‹‹ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ጽፌያለሁ›› ዮናታን
በኦሮምያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀጠል ተንቀሳቅሰሃል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር
ክስ የቀረበበት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሰብዓዊ መብት አራማጅ አቶ ዮናታን ተስፋዬ
ግንቦት 15/2008 ዓ.ም ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ዛሬ ሰኔ 14/2008
ዓ.ም ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያና አቃቤ ህግ ግንቦት 25/2008 ዓ.ም የሰጠውን መልስ መርምሮ ብይኑን
ያሰማው ፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ
የተከሳሹን የእምነት ክህደት ቃል ተቀብሏል፡፡
አቶ ዮናታን የቀረበበት የሽብር ክስ ተሰርዞ በነጻ
እንዲሰናበት በክስ መቃወሚያው መጠየቁ ይታወሳል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ በተከሳሹ ለቀረበው መቃወሚያ መልስ ሰጥቷል፡፡
ግራ ቀኙን ፍርድ ቤቱ እንደመረመረው የገለጹት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ታረቀኝ አማረ የተሰጠውን ብይን በንባብ
አሰምተዋል፡፡
ተከሳሹ ‹‹….አመጽና ብጥብጥ ለማስቀጠልና ለማነሳሳት በፌስቡክ ድረ ገጽ ቀስቃሽ
ጽሁፎችን መጻፍ ድርጊት›› በተከሳሹ ላይ ከተጠቀሰው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 4 ጋር የተቀራረበ አለመሆኑን
የወ/መ/ሕግ/ሥ/ሥ/ቁ.112 ጠቅሶ፣ ከድንጋጌው ውጭ የቀረበና ‹‹የሽብርተኝነት ተግባር›› ስላለመሆኑ ያቀረበውን
መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ‹‹የተመለከተውን ድንጋጌ አያሟላም ያሟላል የሚለው በማስረጃ ምዘና የሚታይ ይሆናል›› በማለት
ውድቅ አድርጎታል፡፡
ተከሳሹ የቀረበበት አመጽና ብጥብጥ ‹‹….የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር….››
እንጂ የኦ.ነ.ግ ተግባር ያለመሆኑ የህግ ግምት ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበው መቃወሚያ ‹‹ክሱ
ተቃውሞውን ስለማስቀጠል በተመለከተ የቀረበ በመሆኑ መቃወሚያውን አልተቀበልነውም›› በሚል ፍ/ቤቱ ውድቅ
አድርጎታል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጽፎታል ተብሎ በማስረጃነት የቀረበው ጽሁፍና ፈጽሞታል ተብሎ
የቀረበበት ድርጊት የወንጀል ኃላፊነትን የማያስከትልና ህገ-መንግስታዊ ጥበቃ የተደረገለት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ
መብት መሆኑን በማስመልከት ክሱ እንዲሰረዝና በነጻ እንዲሰናበት ያቀረበውን ተቃውሞ ደግሞ ‹‹ህገ መንግስቱ አንቀጽ
29(6) ገደቦችንም ያስቀመጠ በመሆኑና አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ንብረት ማውደምን ጠቅሶ ያቀረበው ክስ የተሟላ
ስለሆነ በማስረጃ የሚታይ ይሆናል›› በማለት ተቃውሞውን ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
ተከሳሹ የቀረበበት ክስ
ግልጽ ያለመሆኑንና የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር ግልጽ አለመደረጉን በተመለከተ ላቀረበው መቃወሚያ በጸረ-ሽብር
አዋጁ ላይ የተመለከተውን የምስክሮች ደህንነት ጥበቃ በመጥቀስ ማስረጃ ዝርዝሩ (ምስክሮቹ) እንዲገለጹ የቀረበውን
መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ
አድርጓል፡፡ በዚህም ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን ለመስጠት ዝግጁ ስለመሆኑ ጠይቆ ተከሳሹ ቃሉን ለመስጠት ዝግጁ
መሆኑን ገልጾ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ አቶ ዮናታን የቀረበበት ክስ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸም
አለመፈጸሙና ጥፋተኛ ስለመሆን አለመሆኑ ተጠይቆ ‹‹ክሱ በቀረበበት መንገድ የተገለጸውን የሽብር ተግባር
አልፈጸምኩም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ግን ጽፌያለሁ፡፡ በመሆኑም የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፤
ጥፋተኛ አይደለሁም›› ብሏል፡፡
ተከሳሹ በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት አልፈጸምኩም በማለቱ አቃቤ
ህግ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙ እንዲታዘዝለት የጠየቀ ሲሆን፣ ተከሳሹ በበኩሉ ፌስቡክ ላይ ጽፏቸው ከኮምፒውተር
ሲገለበጡ አይቻለሁ የሚሉ የደረጃ ምስክሮች ከሆኑ ባልተካደ ጉዳይ ላይ ፍትህን ማጓተት እንዳይሆን ግንዛቤ ይያዝልኝ
ሲል ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክር የማሰማት መብቱ የእኔ ነው በማለት ምስክሮቹ እንዲሰሙለት አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቀርበው እንዲሰሙ ለሀምሌ 20/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሁለት ሳምንታት በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና ዛሬም ከጨለማ ክፍል እንደሚገኝ ጠቅሶ
አያያዙ እንዲሻሻልለት ማመልከቻ አስገብቷል፡፡ ተከሳሹ በማመልከቻው ላይ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ መፍትሄ እንዲበጅለት
ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ግን በተሰጠው ቀጠሮ (ሐምሌ 20/2008) ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት እናዝዛለን በማለት
አልፎታል፡፡
0 comments:
Post a Comment