ወደ ኤርትራ ያደረግነው ጉዞ የሃገር ወዳድነት መለኪያ እንጂ ወንጀል አይደለም ሲሉ እነብርሃኑ ተክለያሬድ ለፍርድ
ቤት የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጡ። አርበኞች ግንቦት 7ትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሊሻገሩ ሲሉ ተይዘው በወህኔ ቤት
የሚገኙት የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት የነበሩ ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድና ወጣት እየሩሳሌም ተስፋው
ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ይህንን ያቀረቡት በጽሁፍ ሲሆን፣ እንዳያነቡ መከልከላቸውም
ተመልክቷል።
የሰላማዊ ትግል ጥረታቸው ባለመሳካቱ የመብትና የነጻነት ጥያቄ አንግበው ግንቦት 7ትን ለመቀላቀል ሲሉ መያዛቸውን የዘረዘሩት
ብርሃኑ ተክለያሬድና እየሩሳሌም ተስፋው ወደዚህ ሁኔታ የገፋቸው የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ባቀረቡት ጽሁፍ
ገምግመዋል። ከምርጫ 97 በፊት እንዲሁም በምርጫ 97 እና በኋላ ሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ያለበትን ሁኔታ ገምግመው
በውጤቱ 14 ጊዜያት ለእስር መዳረጋቸውን አስታውሰዋል።
በሃገሪቱ አሉ የተባሉ አፈናዎችን ዘርዝረው በዜጎች
ላይ የሚደርሱ ሰቆቃዎችን አስታውሰው “ሰላማዊ ትግል ማድረግ ይቻላል ብለው የሚያምኑ የዋህ ወገኖቻችን ዕውነቱን
ይገነዘቡት ዘንድ እንዲሁም ለከሳሾቻቸን ንጹህነታችንን እናስታውሳቸው ዘንድ ካደረሱብን ነገሮችን ጥቂቶችን ብቻ
ለማንሳት እንሞክራለን” በማለት ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ባቀረቡትና እንዳያነቡ በተከለከሉት የተከሳሽነት ቃላቸው ላይ
ከራዕይ ወጣቶች ምስረታ ጀምሮ ያለፉበት ሂደትና እስከ 14 ጊዜያት የታሰሩበትን ዘርዝረዋል።
በሰላማዊ ትግል
ያደርጉትን ጥረትና ያለፉበትን መሰናክል በተከሳሽነት ቃላቸው ላይ ያመለከቱት ብርሃኑ ተክለያሬድና እየሩሳሌም ተስፋው
የመብትና የነጻነት ጥያቄዎች በጉልበት እየጨፈለቁ ያለው ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ሌሎችን አሸባሪ ብሎ መፈረጅ
አይልችልም፣ ይልቁንም በጸረሽብር ህጉ ለመጠየቅ የሚገባው እሱ ነው ሲሉ በጽሁፋቸው ተሟግተዋል።
ድምጻቸውን
በጠመንጃ ተነጥቀው ሃገራቸውን ለማዳን ተገደው ነፍጥ ያነሱት የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አባላት አሸባሪዎች
አይደሉም ይልቁንም ሽብርተኛ ተብሎ ሊጠቀስ የሚገባው ህወሃት ነው ያሉት ብርሃኑ ተክለ ያሬድ እየሩሳሌም ተስፋው
“በዚህ ህዝባዊ ድርጅት አርበኞች ግንቦት 7 ሆነን ሽብርተኝነትን ለመከላከል የወሰንን ሽብርንና ሽብርተኝነትን
የምንጸየፍ ንጹሃን ወጣቶችን ነን፣ በሽብር ቡድን አባል ለመሆንም ሆነ ሽብር ለመፈጸም አላሰብንም አልወሰንም
አልተንቀሳቀስንም” ሲሉ ተከራክረዋል።
በሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣት የማይቻልበት ደረጃ ላይ
ተደርሷል በሚል አርበኞች ግንቦት 7ትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ ተይዘው በወህኔ ቤት የሚገኙት ብርሃኑ
ተክለያሬድ እየሩሳሌም ተስፋው ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የተከሳሽነት ቃላቸው መጨረሻ ላይ “ለዚህ ችሎትና ለከሳሾቻችንን
በአጽንዖት ልናስገነዝብ የምንፈልገው ነገር የፈጸምነው ድርጊት ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ የሃገር ወዳጅነት
መለኪያ እንጂ ወንጀል ሆኖ የሚያስከስሰን ባለመሆኑ በእስር ቤት ውስጥ ሆነን እንኳን ከምንጊዜውም በላይ ፍጹም
ነጻነት ይሰማናል” ካሉ በኋላ አሳሪዎቻችንም ይኸው ነጻነት ይሰማቸው ዘንድ የቂም ፖለቲካን በመተው የታሰሩትን
ፈትተው ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰላም ጥሪ በማድረግ ስልጣን ለህዝብ እንዲያስረክቡ ጠይቀዋል። ይህን ካልፈጸሙ መጪውን
ጊዜና ታሪክ ምላሽ ይሰጠዋል ሲሉ የተከሳሽነት ቃላቸውን አጠናቀዋል።
ኢሳት
0 comments:
Post a Comment