“ረሃቡ ከምን እንደሚመነጭ በትክክል ማስቀመጥ መፍትሄውን
ለማስቀመጥ ወሳኝ ነው። የረሃቡ ቀጥተኛ ምንጭ ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የተከሰተው ድርቅ ነው። የአየር
ንብረቱ መዛባትና ድርቁ እኛ ያልፈጠርነው ልናስተካክለው የማንችለው ነባራዊ ሃቅ ነው። በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ማዕቀፍ
ድርቁን ተቋቁመን ረሃቡን ለማስወገድ ያስቀመጥነው ስትራቴጂ ተዓምር ሰሪነቱ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን
በተግባር ተረጋግጧል። የረሃቡ ዋነና ምንጭም የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ ነባራዊ ሁኔታን መቋቋም ረሃብን
ለማጥፋት የቀየስነው ስትራቴጂ በሚፈለገው ፍጥነት በሁሉም አካባቢዎችን ስላልተፈጸመ ነው” ይላል።
በዛን ወቅት “በምጥቁ መሪ!” አብዮታዊ አመራር ሰጪነት የተሰራው ወንጀል ዘመን ተሻጋሪና ነገ ከነገ ወዲያ ተጠያቂነትን የሚያመጣ ነው።
እንዲህ ነበር የሆነው፥
በኢትዮጵያ አዲስ ሚሊኒየም ዋዜማ የተከሰተው ድርቅ ወደረሃብ መሸገገሩን የሚያሳይ ረፖርቶች ከመላው ሃገሪቱ መሰማት ጀመሩ። የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ከዛ አመት በፊት በነበሩት አራት አመታት ኢኮኖሚያችን በሁለት አህዝ አድጓል፥ ሚሊየነር አርሶ አደሮች መፍጠር ችለናል በሚል ቅኝት የሚመራ ስለነበረ ይህን መርዶ ለመቀበል አስቸጋሪ ሆነ። ረሃብን አስወግደናል ብለን ባወጅን ማግስት በረሃብ ተጠቅተን መገኘት በእርግጥም አሳፋሪ ነበር። የአመራርና የማስፈፀም አቅማችን፣ ምርጥ ልምዶች የማስፋት ስትራቴጂያችን ለአለም ተምሳሌት ሆኗል ባልን ጥቂት ቀናት ህዝቡ ረሃቡን መቋቋም አቅቶት እየተሰደደ መሆኑ መመልከት ፕሮፓጋንዳችን “ቢወቅጡት እምቦጭ” እንደሆነ የሚያመላክት ሆነ።
እንደ ተፈራው በዕልፍ አመቱ ዋዜማ የሰው ህይወት በየቦታው መውደቅ ጀመረ፥ ረሃቡን መቋቋም የማንችልበት ሁኔታ ግልፅ ሆኖ ወጣ። የመጀመሪያ ሰሞን እውነታውን አውገርግሮ ከማቅረብ ይልቅ ትክክለኛው መረጃ ተሰብስቦ ወደኢህእዴግ ቢሮ እንዲመጣ ልዩ ውሳኔ ተላለፈ። ለማመን በሚቸግር ሁኔታ የረሃቡ ዋነኛ ሰለባ ከሆኑት አካባቢዎች የሚመጣው መረጃ እጅግ አስፈሪና አስደንጋጭ ሆነ። ከሶማሊያ ጫፍ እስከ አብርሃ አጽብሃ የሚባል የትግራይ ቀበሌ ድረስ ህዝቡ የሚላስ የሚቀመስ ማጣቱ ታወቀ። የከፋ ረሃብ ያጋጠማቸው አካባቢዎች ልጆቻቸውን እየቀበሩ ቀዬአቸውን እየለቀቁ መሰደድ መጀመራቸው እሙን ሆነ።
በሚሊኒየሙ ዋዜማ የችጋሩ ዋነኛ ተጠቂ ከሆኑት አካባቢዎች የመጀመሪያው የሱማሌ ክልል ነበር። የሱማሌ ክልል ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ለስርዓቱ ተገዢ እንዳልሆነ በገሃድ የሚታወቅ እውነታ ነው። በዛ ላይ አካባቢው በጦርነት የሚታመስ መሆኑ የረሃብ አደጋው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አደረገው። በወቅቱ የተፈጠረው ረሃብ በ10ሺዎች የሚጠጉ የቀንድ እና የጋማ ከብቶች መሞታቸው ታወቀ። ከ80 -100 የሚሆኑ ህጻናት በረሃቡ ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈ የሚያሳይ መረጃ የስም ዝርዝር ረፖርት ቀረበ።
ይህንን የሱማሊያ የረሃብ ሁኔታ የተቀበለው ጓድ በረከት ከ “ባለራዕዩ መሪ!” ጋር በመነጋገር አንድ ጠንካራ ትዕዛዝ ሰጠ። ጥብቁ ትዕዛዝ “ማንኛውም የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጋዜጠኛ፣ በመንግስት ክትትል የማይደረግበት በጎ አድርጎት ድርጀት (NGO) ወደሶማሊያ ዝር እንዳይል!” የሚል ነበር። እነሆ ላለፉት 10 አመታት የትኛውም የነጻ ፕሬስ ሆነ የውጭ ጋዜጠኛ ወደሶማሊያ ክልል ልሂድ ብሎ ጥያቄ ቢያቀርብ ኣይፈቀድለትም። ከጓድ በረከት ጋር የቅርብ ወዳጅነት የመሰረቱትም ቢሆን ፍቃድ አያገኙም። የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጣቸው ጥያቄዎች እንዲጥሉ ይደረጋል። በዚህ ምክንያት በሱማሊያ በረሃቡ የሞቱት ህጻናት ከሪፖርቱ ውጪ እንዲሆኑ ተደረገ። እስከ 100 የሚደርሱት ህውየታቸው ያለፉት ህጻናት ማህደር በኢህአዴግ ቢሮ ተቆለፈበት።
በሚሊኒየሙ ዋዜማ ሌላኛው የረሃቡ ተጠቂ አካባቢ ደቡብ ኢትዮጵያ ነበር። ረሃብ ታሪክ ተደርጎበታል የተባለው የደቡብ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች እየረገፉ መሆኑን አስቀድመው መረጃ የመጡት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የውጭ ጋዜጠኞች በመሆናቸው መደበቅ የሚቻል አልነበረም። ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ጋዜጠኞች የተፈናቀሉ እና የሞቱ ሰዎች የሚያሳዩት ዘገባዎችን ለዓለም ህዝብ በማስተላለፋቸው ምክንያት መነጋገሪያነቱ ከጫፍ ጫፍ ናኘ። በመሆኑም ነባራዊ ሁኔታውን እንደቅቡል መውሰድ፣ ግን ደግሞ እውነታውን አውረግርጎ ማቅረብ የአቶ መለስ መራሹ የመንግስት የፕሮፓጋንዳ ስትራቴጂ ሆኖ እንዲቀረፅ ተደረገ።
በዚህም ምክንያት የተራበው ህዝብ ከ 14 ሚሊዮን በላይ ቢሆንም ጓድ! መለስ ባዘጋጀው “የሰሞኑ የረሃብ ፖለቲካ” የውስጠ-ድርጅት ሰነድ ጨምሮ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት 6.4 ሚሊዮን ብቻ ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸው አሳወቁ። በሱማሊያ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ከ500 ያላነሱ ህጻናት በረሃብ ቢሞቱም የፕሮፓጋንዳ ማሽን ከ30 እንደማይበልጡ ይፋ አደረገ። ይህንን አውነታ በማስረጃ ለማስደገፍ ያህል “የሰሞኑ የረሃብ ፖለቲካ” በሚለው የፓርቲ ሰነድ ከገፅ 7-8 የሚከተለውን ይላል፥
“በአንዳንድ የደቡብ አካባቢዎች አደጋውን በወቅቱ ካለማየት
ጋር ተያይዞ ባለፈው አመት 26 ያህል ህጻናት ለሞት የተዳረጉበት ሁኔታ ተከስቷል። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ
በረሃብ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች የሉም። አልፎ አልፎ በአፈጻጸም ጉድለት ምክንያት እንደተጠቀሰው የሟች ዜጎች
ቢኖሩም በአጠቃላይ በመቶ ሺዎች ቀርቶ በመቶዎች የማይሞቱበት ተፈጥሯል። በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታየው የአፈጻጸም
ጉድለት ካስተካከልን ምንም ዜጋ የማይሞትበት ሁኔታ መፍጠር እንደምንችልም ጥርጥር የለውም” ይላል።
እዚህ ላይ ማንም አእምሮ ያለውና የአለምን ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚከታተል ሰው የአየር መዛባት፣ የዝናብ እጥረት አልተከሰተም አይልም። ከአገዛዙ ከበለጠ የድርቅ ባህሪያና ትርጉም መረዳት የሚያቅተውም አይደለም። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የምግብ ምርት ወይም የውሃ አቅርቦት በመቀነሱ ከፍተኛ ጫና የሚያስከትሉ የእርጥበት እጥረት መከሰቱን የሚክድ የለም። የድርቅ መነሻ ምክንያቱ ከመደበኛ እና ከሚጠበቀው በታች በአየር ጠባይ መለያየት የተነሳ የዝናብ እጥረት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በአለም አቀፍ ደረጃም በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት በተለያዩ ዘመናት ሃገሮች በድርቅ ሲጠቁ ተመልክተናል።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ባለፈው ክረምት ጓድ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከውጭ የመጡ የሃገሬ ሰዎች በሚሊኒየም አዳራሽ ሰብስቦ ያሰማው “ኢህአዴጋዊ አውነታ” የኢትዮጵያውያን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በተለይ በካሊፎርኒያ የአሜሪካ ዜጋ በድርቅ እየተሰቃየ መሆኑ አስረግጦ ሲናገር የተሰማው ጭብጨባ እስከዛሬም ጆሮዬን ይሰቀጥጠናል። የሆነው ሆኖ “ካሊፎርኒያ በድርቅ ተሰቃየች” የሚለው አባባል የትኛውን ግብ ለማሳካት በጭብጨባ እንደታጀበ የሚያውቁት አጨብጫቢዎች ብቻ ቢሆንም የገባንበትን የሰብዕና መላሸቅ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር። የአውስትራሊያ አሊያም የካሊፎርኒያ ህዝብ በድርቅ ቢጠቃ ደስ ይለናል ማለት ነው?
የአገጣሚ ነገር ሆኖ የዛሬ ሳምንት እኔና ተወልደ በየነ (ተቦርነ) ለኢሳት የገቢ ማስገኛ ዝግጅት የካሊፎርኒያ እምብርት ወደሆነችው ሎስ አንጀለስ (LA) (ተቦርነ “ላይ አርማጭሆ” ይላታል) ሄደን ነበር። የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሚቴ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ “እንኳን በድርቅ ምክንያት እየተሰቃየች ያለችውን ካሊፎርኒያ በሰላም መጣችሁ!” በሚል ነበር የጀመሩት።
ይህንን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በአርምሞ ሲያዳምጡ የነበሩት ተሰብሳቢዎች በጭበ አስከትሎም የማያባራ ሳቅ አጀቡት። መቼስ! ተንኮል ካልሆነ በስተቀር ጭብጨባና ሳቅ ምን አመጣው? እንኳንም ጓድ! ሃይለማርያም በስብሰባው አልኖረ! እንኳንም በሚሊኒየም አዳራሽ የተገኙ የካሊፎርኒያ ነዋሪዎች አልሆኑ።
እናማ የስብሰባው አዘጋጆች ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ በያዙልን ዕለታዊ መርሃግብር መሰረት ካሊፎርኒያን ያስጎበኙ ነበር። የድሮ ካድሬ ነገር ሆኖብኝ የምንሄድበት መኪና በቆመ ቁጥር ነጩን፣ ጥቁሩን፣ ስፓኒሹን፣ አፍሪካዊውን ካሊፎርኒያ “ ድርቁ እንዴት ነው? ምን ጉዳት አስከተለ?” የሚል ጥያቄ አነሳ ነበር። ያለማጋነን ጥያቄ ከመለሱልኝ ሰዎች ውስጥ ዘጠና በመቶው ድርቅ መኖሩን አያውቁም። የተቀሩት ውሃ ለመቆጠብ የሻወር ቤታቸውን የውሃ ወንፊት እንዳጠበቡ ነግረውናል። ከፊሎቹ ለውሃ ቁጠባ ሲባል መኪናቸውን በሁለት ሳምንት አንዴ እያጠቡ መሆኑን እያዘኑ አጫውተውናል። ሃዘናቸውንም ተጋርተነዋል። የሻወር ቤት ወንፊት ከማጥበብ፣ መኪናን በሳምንት ሁለት ጊዜ ከማጠብ በላይ ምን ስቃይ አለ? አትክልትን ከሳምንት አምስት ቀን ሁለት ቀን ውሃ እንዲጠጡ ከማድረግ በላይ ምን የሚያበሳጭ ነገር አለ?
የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በግዛቱ የመንግስት ተቋም ውስጥ የሚሰራ ሙያተኛ ከአስጎብኚዎች አንዱ ነበር። ግለሰቡ ካሊፎርኒያ ያጋጠማት ችግር ጓድ ሃይለማሪያም ከጠቀሱት በተቃራኒ፣ ከልክ በላይ መብላት የሚመጣ ውፍረት (Obesity) መሆኑን ነገረን። ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዲሉ ወዳጃችን የካሊፎርኒያ ችግር ከመጠን በላይ ምግብ በመብላት እና የአካል እንቅስቃሴ ባለማድረግ የሚመጣ የሰውነት ውፍረት እንደሆነ አጫወተን። በመፍትሄ ደረጃም በግዛቱ በሚገኙ ት/ቤቶች “Child obesity school program” ቀርጸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ነገረን። በየመቶ ሜትሩ የምናያቸው የተዘረጠጡ ህጻናት ለፕሮግራሙ ተገቢነት የሚያረጋግጡ ነበር። እርግጥም ካሊፎርኒያን ጨምሮ በመላው አሜሪካ ጭንቀትና ስቃዩ የዜጎች የስብ ክምችት መሆኑን ለማወቅ ብዙ መልፋት አይጠበቅም። ለጥቂት ደቂቃዎች ወደኢንተርኔት ጎራ ያለ ሰው ከአሜሪካ አጠቃላይ ህዝብ 78 ሚሊዮኑ (ከዚሁም 12 ሚሊዮን ህጻናት) በውፍረት ግዝፈት መጠቃቱን ይመለከታል። ዘለግ አድርጎ ለተመለከተ ደግሞ የሰውነት ግዝፈት መጠን (obesity rate) በውፍረት በሽታ የግዛቶቹ ተደርድሮ ያያል። ለምሳሌ ካሊፎርኒያ 24.1%፣ ሚሲሲፒ 35%፣ ቨርጂኒያ 35.1% ወዘተ እያለ ይቀጥላል።
እነዚህን የመሳሰሉ ሀገሮች በአየር መዛባት ምክንያት ድርቅ ሲከሰትባቸው ትክክለኛ ፖሊሲ በመቅረፅ ዜጎቻቸውን ታድገዋል። የረጅም እና የአጭር ጊዜ ስትራቴጂካል እቅዶችን ከማውጣት ባሻገር ተስማሚ ቴክኖሎጂ በመምረጥ፣ የውሃ እና አፈር አጠባበቅ ተግባርን በማሻሻል፣ የግብርና ምርት ውጤቶችን ወደውጭ እንዳይወጡ በማገድ፣ የገጠር እና የከተማው ልማት በማቀናጀት… ወዘተ ዘላቂ መፍትሄ አስቀምጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች በማስፋፋት፣ የግብርና ምርታቸውን በከፍተኛ እጥፍ በማሳደግና፣ የህዝቡን የመግዛት አቃም በማጎልበት በድርቅ ምክንያት የሚከሰተውን አደጋ ከቁጥጥራቸው ውጪ እንዳይሆን አድርገዋል። ድርቅ ተፈጥሯዊ ነውና በማንኛውም ሰዓት ይመጣል፥ ግን ደግሞ እዚህ ግባ የማይባል ጉዳት አያደርስም። በፖለቲካው መስክም ቢሆን የገነቡት ዲሞክራሲያው ስርዓት ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገት የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። ያለነጻነት ሁሉን አቀፍ ልማት ማምጣት እንደማይቻል ተገንዝበው ለዜጎቻቸው ነጻነት አጎናጽፈዋል።
እንግዲህ በአለም ያለው እውነታ ይህ ነው። ይሁን እንጂ፣ “ የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” እንዲሉ ገዢዎቻችን በስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ በየሁለት አመቱ የሚከሰተውን ከድርቅ የተሻገረ ረሃብ በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት እንደሆነ ሊያስረዱን ይሞክራሉ። አገዛዙ ስልጣን በያዘ ሁለት አመታት ጀምሮ መጀመሪያ 6 ሚሊዮን፣ ቀጥሎ 10 ሚሊዮን፣ በማስከተል 14 ሚሊዮን ህዝብ በረሃብ ተጋልጦ ነበር። አሁን ደግሞ 15 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ የረሃብ አደጋ አንዣቦበታል። እነዚህ ጥሬ ሃቆች የሚካዱ አይደሉም።
በኢትዮጵያ ቀይ፣ ጥቁር፣ መረሬ አፈር ላይ የተነጠፉ እውነታዎች ናቸው። ዛሬም አገዛዙ በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት ራሳችንን መመገብ አቅቶን አቅማዳችንን ለመጽዋት ክፍት አድርገናል። አገዛዙ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰብዓዊና ሌሎች የህዝብ መብቶችን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን እስካልቀየረ አሊያም ስርዓቱ እስካልተቀየረ ድረስ የወደፊት እድላችን የከፋ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሆኗል። የፊተኛው መፍትሄ ኣያለፈበት ይመስላል። የስርዓት ለውጥ የሚለው ደግሞ ይበልጥ ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታይበት ሁኔታ ፈጥሯል። ፍጥነቱ በደረሰው መከራ እና አበሳ፣ በደረብን ቁጭት ልክ ባይሆንም። ዞሮ ዞሮ ሃገራችን የገባችበትን የረሃብ አዙሪት ትግሉን ከሚያዘውሩት ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ አልቀረም!
0 comments:
Post a Comment