በዛሬው ዕለት በነሶልያና የክስ መዝገብ በዞን ዘጠኝ ጦማርያን ላይ ማለትም በሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት)፣ አቤል
ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና በፍቃዱ ኃይሉ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ችሎት ዳኞች
"አዳማ ስልጠና ላይ ናቸው" በሚል ባለመገኘታቸው ምክንያት ለጥቅምት 5/2008 ዓ/ም ለ 38ተኛ ጊዜ ቀጠሮ
መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱ ዳኞች የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ እና አቶ ዘርሁን ተቀይረዋል
የሚባል መረጃ የተገኘ ሲሆን አቶ ታረቀኝ ብቻ ችሎቱ ላይ ይቀጥላሉ ተብሏል። ለችሎቱ አዲስ የተሾሙት ዳኞች ማንነት
እስካሁን አልታወቀም።
በእስር 531ኛ ቀናቸውን እያሳለፉ የሚገኙት ጦማርያኑ ይህ የ"ፍርድ ቤት" ቀጠሮአቸው ለ38ኛ ጊዜ የተሰጣቸው ነው ፣ የቀረበባቸው ማስረጃን ገምግሞ ይከላከሉ ወይስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ የሚለውን ውሳኔ ለማሰማት "ፍርድ ቤቱ" የዛሬውን ጨምሮ ለ5ኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ስሜት የማይሰጡ ክሶች እና የተራዘሙ የፍርድ ሂደቶች ዜጎችን በአገራቸው የበለጠ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው
ከመሆኑም በላይ ያለዋስትና በፍርሃት እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው፣ ይህ እንዲሆን ካልተፈለገ በቀር በቀጠሮዎች መራዘም
ንጹሃንን ጥፋተኛ ማድረግ እንደማይቻል የዞን9 ጦማርያን እናምናለን፡፡
ባልተፈጸመ ወንጀል፣ ባልቀረበ ማስረጃ ዜጎችን ማንገላታት ይቁም፡፡
ዞን9
0 comments:
Post a Comment