– ፓርቲዎቹ መቅደም ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች አስቀምጠዋል
መንግስት በነደፈው የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ውይይት ላይ ትናንትናና ዛሬ ተቃዋሚዎች እየመከሩ ሲሆን ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች መድረክ፣ ሠማያዊ እና መኢአድ በውይይቱ ላይ አልተሳተፉም፡፡
መንግስት ለሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች 20 አባሎቻቸውን አርብና ቅዳሜ በሚደረግ ውይይት ላይ እንዲያሳትፉ በደብዳቤ
ያሳወቀ ሲሆን ኢዴፓን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውይይቱ መሳተፋቸውን ሲያረጋግጡ ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች ግን
ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ በውይይቱ ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ የመንግስት እቅድ ላይ ለውይይት ከመቀመጤ በፊት በብዙሃን ፓርቲ ዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የነፃ መገናኛ ብዙሃንና ሲቪክ ማህበራትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መወያየት አለብኝ ሲል በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው የምላሽ ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
“በኢትዮጵያ ሰላምና እድገት እቅድ ላይ ከመወያየት በፊት በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ መወያየት አስፈላጊ ነው” ያለው
የፓርቲው መግለጫ፤ መሠረታዊ ጉዳዮች መፍትሔ ባልተበጀላቸው ሁኔታ በዕቅዱ ዝርዝር አፈፃፀም ላይ መወያየት ለኢትዮጵያ
እድገትና ብልጽግና ያመጣል ብሎ እንደማያምን በደብዳቤው አመልክቷል፡፡
የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ከመንግስት በቀረበለት ጥሪ
ላይ ስራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ መቅደም ያለባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች አሉ በማለት ከመሳተፍ መቆጠብን እንደመረጠ ለአዲስ
አድማስ አስታውቋል፡፡ ፓርቲው ስብሰባው ላይ ለመሳተፋ የማይችልባቸውን ሶስት ምክንያቶች ጠቅሷል፡፡ የብሔራዊ እርቅና
መግባባት ላይ ያተኮረ ስብሰባ በቅድሚያ እንዲጠራም ጠይቋል፡፡
ግዙፉ ብሔራዊ እቅድ ሁሉንም አሣታፊ በሆነ መልኩ ከግብ እንዲደርስ መጀመሪያ ሁሉንም ተቃዋሚ ያሳተፈ የብሔራዊ
መግባባትና እርቅ ጉባኤ መጠራት አለበት ያለው ፓርቲው፤ “የልማት መሠረቱ የዜጐችን ሰብአዊ መብት መጠበቅ ስለሆነ
የመኢአድ አባላትም ሆኑ ሌሎች የተቃዋሚ አባላት እየተሰቃዩ፣ እየተሳደዱ፣ እየተዋከቡ ባለበትና አጠቃላይ የሰብአዊ
መብታቸው በተገፋበት ሁኔታ እንዲሁም ዜጐች ክልልህ አይደለም በሚል እየተፈናቀሉ፣ በስብሰባው ላይ መገኘት ፍሬ ሊሰጥ
የሚችል አይደለም” ብሏል፡፡ የሚካሄደው ውይይት ለሠፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚዲያዎች በቀጥታ የሚሠራጭ ባለመሆኑ
ሃሳባችን ተቆራርጦ የተሳሳተ መልዕክት ሊተላለፍ ይችላል በሚል ስጋት ከውይይቱ ራሱን ያገለለው ደግሞ የኢትዮጵያ
ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ነው፡፡
ትናንት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው የመጀመሪያ ቀን ውይይት መክፈቻ ላይ ጠቅላይ
ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተገኙ ሲሆን “የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ቢኖሩም ያለን አንድ አገር በመሆኑ ሁሉም
አካላት በአገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መወያየትና ግብአት መስጠት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡
በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀም ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን
ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም ጽሑፍ ካቀረቡ በኋላ የፓርቲ ተወካዮቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ መልካም መሆኑን ጠቅሰው በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን
ላይ ተመዘገበ ተብሎ የቀረበው የኢኮኖሚ እድገት አሃዝ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ በተለይ የትምህርት
ጥራትን ከማስጠበቅና ግብርናን ከማዘመን አንፃር የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ተወካይ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነቱ ላይ መንግስት ትኩረት አድርጐ አልሠራም፤
በቀጣይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ተወካይ ደግሞ ከመሠረተ ልማት ግንባታና ከሃብት
ብክነት ጋር የተያያዙ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡
ትናንት በመጀመሪያው የእቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ሲደረግ የዋለ ሲሆን በዛሬው እለት በቀጣይ ሊተገበር በታሰበው
ሁለተኛው እቅድ ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ቅንጅት እና ኢራፓን
ጨምሮ 20 ያህል ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተሣታፊ መሆናቸውም ታውቋል፡
0 comments:
Post a Comment