Wednesday 14 August 2013

ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በጥብቅ ያወግዛል!

August 14, 2013
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)
(ዴሞክራሲያዊ/Democratic)
ነሃሴ ፯ ቀን ፪ ሺህ ፭ ዓ. ም
የአምባገነኖች ዋና መለያ ባህሪያቸው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችንም ሆነ የእኩልነትንና የፍትኅን ጥያቄዎች የሚያቀርቡ ንፁኃን ዜጎችን ማሳደድ፣ ማዋከብ፣ ማስፈራራት፣ ማሰር፣ መደብደብ፣ ማሰቃየትና መግደል ነው። ከራሳቸው ሃሳብ ጋር የማይስማሙትን ሁሉ በጠላትነት መፈረጅና ከማጥላላት ዘመቻ ጀምሮ ሕይወትን እስከማጥፋት ድረስ ያሉትን እርምጃዎች በዘፈቀደ መውሰድ ባህሪያቸው ነው። አምባገነኖች በተባበረ የሕዝብ ክንድ ከሥልጣናቸው እስካልተወገዱ ድረስና የአገዛዝ ዘመናቸው በረዘመ ቁጥር ለሕዝቡ ያላቸው ንቀትና ዕብሪታቸው እየጨመረ ይመጣና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሽብር መንዛታቸውን በሰፊው ይቀጥሉበታል። የዜጎችን መብቶችም ጨርሰው በመርገጥ አንዳችም የዴሞክራሲ ጭላንጭል እንዳይታይ ያደርጋሉ። ስለዜጎች ሕይወትም ሆነ መብቶች ማሰብና መጨነቅ ሲያልፍም አይነካቸው። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች በተለያዩ አገሮች የተከሰቱ ዓይነተኛና የአምባገነኖች መለያ ባህሪያቸው ነው።
በአገራችን በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለው አምባገነኑ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝም በዓለም ዙሪያ በተለያየ ዘመን ወደ ሥልጣን ከመጡት መሰል ፀረ-ሕዝብ መንግሥታት ቢብስ እንጂ በምንም መልኩ የተሻለ አይደለም። ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እጁን በንፁኃን ዜጎች ደም የታጠበው የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በምዕራብ አሩሲ በኮፈሌ ወረዳ በእስልምና ዕምነት ተከታይ ወገኖቻችን ላይ የፈጸመው የግድያ ወንጀል የገዥውን ቡድን አረመኔያዊነት ከማሳየቱም በላይ ሀገሪቷን ወደ አልተፈለገና ወደ አልታሰበ ሁከትና የብጥብጥ አቅጣጫ የሚመራት በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት እንዳለን እንገልጻለን። ሕጋዊ የአምልኮት ነፃነታቸው ያለምንም የአገዛዙ ጣልቃገብነት እንዲከበር የጠየቁ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያንን በጀምላ በሃይማኖት አክራሪነትና አሸባሪነት ወንጅሎ የግድያ ወንጀል ፈጽሞ፤ ለምዕራቡ ዓለም የፀረ-ሽብር ትግሉ አካል መስሎ ለመቅረብ የሚደረገው ጥረት ተራ ማጭበርበር ከመሆኑም በላይ ሀገራችንንና ሕዝቧን በተቀረው ዓለም በጥርጣሬ እንድትታይና ለጥቃት እንድጋለጥ የሚያደርጋት ትልቅ ብሄራዊ ወንጀል ነው።
ህወሓት/ኢህአዴግ ንፁኃን ዜጎችን ከማሰቃየት፣ ከማሰርና ከመግደል የታቀበበት ወቅት ከቶውንም የለም፤ አልታየም። ድብደባው፣ ማሰሩና ግድያው እየተፈጸመ ያለው በበርካታ ከተማዎችና አካባቢዎች ውስጥ ሲሆን የሰለባዎቹን ትክክለኛ ቁጥር ለጊዜው ማረጋገጥ ባይቻልም፣ እንደተጠቀሰው ድብደባና ግድያዎች፣ በግፍና በገፍ ወደ እሥር ቤት የማጎር እርምጃዎች ያልርኅራሄ ተፈጽመዋል፤ እየተፈጸሙም ነው። ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) ይህን በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን እስራት፣ እንግልትና ጭፍጨፋ በጥብቅ ያወግዛል፤ በዚህም የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን በምሬት ይገልጻል። ለሟቾቹ ቤተሰቦችም መፅናናቱን እንዲሰጣቸው ይመኛል። በአገራችን የተንሰራፋውን ፀረ-ዴሞክራሲ አገዛዝ ከሥልጣን ለማስወገድ ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) ትግሉን አጠንክሮ ለመታገል የገባውን ቃል ኪዳን አድሶ ዛሬም እንደ ትላንቱ ትግሉን አጠናክሮ ይታገላል።
ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) የተለያዩ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ድርጅቶች በጋራም ሆነ በተናጠል ለመብትና ለዴሞክራሲ የሚያደርጉትን ትግል እያደነቀና እየደገፈ፣ ትግሉ ግቡን እንዲመታም ምን ጊዜም ከጎናቸው የሚቆም መሆኑን አሁንም በድጋሜ ያረጋግጣል። በታሪክ እንደታየው አምባገነኖች ከሥልጣን የወረዱት በተደራጀና በተባበረ የሕዝብ ትግል እንጂ በገዛ ፈቃዳቸው ወይም በተናጠል በሚደረጉ ብትን ጥረቶች አይደለምና በዚህ አጋጣሚ ከኢሕአፓ ረዥም የትግል ታሪክና ተመክሮ በመነሳት በተናጠል እየተካሄዱ ያሉ ትግሎች ተቀናጅተው ቢታገሉ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያለውን ዕምነቱን እየገለጸና ለተባበረ የሕዝብ ትግል የድርሻውን እያበረከተ፤ ወደፊትም ደጋግሞ እንደገለጸው ሁሉ ዝግጁነቱን እነሆ ዛሬም ያረጋግጣል።
በሀገራችን የሕዝብን መብቶች የሚያስከብር ስኬታማ ለውጥ ሊመጣና ሰላምና ዴሞክራሲ ሊሰፍን የሚችለው በፅናት በመታገልና አስፈላጊውን ሁሉ መሥዋዕትነት በመክፈል ነው ብሎም ያምናል።
በሙስና የተጨማለቀው አምባገነኑ የህወሓት/ኢህአዴግ ገዥ ቡድን እስከዛሬ በተግባር እንዳሳየው የዜጎችም ሆነ አጠቃላይ የሰው ልጅ መብቶች ጉዳይ ምኑም አይደሉም። ለህወሓት/ኢህአዴግ ዴሞክራሲ ማለት ለአፈናና ለዘረፋ ለሚተባበራቸው የአገዛዙ ጀሌዎች እንጂ የሰፊው ሕዝብ ባለመብትነት ከቶውንም ታስቧቸው አያውቅም።
ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) በአገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ዜጎች ሁሉ በአገራቸው ላይ ሠርቶ የመኖር፣ በሰላም ውሎ የመግባትና በማንኛውም የሀገራችን ክፍል ተንቀሳቅሰው በመረጡት ሥፍራ የመኖር መብታቸው እንዲረጋገጥ፣ መሪዎቻቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመምረጥና የማይስማማቸውንም የመለወጥ መብታቸው ያለምንም ገደብ እንዲረጋገጥ ሀገራዊ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሎ ያምናል። ስለሆነም ማንኛውም በተቃዋሚነት የተሰለፈ ድርጅት ወይንም ለዴሞክራሲና ለፍትኅ የቆመ አገርወዳድ ሁሉ በአንድነት ተባብሮ መታገል ያለበት ወሳኙ ወቅት አሁን መሆኑን ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) በአንክሮ ለማስገንዘብ ይወዳል። አገራችን በአምባገነን ገዥዎች እየተገፋች ከገደል አፋፍ ላይ ደርሳለች፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ገደሉ ውስጥ እንዳይከታት ልንታደጋት የሚገባው ወቅቱ አሁን ነው።
አምባገነኖች በሕዝብ ትግል ይወገዳሉ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተባበረ ትግሉ ያቸንፋል!!

0 comments:

Post a Comment