Monday, 13 June 2016

ወያኔ ከገባበት ውጥረት ለመውጣት በከፈተው ጦርነት ትኩረታችን አይቀለበስም !! አርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ



በጥጋብና እብሪት የተወጠረው የህወሃት አገዛዝ በትናንትናው ዕለት ዕሁድ ሰኔ 5 ቀን 2008 በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በኩል ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ የድንበር ቦታዎች ላይ ጦርነት ጀምራል፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ይህን ዜና አረጋግጠው ዘግበዋል። ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በወያኔ በኩል ስለጦርነቱ ምንም የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም የኤርትራ መንግሥት በጾረና ግንባር በኩል ጥቃት እንደተፈጸመበት ትናንት ማምሻውን ይፋ ባደረገ መግለጫ አረጋግጦአል።

የህወሃት ዘረኝነት በፈጠረው ኢፍትሃዊነትና አፈና የተማረረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በአገዛዙ ላይ ተቃውሞውን እያጠናከረ ባለበት በዚህን ሰዓት በሙስና የተጨማለቁ የህወሃት የጦር ጀነራሎችና በሲቪል ማዕረግ አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩ ሃይሎች ለምን ይህንን ጦርነት መጫር እንደፈለጉ ግልጽ ነው። በኦሮሚያ የተነሳውን የመብት ጥያቄ ለማፈን ከ400 በላይ ሕዝብ መጨፍጨፉና በሺዎች የሚቆጠሩ እስር ቤት መታጎራቸው የህወሃትን ዕድሜ ለማራዘም እንደ አንድ መሣሪያ ሆኖ ላለፉት 25 አመታት ሲያገለግል በኖረው ኦህዲድ ውስጥ እንኳን ከከፍተኛ አመራር እስከ ተራ ካድሬ ያሉትን አስኮርፎአል። የወልቃይት ህዝብ ያነሳው የማንነት ጥያቄ ሌላኛው የህወሃት አጋር በሆነው ብአዴን ውስጥ የማያባራ ክፍፍል ፈጥሮአል። የነጻነት ታጋዮች በቅርቡ አርባምንጭ ከተማ አቅራቢያ የፈጸሙት የጀግንነት ገድል የደቡብ ኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያንቃቃና ለትግል የሚያነሳሳ አርአያነት እንደፈጠረ የህወሃት አገዛዝ ተረድቶአል። በቤኔሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በአፋርና በሱማሌ ከመሬት ንጥቂያ ጋር በተያያዘ ወንጀል ህወሃት ከህዝቡ ጋር አይጥና ድመት ድብብቆሽ ውስጥ ከገባ አመታትን አስቆጥሮአል። በአዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ቀድሞውኑም የድጋፍ መሠረት እንደሌለው ማወቁ ብቻ ሳይሆን ይኩራራበት የነበረው የትግራይ ምሽግነትም ከእጁ ሙሉ በሙሉ እያፈተለከ መምጣቱን ተገንዝቧል። በዚህም ምክንያት ፊቱን ወደሰሜን በማዞር የሕዝቡን ትኩረት አስታለሁ ብሎ ወያኔ አምኖአል። አባይ ጸሃይዬና ሳሞራ ዩኑስ መቀሌ ላይ በቅርቡ ባደረጉት የህወሃት ስብሰባ ላይ “ህወሃት ከሌለ የትግራይ ህዝብ አይኖርም፤ ኢህአደግ ከሌለ ኢትዮጵያ አትኖርም” ማለታቸው ኤርትራን በመውረር በተለይም የትግራይን ህዝብ ድጋፍ መልሶ ያስገኛል የሚል እምነት በአገዛዙ መሪዎች ውስጥ መፈጠሩን ያመለክታል።

ሌላው ህወሃትን ወደ ጦር አጫሪነት እየነዳው ያለው እብደት መለስ ዜናዊ ከሞተ ወዲህ ድርጅቱ ውስጥ የነገሰው የእርስ በርስ የሥልጣን ሹኩቻ የፈጠረው ውጥረት እንደሆነ መገመት አያዳግትም። አንዱን ውጥረት ለማርገብ ሌላ የውጥረት ግንባር በመክፈት ለሚታወቀው ህወሃት ይህ የተለመደ ስትራቴጂ ነው።

አርበኞች ግንቦት7 ህወሃት የኢትዮጵያን ሕዝብ ትኩረት ለመቀየር የሚያደርገው ማንኛውም አይነት ጥረት እንዳይሳካለትና የጀመረው ይህ የትኩረት ማስቀየሻ ስትራቴጂ የህወሃትን ውድቀት አፍጣኝ እንዲሆኑ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ካሁን ቀደም ለአገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የሚሰጠው ፋይዳ ሳይመከርበትና ሕዝባዊ ስምምነት ሳይኖር ከአሥራ አንድ አመት በፊት ሱማሌ ውስጥ ዘፍ ተብሎ የተገባበት ጦርነት በየቀኑ የስንት ወንድሞቻችንን ህይወት እየቀጠፈ እንደሆነ እያየነው ነው። ቁጥራቸው ከ60 በላይ የሆኑ ወገኖቻችን ሰሞኑ በሽብርተኛው አልሸባብ ሲጨፈጨፉ የወያኔ መሪዎች አንዲትም ወፍ የሞተቺባቸው ያህል እንኳ አልተሰማቸውም ። ይህንን ሁሉም ያገራችን ህዝብ ያውቃል። እስከዛሬ በሰላም አስከባሪነት ስም ወደ ሰው አገር እየተላኩ ደመ ከልብ እየሆኑ ያሉ ወገኖቻችን ህይወት እያንገበገበን ባለበት በዚህን ሰዓት ለወያኔ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ እንደ አገር የምንዋጋው ሌላ ጦርነት እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል። በ1998ቱ የባድሜ ጦርነት ወቅት ህዝባችን የከፈለው ዋጋና ከባድሜ ጦርነት መልስ ጉልበቱን አጠናክሮ ለመውጣት ዕድል ያገኘው የህወሃት በህዝባችንና በአገራችን ላይ እስከዛሬ እየፈጸመው ያለው አፈናና ጭፍጨፋ ተረስቶ ሌላ ዕድል ለመስጠት ዳግም መሳሪያ የምንሆንበት ምክንያት የለም።

አርበኞች ግንቦት 7 ከአሁን ቦኋላ ወያኔ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘምና የተዘፈቀበትን የሃብት ዘረፋ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያደርገውን የሞት ሽረት ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም አይነት ሁኔታ ማስተናገድ የለበትም ብሎ ያምናል። በዚህም ምክንያት በመላው አገራችን የተጀመረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለፍትህ ለእኩልነትና ለነጻነት የሚደረገው ትግል ከግቡ እንዲደርስ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ ትግሉን ለማጠናከር እንዲረባረብ አርበኞች ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል ። በመካሄድ ላይ ያለውን የነጻነት ትግል አቅጣጫ ለማስለወጥ ወያኔ የሚያደርገውን የጦርነት እንቅስቃሴ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የነጻነት ቀናችንን እንድናፋጥን ሁላችንም እንነሳ ።

አርበኞች ግንቦት 7 ወያኔ በሰሜን በኩል የጀመረውን ትንኮሳ እየተከታተለ ለህዝባችን ወቅታዊ መረጃ ይሰጣል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አርበኞች ግንቦት 7

0 comments:

Post a Comment