Wednesday 4 May 2016

አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከኦ.ነ.ግ ጋር ተያይዞ የሽብር ክስ ተመሰረተበት

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም የወጣውን አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ክስ ተመስርቶበታል፡፡

ዛሬ ሚያዝያ 26/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክሱ በዳኞች ቢሮ በንባብ የተሰማበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24/2008 ዓ.ም ጀምሮ ተከሳሹ በሚጠቀምበት ደረ-ገጽ በተለይም ፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ‹‹አመጽና ብጥብጥ›› ለማስቀጠል የኦ.ነ.ግ.ን አላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦበታል፡፡ የክስ ፋይሉ ሌላ ምንም አይነት ተከሳሽን ሳይጨመር ለብቻው ለአቶ ዮናታን የተከፈተ ሲሆን የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር በማህረሰብ ሚዲያ የለጠፋቸው ፅሁፎች ናቸው፡፡

በዚህም ተከሳሹ ‹የቡድኑን (ኦነግ) አላማ ለማሳካት አመጽና ብጥብጡ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በሚጠቀምበት ደረ-ገጽ (ፌስቡክ) ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመጻፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር፣ እና ማነሳሳት ወንጀል› መከሰሱን የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተለያዩ ቀናት በግል የፌስቡክ ገጹ ላይ ያስነበባቸው ጽሁፎች ክሱ ላይ ተካተዋል፤ በማስረጃነትም ተያይዘውበታል፡፡

በቀን 08/04/2008 ዓ.ም ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በተመለከተ የጻፈው፣ በ11/04/2008 ዓ.ም ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም በሚል የጻፈው፣ 06/04/2008 ዓ.ም ሲጀመር ምንም ማስተር ፕላን የለም በሚል የጻፈው፣ 01/04/2008 ዓ.ም የተቃውሞ ትግሉ ቀጥሏል በሚል የጻፈው፣ 28/03/2008 ዓ.ም እንሆ 7 መልዕክት ብሎ በጻፈው እና በሌሎችም ጽሁፎች አማካኝነት ቅስቀሳ አድርጓል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ጠቅሷል፡፡

ዮናታን ተስፋዬ በነጠላ መዝገብ ብቻውን የተከሰሰ ሲሆን፣ ዛሬ ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ጉዳዩ በቢሮ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ዮናታን የክስ መቃወሚያውን ይዞ እንዲቀርብ ለግንቦት 15/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

ሙሉ ክሱ ከስር ያለው ሊንክ ላይ ይገኛል፡፡
https://drive.google.com/file/d/0BycbySIJbSLpamdsV2Vtb2g0LXM/view?pref=2&pli=1

0 comments:

Post a Comment