በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ከመንፈቅ በላይ የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ እስር ቤት የተጋዙ ዜጎች ቁጥር
ከ40ሺህ እስከ 50ሺህ እንደሚገመት የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ገለጹ። ወጣቶቹ በስርዓቱ ላይ
ተቃውሟቸውን ከሚገልጹባቸው መንገዶች አንዱ ባለስልጣናት ስርዓቱን እንዲያወግዙና መንገድ በድንጋይ እንዲዘጉ ማስገደድ
እንደነበርም አመልክተዋል። ኦህዴድ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ መስከረም ወር ላይ ስራ ጀምሮ፣
በህዳር ወር የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ስለምርጫው ውጤት በራሱ የሚናገረው ነገር መኖሩን ያመለከቱት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣
ምዕራብያውያኑ በምርጫው ከ50 እስከ 60 ወንበር ለተቃዋሚዎች
ይለቀቃል የሚል ዕምነት እንደነበራቸውም አስታወሰዋል።
ምርጫው በኢህአዴግ አሸናፊነት ተጠናቀቀ በተባለ ማግስት
ኦሮሚያ ክልል ግንጪ ውስጥ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከህጻናት እስከ አዛውንት ሌላው ቀርቶ የአካባቢው ሚሊሺያዎችን ጭምር
ያሳተፈ እንደነበር ገልጸዋል። ወሊሶ አካባቢ በአንድ ባለስልጣን ላይ ወጣቶች የፈጸሙትንና በማስገደድ መንገድ
ያዘጉበትንም ሁኔታ ዶ/ር መረራ ለኢሳት በሰጡት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል። ወሊሶ ላይ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን
ሃላፊ ወጣቶች ሲመጡባቸው ጠረጴዛ ስር ለመደበቅ ያደረጉትን ሙከራ በኋላም አስገድደዋቸው ድንጋይ እየተሸከሙ መንገድ
መዝጋታቸውን በዚሁ ቃለምልልስ አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በተቀጣጠለበት ወቅት የሃገሪቱ
የደህንነት ሃላፊዎች የመድረክ አባል ፓርቲዎችን ከኦፌኮ ነጥለው በማነጋገር ስብስቡን ለመከፋፈል መሞከራቸውንም
አስታውቀዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ተገደው መውጣታቸውን የገለጹት ዶ/ር መረራ
ጉዲና፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት የነበሩት እንድርያስ እሸቴ ከየትኛውም ተቋም የፕሮፌሰርነት ማዕረግ
ሳይሰጣቸው ፕሮፌሰር እየተባሉ ሲጠሩ መቆየታቸውን በዚሁ ቃለምልልስ “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና አልታረቅ ያሉ
ህልሞች” በሚለው መጽሃፋቸው በዝርዝር ተመልክተዋል።
ኢሳት
0 comments:
Post a Comment