Saturday, 3 October 2015

በኢትዮጵያ የርሃብተኞቹ ቁጥር 7.5 ሚልዩን ደርሷል



-በቅርቡ 15 ሚልዩን ይደርሳል እየተባለ ነው(ይህ ቁጥር በሶሪያ በተቀሰቀሰው ቀውስ ለመፈናቀል ከተዳረጉ ይበልጣል)
–855.000 ሰዎች የህይወት አድን እገዛ ይፈልጋ
–መንግስት ያገኘሁት 33 ሚልዩን ዶላር ነው ቢልም 237 ሚልዩን ዶላር ያስፈልጋል


ትናንት አርብ ለጋሽ ድርጅቶች ባወጡት ሪፖርት በኤል ኒኖ እና በዝናብ መጥፋት ምክንያት በተፈጠረ ድርቅ በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 7.5 ሚልዮን ደርሷል ብለዋል፡፡
በነሐሴ ወር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 4.5 ሚልዩን እንደሆነ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁጥሩ በእጥፍ እያደገ ይገኛል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፋጣኝ የሆነ እርምጃ ካልተወሰደ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በቀጣዩ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 15 ሚልዩን ይደርሳል በማለት አስጠንቅቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት Office for the Coordination of Humanitarian Affairs ባወጣው ሪፖርት ‹‹የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ እገዛ ለማድረግ ካልፈጠነ በስተቀር በምግብ እጥረትና ተያያዥ ችግሮቹ ምክንያት የሚፈጠረው ቀውስ አደገኛ ይሆናል››ብሏል፡፡
ዩኒሴፍ በበኩሉ 300.000 ህጻናት በምግብ ማጣት ለጉዳት እንደሚዳረጉ አስጠንቅቋል፡፡

The Famine Early Warning Systems Network ሊከሰት ስለሚችል ድርቅ ጥልቅ ጥናት በማድረግ ‹‹ምርት ከተጠበቀው በታች ››እንደሚሆን ተንብዩ እንደነበር በማስታወቅ ‹‹ባልተለመደ ሁኔታ የከብቶች መሞት ተመዝግቧል፣የቀሩት ከብቶች በጣም አነስተኛ ናቸው፣ሊሸጡ የሚችሉ እንስሳት ትንሽ ናቸው፣ከእንጨትና ከሰል ውጪ ተሸጦ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ነገር ምንም የለም፡፡ወላጆች ለቤተሰባቸው ምግብ ለመግዛት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አይደሉም››በማለት ሁኔታው አስከፊ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት በሁለተኝነት በተቀመጠችው ኢትዩጵያ 855.000 ሰዎች የህይወት አድን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሌሎች 2.3 ሚልዩን ያህል ደግሞ ረዳት አልባ ናቸው ብሏል፡፡

ኤል ኒኖ በአለም ላይ ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመርን ከማስከተሉም በላይ በተወሰኑ የአለማችን ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ዝናብና ድርቀትን ሊያስከትል እንደሚችል እየተነገረለት ይገኛል፡፡

በከፍተኛ ደረጃ የተጠቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የአፋር ምስራቅና የደቡብ ሶማሊ ክልሎች ሲሆኑ ባልተለመደ ሁኔታም በመካከለኛውና በምስራቅ ኦሮሚያ የውሃ እጥረት ተከስቷል፡፡

የምግብ እጥረት በኢትዮጵያ የተለመደ ክስተት በመሆን ተመዝግቧል፡፡በ1977 በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ርሃብ ከፍተኛው ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ባወጣው የድህነት ኢንዴክስ መሰረት 20 ሚልዩን የአገሪቱ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ፡፡የኢትዮጵያ መንግስት 33 ሚልዩን ዶላር ማሰባሰቡን ቢገልጽም የተባበሩት መንግስታት ለድንገተኛ እርዳታ የሚያስፈልገው ገንዘብ 237 ሚልዩን ዶላር መሆኑን አስታውቋል፡፡አቶ ሬድዋን ሁሴን በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ከለጋሽ ድርጅቶች ቃል የተገባልን እርዳታ በጊዜው ሊደርስልን አልቻለም ››ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ዳዊት ሰለሞን

0 comments:

Post a Comment