Saturday, 14 November 2015

‹‹ርሃቡን ያመጣው የኢህአዴግ የስልጣን ስስት ነው!›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

 ነገረ ኢትዮጵያ
• ‹‹ለመፍትሄው መረባረብ አለብን››
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት

‹‹የርሃቡ የቅርብ ጊዜ ምክንያቱ የዝናብ እጥረት ነው፡፡ የዝናብ እጥረት ድርቅን እስከተለ፡፡ ርሃቡን ያመጣው ግን የኢህአዴግ የስልጣን ስስት ነው፡፡ የኢህአዴግ የስልጣን ስስት ለረዥም ጊዜ፣ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ታቅዶ እንዳይሰራ አድርጎታል፡፡ ኢህአዴግ የሚሰራው ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም እንጅ ለህዝብ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የሚሰራው አቅዶ ቢሆን፣ 10 አመት አደግን ተብሎ የ2 ወር ዝናብ መጥፋት ይህን ያህል ርሃብ ባላስከተለ ነበር፡፡ አሁን በየቀኑ የሚያወሩልን የውሸት ክምር ነው፡፡

የጭካኔያቸው ጭካኔ ደግሞ፣ ያኔ ርሃብን የስልጣን መወጣጫ እንዳላደረጉት አሁን ይህን ያህል ህዝብ ተርቦ ‹‹የአፋር ድርጅት በዓሉን አከበረ፣ ብአዴን የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው›› የሚል ዜና ነው በመንግስት ሚዲያ የምንሰማው፡፡ ይህን የሚያደርጉት ስለ ርሃቡ እንዳይሰማ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ጨካኞች እንደሆኑ፣ ከህዝብ ጋርም እንደተጣሉ ነው፡፡ ተግባራቸው ሁሉ የእብሪት እንጅ ህዝብን የሚጠቅም አይደለም፡፡

አገዛዙ ለርሃቡ ትኩረት አልሰጠም፡፡ በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ዋናው ትኩረታችን መሆን ያለበት መፍትሄው ላይ ነው፡፡ በችግሩ የተጎዳው ህዝቡ፣ እንዲሁም መፍትሄም የሚያመጣው ህዝቡ መሆኑን አውቀን መረባረብ ይገባናል፡፡ ለችግሩም ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የአደባባይ ሰዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ለዓለም መንግስታት ቅርበት ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ደርጅቶች በሙሉ ልንረባረብ ይገባል፡፡ ለመፍትሄው መረባረብ አለብን!››

0 comments:

Post a Comment