Monday 12 August 2013

የተባረኩ እግሮች

የተባረኩ እግሮች


ዳንኤል ክብረት

የሀገርን ክብር ከፍ የሚያደርጉ፣ ጽናትንና ብርታትን የሚሰብኩ፣ አልበገር ባይነትንና ተጋድሎን የሚያውጁ፣ ለዓላማ ቁርጠኝነትንና ትጋትን የሚናኙ የተባረኩ እግሮች፡፡ ምን ነበር ይሆን የምታስቢው እንዲያ ተከበሽ ስትሮጭ፣ ምን ነበር ይሆን የምታልሚው እንዲያ ሀገርሽ አንድ ወርቅ እንኳን አጥታ ስሟ ከሠንጠረዡ ሲጠፋ፤ ምን ነበር ይሆን የምታስቢው የእነ አበበና የነ ማሞ፣ የነ ምሩጽና የነኃሌሌ፣ የነ ቀነኒሳና የነ ገዛኸኝ ታሪክ ወደ ተረትነት ሲለወጥ፤ ተንታኙ ሁሉ እንዲህ ነበሩኮ የሚለንን ስትሰሚ ምን ነበር ይሆን የምታስቢው፡፡
የሮጥሽውን እንጂ ያሰብሽውን አላየነውም፡፡ ያደረግሽውን እንጂ የወሰንሽውን አልተመለከትነውም፡፡ ወደየት ነበር የሮጥሽው? ምን ነበር ከፊት የሚታይሽ? አበበ ነው ወይስ ኃይሌ? ባንዲራሽ ነው ወይስ ሕዝብሽ? መቼም ምንመ ሳታይ እንዲያ አልተፈተለክሽም፡፡ ምንስ ነበር የምትሰሚው? መቼም የሞስኮን ሕዝብ ጩኸት አይደለም፡፡ በማያውቁት ቋንቋ የሚነገር ጩኸት ምች እንዲያ ያስሮጣልና፡፡ ሂጂ፣ ሂጂ፣ ሂጂ ጥሩነሽ ሩጭ፤ ታሪክ ተረት ሆኖ እንዳይቀር ለሀገርሽ ወርቁን አምጭ› ‹ሂጅ አብረንኅ እየሮጥን ነው፣ ብቻሽን ከቶ አይደለሽም፤ ምሩጽ ቀድሞ ሰባብሮታል፣ ይህ አየር ለኛ አዲስ አይደለም› የሚለው የሕዝብሽ ድምጽ ነበር በሹክሹክታ የተማሽው? አርምሞኮ ቋንቋ ነው በውስጥ ከነፍስ ጋር የሚያወሩት፡፡


እነዚያ እግሮችሽ እንደ ሲላ ሲወረወሩ፣ እንደ ንሥር ሲበርሩ፣ እንደ አቦ ሸማኔ ሲፈተለኩ፣ እንደ ሚግ ሲምዘገዘጉ፣ እጆችሽ እንደ መልአክ ክንፍ አየሩን ሲሰነጥቁ፣ ደረትሽ እንደ ሚሳይል እየከፈለው ሲተኮስ፤ እንደታቀፈች ሰጎን ዓይኖችሽ ምድር ምድር ሲያዩ፣ ከአየር ጋር ስትሟገች፣ ከድል ጋር ስትጠራሪ፣ ከእልክ ጋር ተወራርደሽ፣ ከእምቢ ጋር አብረሽ ስትሮጭ፤ ልብና እግሮችሽ ተስማምተው እየተማከሩ ሲነጉዱ፤ ዓይንና እጆችሽ ተፋቅረው የርቀት መጠን ሲለኩ፤ እንደ ንብ አውራ ታጅበሽ፣ እንደ ንብ ንግሥት ስትከንፊ፤ ምነ ነበር ያኔ የምታስቢው?
ሀገር ነበረች ከኋላሽ፣ ሀገር ነበረች ከፊትሽ፤ እንዳንች ማልያ አጥልቀን፣ እንዳንቺ ሞስኮ ባንጓዝ፤ እንዳንቺ ሀገር ወክለን እንዳንቺ በመም ላይ ባንከፍ፤ ልባችን ካንች ጋር ነበር፣ ሁሉንም ዙር አብሮ ዞሯል፤ ኅሊናችንም ካንቺ ጋር ለአምላክ ሥዕለቱን አቅርቧል፡፡ እንዴት ደስ ይላል መሰለሽ አገር አስከትሎ መሮጥ፤ እያባረርሽን አልነበረም፣ እየተከተልንሽ እንጂ፣ በእጅሽ መሣሪያ አልያዝሽም፤ ውርደትን ቀዘፍሽው እንጂ፡፡ ሀገርን ሊያኮራ የሚሮጥ፣ ድሮም ሕዝብ አብሮት ይሮጣል፣ እግሮቹ ብሩካን ናቸው ብሎ ከጥንቱ መርቆታል፡፡ በሞስኮ አፈር ላይ አይደለም በብሩካን እግሮችሽ የሮጥሽው፣ በሚወድሽና በሚሳሳልሽ ሕዝብ በልቡናቸው ውስጥ ነው፡፡

አብረንሽ ባንሮጥ ኑሮ ድል ስታደርጊ ለምን አብሮ ደስ አለን? ድል አደረግን ሲሉንኮ አብረናቸው ያልተደሰትን ብዙዎች አሉ፡፡ ድሉ የራሳቸው ብቻ የሆነ፤ ብቻቸውን ያሸነፉ፤ ድላቸውን ያልገዛንላቸው፡፡ አንዳንዶች ወርቅ ከሀገራቸው ሲያወጡ አንቺ ግን ወርቅ ወደ ሀገርሽ አመጣሽ፤ ስለዚህ አብረንሽ ሮጥን፡፡ አብረንሽም ስለሮጥን አብረንሽ ተደሰትን፡፡ ሞስኮ ላይ ያዩሽ ሁሉ፤ ምሩጽ አልሞተም አሉ፡፡ አረንጓዴው ጎርፍ ቢደርቅም አረንጓዴ ወርቅ አላቸው አሉ፡፡ ሁሉንም የሚግባባ ሃሳብና ፕሮግራም፣ አስተዳደርና አመራር፣ አካሄድና መዋቅር በጠፋበት ጊዜ ምሥራቅ ከምዕራብ ሰሜን ከደቡብ አስተባብረሻልና የመግባቢያ ሰነዳችን ሆነሻል፡፡ በየጎራው የቆሙትን፣ በየተቃራኒው የተሰለፉትን ሁሉንም ሞስኮ አምጥተሸ አንድ አድርገሻቸዋልና የአንድነት ዓርማ ሆነሻል፡፡ 
ማጭበርበር በሌለው ምርጫ ተመርጠሻል፤ የምረጡኝ ዘመቻ ሳያስፈልግሽ በተግባር ሕዝብ አሰልፈሻል፤ ዙፋን ሳያስፈልገሽ ነግሠሽ፣ ሉል ሳያስፈልግሽ ገዝተሻል፡፡ ስም ወደ ግብር ይመራልና ጥሩነሽ ጀግና ሆነሻል፡፡
እግሮችሽን አበርትቶ፣ ጣቶችሽን ያለምልማቸው፣ ኅሊናሽን አንቅቶ፣ ለዓይኖችሽ ብርሃን ይጨምርላቸው፤ የልብሽን ምት ጠብቆ እጆችሽን አክናፍ ያርጋቸው፤ ሳትደክሚ ምትክሽን፣ ሳታርፊ ደቀ መዝሙርሽን ያሳይሽ፡፡ ቀና እንዳደረግሽን ቀና በይ፣ እንዳከብርሽን ይክብርሽ፤ እንዳኮራሽን ያኩራሽ፤ እንዳደመቅሽን ያድምቅሽ፡፡ 

0 comments:

Post a Comment