Tuesday, 13 September 2016

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ፓለቲከኛ አንዱአለም አራጌ በሽብር እና በሃገር ክህደት ወንጀል ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ከገቡ ድፍን አምስት ዓመት ሆናቸው

ጋዜጠኛ ና ጦማሪ እስክንድር ነጋ እና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፓለቲከኛ አንዱአለም አራጌ በሽብር እና በሃገር ክህደት ወንጀል ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ከገቡ መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም ድፍን አምስት ዓመት ሆናቸው፡፡

እስክንድር "ንፁህ ስለሆንኩኝ፣ የቀረበብኝ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ እንዲሁም ፍርድቤቶችን የሚያህሉ የተከበሩ ተቋማት የበቀል የአፈናና የጭቆና መድረክ መሆን ስለሌለባቸው በነፃ እንድለቀቅ የተከበረውን ፍርድቤት እጠይቃለሁ" ብሎ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኙን በነሐሴ 2004 ዓ.ም ያቀረበ ቢሆንም የከፍተኛው ፍርድቤት የፈረደበትን የአስራ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና አምስት አመታት ህዝባዊ መብቶች እግድ ጠቅላይ ፍርድቤቱም አፅንቶበት የፍርዱን ሩብ አመታት በእስራት አሳልፏል፡፡

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አምስት አመታትን በእስር ሲያሳልፍ ዘንድሮ የ48 አመት ጎልማሳ የሚሆነው ጦማሪው እስክንድር ነጋ በየኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ መንግስት ለሰባተኛ ጊዜ ሲታሰር በበርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብተ ተሟጋች ድርጅቶች እስራቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆን ደምፃቸውን ከፍ አድርገው አምስቱንም አመታት ለኢትዮጵያ መንግስት ውትወታቸውን አስምተዋል፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፍርድቤት የችሎት ሂደቱን በመከታተል ላይ እያለ በግንቦት ወር 2004ዓ.ም ፔን አሜሪካ ከተባለ አለማቀፍ ድርጅት በአደገኛ የመገናኛ ብዙሐን ድባብ ውስጥ ሆኖ በመፃፍ ላደረገው አስታዋፅኦዖ "የመፃፍ ነፃነት ሽልማትን" አግኝቷል፡፡ በዚሁ አመት አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስክንድር ነጋ የህሊና እስረኛ ስለመሆኑ አውጇል፡፡
ለሰባተኛ ጊዜ ለእስር በተዳረገ በአንድ አመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ በታህሳስ 2005ዓ.ም ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዎች የነፃ ንግግር ሽልማት አሸናፊ ከመሆኑ በተጨማሪ በ36ተኛው አለማቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲቫል ላይ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ "የአንድ ስብዓዊነት ሽልማት" አሸናፊ ሆኗል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያው በሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር አዋጅ ቀደምት ሰለባ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር በ1997 ዓ.ም የተደረገውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ መንግስት በአገር ክህደት፣ አመፅ በመቀስቀስ፣ህገ መንግስት እና ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የፈረደበት ቢሆንም አንድ አመት ከአምስት ወራት እሰራት በኃላ ክሱ ተቋርጦ መለቀቁ ይታወሳል፡፡

የኢንተርናሽናል ወመንስ ሚዲያ አሶሴሽን "የብርቱ ጋዜጠኛ" ሽልማት አሸናፊ የጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርክዓለም ፋሲልም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ ከባለቤቷ ጋር በተመሳሳይ ክስ በአንድነት ታስራ በቃሊቲ እስር ቤት ሳለች የመጀመሪያ እና ብቸኛ ልጃቸውን ናፍቆት እስክንድርን ተገላገላለች፡፡

የያኔው ስድስተ አመት ህፃን ልጁን ከትምህርትቤት ወደ ቤት እያመጣ ሳለ በድንገት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው እስክንድር ነጋ እነሆ ዛሬ አብረውት ከተከሰሱት 23 አባሪዎቹ ጋር አምስት አመትን ሲደፍን የቀደሞ የአንድነት ፓርቲ ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌም የእድሜ ልክ እስራቱን በቃሊቲ ማረሚቤት እየገፋ ይገኛል፡፡

‹ምርጫ 97ን›› ተከትሎ ወህኒ ከወረደው የቅንጅት አመራር አንዱ የነበረው የያኔው ወጣት የአሁኑ ጎልማሳ፣ በብዙዋች ዘንድ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ተበሎ የሚወደሰውአንዷለም አራጌ የቅጥት ማቅለያ እንዲያቀርብ በፍርድቤት ሲጠየቅ አንዷለም አራጌ እንዲህ ብሎ ነበር ማቅለያውን ያቀረበው፡፡ "እኔም ለልጆቼ፣ ለወገኖቼ፣ ለአገሬ እና ለራሴ በመረጥኩት ሰላማዊ ትግል ስታገል ቆይቻለሁ፡፡ የበደልኩት ህዝብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ወንጀል ሰርቻለሁ ብዬ አላሰብም፡፡ ውስጤ ፍፁም ሠላማዊ ነው ከሳሾቼ የሚስጡኝን የግፍ ፅዋ ለመጠጣት ዝግጁ ነኝ፡፡"

አቶ አንዷለም አራጌ “ያልተሄደበት መንገድ” የሚል የመጀመሪያ መጸሐፉን በእስር ላይ ሆኖ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለአንባቢያን አደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም ሰኔ ወር ደግሞ “የሀገር ፍቅር እዳ” የተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፋ ዳግም ለህትመት በቅቷል፡፡
እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ የሰላማዊ ትግል አርበኞ አዲሱን አመት 2009 ዓ.ም የተቀበሉት አምስተኛ አመታቸውን በማሰብ ነው፡፡

እስክንድር ነጋ እና አንዷዓለም አራጌ በፍትህ እጦት አመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ሲገደዱ እስራቸው አገሪቷ በዓለም አቀፍ ህግ መደረክ ተገዢ እሆናለሁ ብላ ቃል የገባችባቸውን የቃልኪዳን ሰነዶች ሁሉ የናደ ሰለመሆኑ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲሞግቱ አምስት አመታት አልፈዋል፡፡

ዛሬም አስራቸው ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ አላግባብ፣ ኢፍታዊ እና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ያላከበረ ነው ፡፡ አንዱአለም በተለምዶው ቅጣት ቤት ተብሎ የሚጠራው ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ታስሮ ሲገኝ እስክንድር በቃሊቲ የተለያዩ ዞኖች ታስሯል፡፡ ሁለቱም እስረኞች ከቅርብ ቤተሰብ ውጪ ማንም እንዳይጠይቃቸው የተከለከሉ ሲሆን ከእስራቸው እስከ አያያዛቸው ኢሰብአዊነትን እያስተናገዱ አምስት አመት አስቆጥረዋል፡፡

የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት

                                                                 አንዱአለም አራጌ

                                                                         እስክንድር ነጋ

0 comments:

Post a Comment