Sunday, 25 September 2016

የዲምክራሲለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ እና የኢትዮጵያ የጋራ መድረክ የተሰጠ የአቋም መግለጫ !!


አገራችን ኢትዮጵያ በጎጠኛና ዘረኛ ቡድን መዳፍ ስር ወድቃ  ህዝቦቿ ከመቼውም እጅግ የከፋ የመከራና ስቃይ  ፅዋ  እየጠጡ ተዋርደውና ተንቀው በመኖር እነሆ 25 የግፍ አመታት ተቆጠሩ፤ ዘረኛውና አምባገነኑ ቡድን ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ማህበራዊ እሴቶችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ በማንአለብኝነት፣ ቅጥ በአጣ ትምክህትና አረመኔያዊነት በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ሂትለራዊና ፋሽስታዊ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል።

ይህ አይነት ዘረኛ ቡድን በማነኛውም መለኪያ እንዲሁም ታሪካዊ ዳራ ኢትዮጵያን ያክል ታላቅ ታሪክ ያላት ሀገር ለማስተዳደርም ሆነ ለመምራት ፈጽሞ  ብቃትና ሞራል እንደሌለው ከፈጸማቸውና ከሚፈጽማቸው እኩይ ተግባር በተጨባጭ ለማየት ችለናል፤ በድርጊቱም እጅግ አዝነናል፣ ተቆጭተናል፣ የበለጠ እልህ ውስጥም ገብተናል። ይህም የወያኔ አረመኔያዊነት በቅርቡ በአገራችን ተቀጣጥሎ በመካሄድ  ላይ የሚገኘው ህዝባዊ እምቢተኝነት ደረጃ  ላይ እንዲደርስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

እንደ  አገዛዙ ሥርዓት የፖለቲካ ዓለማና ግብ ኢትዮጵያዊያን በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለው እርስ በእርስ እየተጋጩና እየተናቆሩ ለአገዛዙ የሥልጣን ማራዘሚያ  የሚጠቀምበት ከንቱ ስልት ተዳክሞ የአንድነት ኃይሉ ተጠናክሮ  በጋራ የኢትዮጵያ ታላቅ ጠላት በሆነው በወያኔ ሥርዓት ላይ በቁርጠኝነት እንዲነሳ  ጊዜ የማይሰጠ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህን የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ስልት ከመጨረሻው ግብ ለማድረስ የተያዘው የነጻነት ትግል ለውጤት እንዲበቃ  ምን መደረግ አለበት የሚለውን ዋና ሃሳብ በመያዝ ሁሉም ለኢትዮጵያ  ፍትህና ዲሞክራሲ መስፈን፣ ዲሞክራሲያዊና  ሰባዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ህዝባዊ ተቋማትና የእያንዳንዳችን እንደግለሰብ ልናበረክት የሚገባን አስተዋጾ ላይ ለመምከር ይህ ዛሬ የተጠራው ህዝባዊ ውይይት  እጅግ  ጠቃሚ ወቅታዊ ጉዳዮችና የመፍትሄ ሃሳቦች የተነሱበት፣ ከፍተኛ የትግል መነቃቃትና አብሮነት የተንጸባረቀበት ነበረ።

የተጀመረው  ህዝባዊ እምቢተኝነት ከጫፍ ደርሶ  አረመኔያዊ አገዛዝ ከህዝባችን ጫንቃ አውርደን ለአንዴና ለመጨረሻ  ጊዜ ለመቅበር ሁለገብ እንቅስቃሴ  አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ከቀረቡ የውይይት ርዕሶች፣ ነጥቦችና  በተሳታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶችና የሃሳብ ልውውጦች  የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ተችሏል። በተጋባዥ እንግዶች በዶ/ ሙሉዓለም አዳም፣ በዶ/ ተክሉ አባተ እና ወጣት ኤልሳቤጥ ግርማ የቀረቡ የመወያያ ነጥቦችም  በሚገባ ወቅቱን ያገናዘቡና የታለመላቸውን ግብ ማሳካት እንደሚችሉ ከውይይቱ በአጽንኦት ተረድተናል።

ዛሬ በዚህ አዳራሽ ለውይይት የተገኘን ኢትዮጵያውያን አገራችን ከገባችበት አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ በማውጣት እውነተኛ ሰላም፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላችንን ጥረት ማድረግ እንደሚገባን በውይይቱ የተሰጡትን የመፍትሄ ሃሳቦች፣ አቅጣጫዎችና የትግል ስልቶች በሚገባ ተረድተን ለአፈጻጸማቸው አውንታዊ ምላሽ ለመስጠትና በትግሉ ጎራ ሙሉ በሙሉ ለመሳተፍ በአንድ ድምጽ ተስማምተን ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ነጥቦች በጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

 1. በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ወቅት በንጹሃን ዜጎች ላይ በአረመኔው   የወያኔ አግዓዚ ጦርና ልዩ ኃይል የተወሰደውንና እየተወሰደ ያለውን እጅግ ዘግናኝ አረመኔያዊ ግድያዎችን አምርረን እናወግዛለን፤ ገዳዮችንም በህግ እንፋረዳቸዋለን፤ ሰማዕታትንም በታሪክ ለዘላለም እንዘክራቸዋለን

 2. የጥፋት መልዕክተኛ ዘረኛ የፋሽስት ስርዓትንና ተባባሪዎቹን ለማሶገድ የሚደረጉ ማናቸውንም አይነት የትግል ስልቶችንና ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ በአንድነት እንደግፋለንእንሳተፋለን

 3. ዘረኛውና አንባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በዓለም አቀፍ መድረክ ያለውን የድፕሎማሲ ቁመና በማጋለጥ ድጋፋ የሚያደርጉ አጋሮቻቸውንም ከሚሰጡት እርዳታ እጃቸውን እንዲሰበስቡ አጠክረን እንመክራለን እንዲሁም በውጭ በሚገኙ ማነኛውም የወያኔ ተቋማትና መጠቀሚያ ድርጅቶች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊና ሞራላዊ እርምጃ በመውሰድ እና ማዕቀብ በማድረግ እንዲዳከሙ እናደርጋለን

 4. በኢትዮጵያ የተረጋገጠ ሰላም፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ለማስፈን የቆሙ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ህዝባዊ ተቋማት የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት መምራት፣ ማስተባበርና በቀጥተኛ ተሳትፎ ተገቢውን ሚና እንዲጫዎቱ እንጠይቃለን።

  5. በአገራችን በሚካሄደው የለውጥ ትግል ሂደት መሪ ተዋናኝ በመሆን ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ያለውና በትግሉም ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈለ በሚገኘው ከወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንሰጣለን በማነኛውም ጊዜ ከጎናቸው እንቆማለን

  6. በኢትዮጵያ መፃኢ እጣ ፈንታ ለመወሰን በጋራና በተናጠል ለሚታገሉ አካላት መካከል ያለውን መለስተኛ የአመለካከት ልዩነት በማጥበብና በመቻቻል ተከባብረው በጋራ ጠላታችን ላይ ያነጣጠረ ትግል እንዲያካሂዱ ጥሪ እናደርጋለን

  7. ዘረኛውና አንባገነኑ የወያኔ ስርዓት ከአሁን በኋላ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ጥርጣሬና ያለመተማመን ስሜት በመፍጠር የአገዛዝ እድሜውን ለማራዘም የሚጠቀምበት ኋላቀር አካሄድ ከዚህ በኋላ እንዳይቀጥልና ትግሉ ኢትዮጵያዊነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን በጋራ እንታገላለን!

ድል ለሰፊው ኢትዮጵያዊ ህዝብ፤ ውድቀትና ሞት ለወያኔ ዘረኛ ቡድን   
መስከረም 14 , 2009 ዓም ኖርዌይ ኦስሎ



0 comments:

Post a Comment