Saturday, 31 August 2013

ችግራችን አለመነጋገራችን!

Abraha desta

ከተወሰኑ የኢትዮዽያ ፖለቲካ ተንታኞችና ጋዜጠኞች ጋር የመነጋገር ዕድል አጋጥሞኝ ነበር። እነኚህ ሰዎች በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት (ወይም ብዬ አስባለሁ) ከሀገር እንዲወጡ የተደረጉ ናቸው፤ ለምሳሌ መስፍን ነጋሽ (Mesfin Negash)።

ከነ መስፍን ጋር የኢትዮዽያ ፖለቲካ በተመለከተ ከጓደኞቼ ጋር ሁነን ሓሳብ ለሓሳብ ተለዋውጠናል። የነሱ የፖለቲካ ሓሳብና ትንታኔ ካዳመጥኩ በኋላ ግራ ገባኝ፤ ልዩነታችን ምን ላይ መሆኑ መለየት አቃተኛ። እነሱ (መስፍንና ሌሎቹ) የሚናገሩት ነገር የኔ ሓሳብ ነው (አብዛኛው የትግራይ ህዝብም የሚጋራው ይመስለኛል)።

በኋላ ግን አንድ ነገር ገባኝ፤ የተለያየ ቋንቋ የምንናገር፣ በተለያየ ባህል ያደግን ዜጎች ብንሆንም ሓሳባችንና የፖለቲካ አመለካከታችን ይመሳሰላል። ሓሳብችን በተለያየ ቋንቋ እንናገረዋለን፤ በተለያየ ባህል እንገልፀዋለን።

ግን አንግባባም። ተመሳሳይ ሓሳብ እያራመድን ለምን አንግባባም? አንድ በመሃከላችን ቁሞ የጋረደን ግንብ አለ። ይህ አደገኛ ግንብ እርስበርስ የመጠራጠር መንፈስ ነው። እርስበርሳችን አንተማመንም። ለምን አንተማመንም? ተመሳሳይ ሓሳብና አቋም እንዳለን አናውቅም። ለምን አናውቅም? ሓሳብ ለሓሳብ አልተለዋወጥንም። ለምን አልተለዋወጥንም? አልተነጋገርንም። ለምን አልተነጋገርንም? አልተገናኘንም። ለምን አልተገናኘንም? ተለያይተን ስለምናድግና ስለምንኖር፤ የየራሳችን ቋንቋና ባህል ይዘን።

ለምን ተለያየን? ብሄር መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ተከተልን። ለምን ብሄር መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ተከተልን? የፖለቲካ መሪዎቻችን ፈለጉት። ለምን ፈለጉት? ህዝቦችን ለመከፋፈል። ለምን መከፋፈል አስፈለገ? ለመግዛት። እንዴት? ህዝብ (በብሄር ወይ ሀይማኖት) ከተከፋፈለ ህብረት አይኖረውም። ህብረት ከሌለው አንድነት የለውም። አንድነት ከሌለው ጨቋኝ ስርዓት ከስልጣን ለማውረድ ዓቅም አይኖረውም። ህዝብ ዓቅም ከሌለው ገዢዎች እንደፈለጉት በስልጣን መቆየት ይችላሉ።

ጉርሻ አንድ፦
የተለያየ ቋንቋና ባህል ይዞ ማደግ በራሱ ችግር አይደለም። ችግሩ ያለው የራሳችን ባህልና እድገት ብቻ የምናውቅ ከሆነ የሌሎች ኢትዮዽያውያን ወገኖች ባህልና ቋንቋ ትክክለኛነትና ሙሉነት እንጠራጠራለን። ምክንያቱም በአንድ ባህል ብቻ ስናድግ የአስተሳሰብ አድማሳችንም በዛው ልክ ጠባብ ይሆናል። ስለሌሎች ሙሉ ግንዛቤ ከሌለን የራሳችን ብቻ ትክክል መስሎ ይታየናል። ሌሎችም እንዲሁ፤ ባስተዳደጋችን ምክንያት የምናይበት መነፅር ጠባሏ።

እንደዉጤቱም ወደ አላስፈላጊ ፍክክር እንገባለን። ፍክክሩ በፖለቲከኞች ፍላጎትና ቅስቀሳ መሰረት ፖለቲካዊ መልክ ይይዛል። ከዛ እንጋጫለን። ተበታትነን እንቀራለን።

(በትላልቅ ከተሞች የሚያድጉ ወጣቶች በገጠር ከሚያድጉ ወጣቶች የተሻለ የአንድነት መንፈስ የሚያንፀባርቁበት ምክንያት በከተሞች የብዙ የተለያዩ ህዝቦች ባህል እያዩና እየተገነዘቡ ስለሚያድጉ ነው።)

ጉርሻ ሁለት፦
ገዢዎች ህዝብን የሚከፋፍሉ ለራሳቸው የስልጣን ጥቅም ሲሉ ነው። ህዝብን የመከፋፈል ፖለቲካዊ ስትራተጂ ከኢህአዴግ በፊትም ሲሰራበት የነበረ ነው። ገዢዎች ሊያጠፉ ይችላሉ። ፖለቲከኞች ሲያጠፉም ሲያለሙም ራሳቸው እንጂ ህዝብን ሊወክሉ አይችሉም። እርግጥ ነው ፖለቲከኞች ለፖለቲካዊ ድጋፍ ሲባል የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል እንደሚወክሉ ሊለፍፉ ይችላሉ። ግን ትክክል አይደለም። አንድ ባለስልጣን ከሰረቀ መጠየቅ ያለበት ራሱ እንጂ ‘እወክለዋለሁ’ የሚለውን ህዝብ አይደለም።

ልብ እንበል፤ ህዝብ ከህዝብ ጋር ሲጣላ የሚጠቀሙት ገዢዎች ናቸው። ህዝቡ ደግሞ ተጎጂ። በስልጣን ፍክክር ምክንያት ፖለቲከኞች ሲጣሉ ህዝቡ በንቃት መከታተል ይኖርበታል። ምክንያቱም ‘ሁለት ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው’ ይባል የለ።

ግጭት ያለ ነው። ግጭት መቀነስ እንጂ ማስወገድ አንችልም። ምክንያቱም ተፈጥራዊ ባህሪያችን ነው። ነገር ግን ለጋራ ጥቅማችን ስንል ግጭትን ትተን መስማማትን እንምረጥ። ይህ ማድረግ የምንችለው ደግሞ በህዝቦች መካከል መግባባት እንዲኖር የመወያያ መድረክ በመክፈት ነው።

ችግራችን ተነጋግረን መግባባት አለመቻላችን ነው።

(ይቺ ‘ፀረሽብር ሕግ’ ደግሞ አስታወስኳት። ‘ተነጋገረ’ ብለው ደግሞ …. በሉ ሳቄ መጣ …! በቃ ቻው።)

0 comments:

Post a Comment