Tuesday 31 May 2016

የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃመንድ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ

በእስር ላይ የሚገኙ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቂ ህጋዊ ድጋፍን አላገኙም በማለት ለኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ሲሰጡ የቆዩት የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃመንድ ነገ በስቲያ ረቡዕ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ። ሚኒስትሩ ሃመንድ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ብሪታኒያ ለምታነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የማትሰጥ ከሆነ የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙንት ሊሻክር ይችላል ሲሉ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።

የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች የብሪታኒያ መንግስት ዜጋውን ለማስለቀቅ በቂ ትኩረትን አልሰጠም ሲሉ በድጋሚ የተቃውሞ ዘመቻን እያካሄዱ እንደሚገኝ ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የዘጠኝ አመት ታዳጊ ህጻን በሃገሪቱ መንግስት ላይ ክስ መመስረቷ የሚታወስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ጉብኝትን የሚያደርጉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን አብይ ጉዳይ አድርገው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በአዲስ አበባ ጉብኝትን ያደርጋሉ ቢልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ሳያደርጉ መቅረታቸውን ለመርዳት ተችሏል።
ይሁንና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፊሊፕ ሃመንድ በኢትዮጵያ የሁለት ቀን ጉብኝትን ለማድረግ ረቡዕ አዲስ አበባ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስሩን ጉብኝት ልዩ ቢያደርግም የጉብኝቱን አጀንዳ በተመለከተ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሁም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድበት ለመረዳት ተችሏል።

የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን የሚከታተልውና ሪፕሪቭ የተሰኘው የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሃገሪቱ መንግስት ከሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይልቅ ለዲሞክራሲ እንዲሁም ለዜጎች መብት መከበር ቅድሚያ እንዲሰጥ በድጋሚ አሳስቧል።
በተለያዩ መድረኮች የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በማንሳት ሲወያዩ መቆየታቸውን ሲገልጹ የቆዩት የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃመንድ፣ መንግስታቸው ሲያቀርብ የቆየው ጥያቄ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ የኢትዮጵያና የብሪታኒያ ግንኙነት ሊሻክር ይችላል ሲሉ በቅርቡ ማሳሰባቸው ይታወቃል።

ሚኒስትሩ ከእሁድ ጀምሮ በሳውዲ አረቢያ ጉብኝትን እያደረጉ ሲሆን፣ ከስድስት የባህረ-ሰላጤ ሃገራት መሪዎች ጋርም እንደሚወያዩ ታውቋል።

0 comments:

Post a Comment