በመረዳት፣ በመላ ኢትዮጵያ የሚያካሂደው ሌላም ሠፊ የጥፋት ዕቅድ አቅዶ ለተግባራዊነቱ በጥድፊያ እየሠራ መሆኑ እየተሰማ ነው። ይህም መጠነ ሠፊ የሆነ ጥፋት ያነጣጠረው በዐማራና በኦሮሞ ነገዶች ሕዝብ ላይ እንደሆነ ታውቋል። የትግሬ-ወያኔ በእነዚህ ነገዶች ሕዝብ ላይ የጥፋት ተልዕኮውን ለመወጣት ያቀደው ዕቅድ፣ “በዐረብ ኢሚሪቶችና በሻዕቢያ የሚታገዙ አሸባሪዎች፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ ነው» የሚለውን ሀሳብ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ፣ በተለይም ሽብርተኝነት ለመዋጋት በሚል ሸሪክ የሆነውን የምዕራቡን ዓለምና የአሜሪካንን ልብ ለማማለል እንደሆነ ይገመታል። በዚህ ረገድ በቅርብ ቀናት ውስጥ የትግሬ-ወያኔ በሐረር፣ በድሬደዋ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳርና መሰል ከተሞች፣ የሕዝብ ክምችት በሚበዛባቸው ቦታዎች፣ በመንግሥታዊ ተቋሞች፣ በመገናኛ አውታሮች ወዘተርፈ ፈንጅ በማፈንዳት እኩይ ዓላማውን በተግባር እንደሚያውል ውስጥ አዋቂዎች አስጠንቅቀዋል። ፈንጂዎችን ራሱ አፈንድቶ፣ “የዐማራ እና የኦሮሞ ጽንፈኞች እንዲህ አደረጉ» በማለት ለደጋፊዎቹ የተቀነባበረ የሤራ መረጃ በማቅረብ፣ “ሕገ-መንግሥት» ተብየውን አግዶ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ወታደራዊ አገዛዝ በማወጅ፣ በሁሉም ቦታዎች ለወያኔ ጄኔራሎች የመግደልና የማሰር ሥልጣን በመስጠት በዐማራውና በኦሮሞው ነገዶች ሕዝብ ላይ መጠነ ሠፊና አሰቃቂ ዕልቂት ለመፈጸም ቁርጠኛ አቋም መያዙ ታውቋል።

በሰኔ 1980 ዓ.ም. “ነፃ ላወጣህ መጣሁ» ባለውና በራሱ ነገድ በሆነው የሀውዜን ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ላይ ያን የመሰለ የተቀነባበረ ሤራ ሠርቶ ሕዝብ ያስጨረሰ ድርጅት፣ “ጠላቶቼ ናቸው» ባላቸው የዐማራና የኦሮሞ ነገድ ሕዝብ ላይ ይህን ዓይነቱን ድርጊት አያቅድም፣ አይፈጽምም፣ አያደርጉትም፣ አይሆንም የሚያሰኝ አመክንዮ አይኖርም። ኢትዮጵያዊ የሆኑትንና “ለትግሬ-ወያኔ ዓላማ አንገዝም፣ አባልም አንሆንም» ያሉትን የትግራይ ልጆች፣ “አባሎቼ ናቸው» የሚል የተቀነባበረ የሐሰት መረጃ፣ ለደርግ የመረጃ አካላት እያቀበለ ወገኖቹን ያስጨፈጨፈ ድርጅት ይህን አያስብም አይባልም። በሂደት እንዳስተዋልነው፣ ወያኔ “አደርገዋለሁ፣ አጠፋዋለሁ» ብሎ ያቀደውንና ያለው በተግባር ከመፈጸም ወደ ኋላ ያለበት አንድም አጋጣሚ አላየንም። ይህንም እኩይ ድርጊት አያደርገውም ለማለት የሚያስችል ምክንያት ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው።

የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን፣ ዐማራንና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን አጠፋለሁ ብሎ አቅዶ መነሳቱ ይታወቃል። በዕቅዱ መሠረትም 5 ሚሊዮን ዐማራ አጠፋ። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አመራርን ከሦሥት ከፈለ፥ የአገር ቤትና ስደተኛ ሲኖዶሶች እንዲሁም ገለልተኛ በሚል። የሃይማኖቱ ነባር ተቋሞችን፣ ለምሣሌ ያህል፥ የዋልድባን፣ የዝቋላ አቦን እና የማኅበረሥላሴን ገዳማትን አቃጠለ፤ ቅጥረ ግቢያቸውን መነጠረ። የሃይማኖት አባቶችን አሰደደ። ቱባ ባለሥልጣኖቹ ዐባይ ፀሐየ፤ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ሣሞራ የኑስ ሌሎችም በአደባባይ፣ “ዐማራና ኦርቶዶክሱን አከርካሪውን ሰብረነዋል፣» “ገድለን ቀብረነዋል» ማለታቸውን አንዘነጋም። እናም ባለፉት 25 ዓመታት ገድለው ካልጨረሱት ውስጥ የቀረውን የዐማራና የኦሮሞን ነገዶች ሕዝብ “አስቸኳይ ወታደራዊ» አገዛዝ በማወጅ ሊጨርሱት ቁርጥ ሀሳብ ማድረጋቸውን የዐማራውና የኦሮሞው ነገድ አባሎች ለአፍታም መጠራጠር አይኖርባቸውም። ስለሆነም፣ የትግሬ-ወያኔ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ጥፋት ተልዕኮው ሳይገባ፣ ዐማሮችና ኦሮሞዎች ዕቅዱን ለማክሸፍ መተባበር ይጠበቅባቸዋል።

ከሁሉም በላይ “ሺህ ጋን ቢታለብ ወይ በገሌ» እንዳለችው ድመት፣ ዐማራው በብሔርተኞቹ ድርጅቶች በቀና ስለማይታይ፣ ልጆቹ በመካከላቸው አለን የሚሏቸውን ጥቃቅን ልዩነቶች በማርገብ፣ በአንድነት በመቆም ለወገናችን መከታ መሆን ይጠበቅብናል። የዐማራው ምሁራንና ፖለቲካኞች በአንድነት መቆም፣ የአንድነት ኃይሉን ለተፈላጊው አጠቃላይ የኢትዮጵያውያን አንድነት ጽኑ መሠረት ስለሚሆን፣ የዐማራው ምሁራን በቅድሚያ የነገዳቸውን አንድነት ዕውን በማድረግ፣ በሌሎች አቻ ቡድኖችና ድርጅቶች ላይ መልካም ተጽዕኖ ማሳደር ይጠበቅባቸዋል። ይህን ለማድረግ ስበቦችን መደርደር አስፈላጊ አይደለም። በወገናችን አንገት ላይ ሳንጃ ተጥሏል፤ በግንባርና ደረቱ ላይ አፈሙዝ ተደግኗል። ስለዚህ ይህ ጊዜ አይሰጥምና በዐማራ ስም የተደራጃችሁ ድርጅቶች ከያላችሁበት “አለን» ብላችሁ በጋራ የምትሠሩበት መንገድ ካሁኑ ካልጀመራችሁ፣ ይህንም ለወገናችሁ በግልጽ ካላሳያችሁ፣ የጥፋቱ አካል እንጂ፣ የመፍትሔው አካል ናችሁ ብሎ ማኅበረሰቡም ሆነ ታሪክ ሊያወሳችሁ እንደማይችል በእርግጠኝነት መናገር ድፍረት አይሆንም። ስለሆነም ሁላችንም ለዐማራው ኅብረትና አንድነት ኅሊናችን ከፍተን በቅንነት እንነሳ! በዚህ የመከራ ጊዜ የዐማራው ልሂቅ በአንድነት ቆሞ፣ ለወገኖቹ ቤዛ ካልሆነ ምንጊዜም ዐማራው አንድ ይሆናል ለማለት ያስቸግራል። እንኳን የአንድ ታላቅና ታሪካዊ ነገድ ልጆች ቀርቶ፣ በክረምት እባብና ጓጉንቼር በአንድ ጉድጓድ ይኖራሉ። ይህ ክፉ የወያኔ ዘመን ዐማራውን ቀርቶ፣ ዐማራና ኦሮሞውን በአንድ ካላሰላለፈ የኢትዮጵያ አንድነት ርቆ የተሰቀለ ባዶ ተስፋ ከመሆን አያልፍም።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ዐማራነት ነፃነት፣ ዕኩልነት አንድነት ነው!
ኢትዮጵያ በቆራጥና ጀግና ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

0 comments:

Post a Comment