Saturday 10 August 2013

ተደብድበንም ድል ያደረግነው እኛው ነን! (ድምፃችን ይሰማ)

August 10, 2013
የመንግስት አረመኔያዊ ተግባር በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየዳከረ መሆኑን ማሳያ ነው!
‹‹(ስትቆስሉ) የምትታመሙ ብትኾኑ እናንተ እንደምትታመሙ እነሱም ይታመማሉ፡፡ የማይከጅሉትንም ከአላህ ትከጅላላችሁ፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡›› (ቅ.ቁርአን 4፣104)
የድል መገለጫዎች በርካታ ናቸው፡፡ ድል ማለት አንድን ዓላማ አንግቦና ታግሎ ዓላማውን ማስፈጸም ብቻ አይደለም፡፡ ያመኑበትን ዓላማ ከባድ የሚባሉ መከራዎች ቢያጋጥሙ እንኳን በጽናት ይዞ መቆየት ታላቅ ድል ነው፡፡ ለሚታገሉለት ዓላማ መሞትም ታላቅ ድል ነው፡፡ ቁርአንም የሚስተምረን የድል ፅንሰ ሃሳብ ይኸው ነው፡፡ በሱረቱል አልቡሩጅ ውስጥ የተጠቀሰው ‹‹የጉድጓዶቹ ሰዎች›› ታሪክ ይህን የድል ፅንሰሃሳብ በደንብ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በየመን የነበረ አንድ ንጉስ ህዝቦቹ የጣኦት አምልኮን ትተው በአላህ አንድንት በማመናቸው ምክኒያት እጅጉን ተቆጥቶ ጉድጓድ እንዲቆፈርና ውስጡ እሳት እንዲቀጣጠል አዘዘ፡፡ ህዝቦቹንም ጉድጓዱ ፊት አሰልፎ ወደ ጣዖት አምልኮ እንዲመለሱ፤ የማይመለሱትን ደግሞ እሳቱ ውስጥ እንዲጣሉ አዘዘ፡፡ አማኞቹም ወደ ክህደት ፈጽሞ አንመለሰም በማለታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው በእሳት ተቃጠሉ፡፡ ቁርአን የነዚህን ሰዎች ታሪክ ከጨረሰ በኋላ አማኞቹ ድል ስለ ማድረጋቸው ይነግረናል፡፡Ethiopian Musilms
‹‹እነዚያ ምእመናንና ምእምናትን ያሰቃዩ፣ ከዚያም ያልተጸጸቱ ለእነርሱ የገሀነም ቅጣት አልላቸው፡፡ ለእነርሱም የመቃጠሉ ስቃይ አልላቸው፡፡ እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችንም የሠሩ ለእነርሱ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች አሏቸው፡፡ ይህ ታላቅ ማግኘት ነው፡፡›› (ቅ.ቁርአን 85፣10-11)
አዎ! እነዚህ አማኞች በእሳት ተቃጥለው ሞተውም ድል አድርገዋል፡፡ ያመኑለት መርህ ድል አድርጓል፡፡ ይህ ግፈኛ ንጉስ አካላዊ ጉዳት ቢያደርስባቸውም ውስጥ ያለው እምነታቸውን የሚቀይርበት አቅም ባለመግኘቱ ድል አድርገውታል፡፡ ትክክለኛውም ድል ይኸው ነው፡፡ ተሸነፉ የሚባለው ውስጣቸው ተሸንፎ ጣዖት አምላኪነት በግዴታ ቢቀበሉ ነበር፡፡ እኛ ኢትዮጲያውያን ሙስሊሞች መንግስት በሃይማኖታችን ውስጥ የሚያካሂደው ጣልቃ ገብነት ድንበር በማለፉ ምክንያት እንቅስቃሴችንን ስንጀምርና ተቃውሞአችነን ስናሰማ መንግስት የጀመረውን የግዳጅ ጠመቃ ለማክሸፍና መጅሊሳችንም ሙስሊሙ በሚመርጣቸው መሪዎች መተዳደር እንዳለበት ጽኑ እምነት ኖሮን ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ይዘን ስንነሳም የምንጋፈጠው አካል የተደራጀ የደህንነት ሃይል፣ በዘመናዊ ማሳቀያ ማሽኖች የተሞላ የምርመራ ማዕከላት፣ ርህራሄ የሌላቸው የፖሊስ ሃይሎች ያለውን መንግስትን መሆኑንና በሂደታችን ብዙ መከራዎች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ አምነን ነው፡፡
ኮሚቴዎቻችን መብትን የማስከበር ሂደት አልጋ በአልጋ የሆነ ጉዞ አለመሆኑንና ብዙ መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ሊሆን እንደሚችል ደጋግመው አስገንዝበውናል፡፡ በስከዛሬውም ሂደታችን ለያዝነው ዓላማ ስንል ሕይወታችንን፣ አካላችንንና ንብረታችንን ገብረናል፡፡ መንግስት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው የሃይል እርምጃዎች ፅናትንና ብርታትን ከመጨመር ውጪ ከዓላማችን ንቅንቅ አላደረገንም፡፡ ኮሚቴዎቻችን በማዕከላዊ ማሳቀያ ቤት ከሚደርስባቸው አሰቃቂ ቅጣት በተጨማሪ በርካታ የስነልቦና ጦርነት የተደረገባቸው ቢሆንም ከአቋማቸው ንቅንቅ አላሉም፡፡ ድል ማለት ይህ ነው፡፡ አካላቸው አረመኔ በሆኑ መርማሪዎች ቁጥጥር ስር ቢውልም ህሊናቸውንና እምነታቸውን ግን እንዲቆጣጠሩዋቸው ግን አልፈቀዱም፡፡ ከዚህ የበለጠ ድል ከቶ ከወዴት ይገኛል፡፡
በትላንትናው የዒድ አረመኔያዊ ጭፍጨፋም መንግስት ህዝበ ሙስሊሙ እያደረገው ያለውን ትግል ዱላን ፈርቶ እንዲያቆያም፣ በሃይማኖቱ ጉዳይ ገብቶ እንዳሻው ሲፈተፍትና መጅሊስም በማንም ይመራ በማን ‹‹እኔ ምን አገባኝ›› እንዲል ታልሞ የተፈጸ መሆኑ ጥርጣሬ የለንም፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ግን ከዚያ ሁሉ የዱላ ውርጅብኝ በኋላም ለዓላማው ላይ ጽናትን እንጂ ሌላ አልጨመረም፡፡ ትግሉን አጠናክሮ ለመቀጠል እልህን እንጂ ሌላ አልጨመረም፡፡ ድል ማለት ይህ ነው! የእኛ ሽንፈት ኢ-ፍትሃዊትን አይተን ዝም ያልን እለት ነው! የእኛ ውድቀት በተፈጥሮአዊና ሕገ መንግስታዊ መብታችን ላይ የሚፈጸመውን ደባ አይተን እዳላይ የሆንን እለት ነው! የእኛ ሽንፈት የሚባለው መንግስት በእምነታችን ጣልቃ ገብቶ እንዳሻው ሲጫወትና መጅሊሱም የካድሬ መፈንጫ ሆኖ ‹‹ምን አገባን›› የሚል ምላሽ የሰጠን እለት ነው፡፡ የእኛ ሽንፈት በእስር የሚሰቃዩ ኮሚቴዎቻችንን ‹‹ፈጣሪ ይድረስላቸው›› በሚል ብሂል እጃችንን አጣጥፈን የተቀመጥን እለት ነው፡፡ አረመኔዎች እኛን በዱላ በመደብደባቸው ድል አንዳደረጉ ከተሰማቸው ፈጽሞ ተሳስተዋል፡፡ እኛ ቀድሞውኑ ከጠገበ ፖሊስ ጋር ለመግጠም አይደለም ወደ ጎዳና የወጣነው፡፡ እኛ ወደ ጎዳና የወጣነው ለሰላም እንጂ መች ለጦርነት ሆነና፡፡ ስኬታችንና ውድቀታችንም ለዓላማችን ባለን ጽናት እንጂ በዱላ የሚለካም አይደለም፡፡
በትግል ሂደት ውስጥ ጉዳትን ማስተናገድ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው፡፡ ያለ መስዋዕትነት ስኬት የለም፡፡ አላህ በቅዱስ ቁርአኑ እንዳለው ‹‹(ስትቆስሉ) የምትታመሙ ብትኾኑ እናንተ እንደምትታመሙ እነሱም ይታመማሉ፡፡ የማይከጅሉትንም ከአላህ ትከጅላላችሁ፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡›› (ቅ.ቁርአን 4፣104)፡፡ አዎ! እኛ በእያንዳንዱ በምንከፍለው መስዋዕትነት የአላህን ምንዳ እንከጅላለን፡፡ በደለኞች ደግሞ በሚፈጽሙት ግፍ ልክ የፈጸሙት ግፍ ነገ ይዞ በሚመጣባቸው ጣጣ ይጨነቃሉ፡፡
የትላንትናው የዒድ ጥቃት መንግስት እንቅስቃሴያችንን ለማክሸፍ ያደረጋቸው የተለያዩ ሙከራዎች ሁሉ አንዱ አካል ነው፡፡ ይናንቱ ጸያፍ እርምጃ የከዚህ ቀደም ሙከራዎቹ ሁሉ እንደከሸፉበትና ተስፋ እንደቆረጠ የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአቶ ኩማ ደመቅሳ አፍ የሰማነው መንግስት የልማት ስራውን ትቶ በሙስሊሙ ጉዳይ የተጠመደበት ሴራ ሁሉ ከንቱ መቅረቱን በግላጭ ያሳየን ክስተት ነው፡፡ መንግስት የውጪ ጠላትን ሊመክትበት ያዘጋጀውን ሃይል የሚያስተዳድረው ሰላማዊና ያልታጠቀ ህዝብ ላይ ከተጠቀመ በእርግጥም ከስሯል፣ ከሽፏል፡፡
መልእክታችንን አሁን በእስር ላይ በሚገኘው የኮሚቴው አባል ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ንግግር እንቋጭ፡-
‹‹በተለያየ መልኩ ግፈኞች የሚያሰቃዩት አካላቸውን ለመጉዳት ሳይሆን ለሰው ልጅ እጅግ ወሳኝ የሆነውን ተስፋና ወኔ ለመስበር ነው። የነፃነት ስሜት ያላቸውን ሰዎች በዳይ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ እራስ ምታት ናቸው። ተስፋ እንዲቆርጡም ወኔ እንዲያጡም በቃልም በጉልበትም የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ጀግና ማለት እነዚህን የስነ ልቦና ጦርነቶች ተቋቁሞ ሊሰብሩት የፈለጉትን ስነ ልቦና በተስፋ ሞልቶ በፅናት የሚጓዝ ነው።››
አላሁ አክበር!

0 comments:

Post a Comment