ደግ ደጉን ስናጣ ፣ ሃዘኑ መረረ
ሞት አምላኩ ከድቶት፣ ገሎት በነበረ።
ሞት አምላኩ ከድቶት፣ ገሎት በነበረ።
የሠፈራችን ሙሾ አውራጅ
የጋሽ ሙሉጌታን ማረፍ የሰማን ብዙዎቻችን ይህቺ ሃገር ከእንግዲህ አስተማሪ የሆነ ሰው ማን ቀራት? ብለን እንድናስብ አድርጎናል። ለሃገር በርካታ ትምህርት የሚሰጡ እንደ ተንቀሳቃሸ ቤተ መጽሐፍት የሚቆጠሩ አንጋፋ የሃገራችን ጠበብቶች በሞት እየተለዩን ነው። እንደ ፕሮፌሰር አሥራት፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንንና አምባሳደር ዘውዴ ረታን የመሳሰሉ ቱባ ቱባ የሰው ሃብቶች ማጣታችን የጎዳንን ያህል የጋሽ ሙሉጌታም ህልፈተ ሕይወት እንዲሁ እንደሚጎዳን አያጠራጥረንም ።
ምናልባትም ይህ ውሉ እንደ ጠፋ ልቃቂት የተበላሸውን የሃገራችን የፖለቲካ ስርዓት እንደ ጉም በኖ አንድ ቀን የአንድነት ጥሪ የሚበሰርበት የድል ምዕራፍ ላይ ቢደረስ፣ እንደነ ጋሼ ሙሉጌታ ዓይነት ታሪክን የሚመረምሩ፣ ዘመንን የሚቆጥሩ፣ ሃገርን የሚያስከብሩ ብርቱ አርቆ አሳቢዎች እንደሚያስፈልጉን አያጠያይቅም። ይህ በጎሳ ክፍፍልን ለማምከን የተጀመረው ጸረ ዘረኝነት ትግል አንድ መልክ ሲይዝ፣ ህዝቡን ሊያሰባስቡና የአንድነትን አቅጣጫ ሊያመላክቱ የሚችሉ እውነተኛ የሃገር ሽማግሌዎች የምንሻበት ወቅት ሩቁ ላይሆን ይችላል። ከዚህ አንፃር እንደ ጋሼ ሙሉጌታ ዓይነት አዋቂዎችና የሃገር ሽማግሌዎችን ማጣት በብርቱ እንደሚጎዳን ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።
ጋሼ ሙሉጌታን ያወቅሁት ጀርመን ውስጥ በተደረገ አንድ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት ነበር። ነፍሱን ይማረውና ተፈራ አስማረና ገሞራው ካሣ አብረው መጥተው ነበር። በዚያ ወቅት በተገኘው አጋጣሚ ከእሱ ጋር ለመወያየት ችያለሁ ። ብዙም ተምሬአለሁ። ጋሼ ሙሉጌታ በወቅቱ እስከ አሁን ድረስ ብዙዎቻችን፣ በተለይም የተቃዋሚ ድርጅቶች በተግባር ያላዋሉት ነገር ግን ጠቃሚ ምክር ሰጥቶን ነበር። ባጭሩ መልዕክቱ እንደዚህ ያለ ይዘት ያለው ነበር።
“ወያኔዎችን አጥኗቸው፣ እወቋቸው ፣ አሠራራቸውን ተረዱ፣ የሚሉትን አዳምጧቸው። እነሱ እናንተን ከሚያውቋችሁ በላይ እነሱን ካላወቃችሁ ምን ጊዜም አታሸንፏቸውም። እነርሱ እኛ ውስጥ ሰርገው ለመግባት አያዳግታቸውም። እኛ ግን እነርሱ ውስጥ ሰርገን ለመግባት ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ቢሆንም ግን የተከፈለው መሰዋትነት ተከፍሎ እነርሱን ማወቅ ይገባናል ። የወያኔን አጥፊ እኩይ ዓላማ ብቻ ማወቅ በቂያችን አይደለም ። አሠራራቸውስ እንዴት ነው ? እኛን ለመከፋፈል የሚጠቀሙበት ስልትና መንገድስ ምንና እንዴት ነው ? እኛ ውስጥ ያሰረጉት ሰው ማነው ? ማነውስ በጥቅም ተደላይ ለእነርሱ የሚሠራ ? የመሳሰሉትን አስፈላጊና ጠቃሚ መረጃዎችን ሁሉ ማጥናትና ማግኘት ካልቻልን እኛ ብቻ የእነርሱ የመከፋፈል አባዜ ሰለባዎች እንሆናለን እንጅ፣ እነርሱን መለያየት ከቶ አንችልም።”
በማለት ሰፋ ያለ ምክር ሰጥቶን ነበር።
ባለፉት ሳምንታት የሞላ አስገዶምን ጉዳይ ሳነብ ጋሼ ሙሉጌታ እንደገና ትዝ አለኝ። እንዴት ይህንን ያህል ደካማ ሊኮን ይቻላል? ወያኔን መሪ እስከማድረግ የሚደርስ ድክመት እንዴት ? የሚለው ጥያቄ በአዕምሮዬ ውስጥ ተመላለሰ። በኤርትራ የሚካሄደውን ትግል መደገፍ አለመደገፍ ሳይሆን እንዴት ወያኔ ይህን ያህል ሰርስሮ ሊገባ ቻለ የሚለው ጥያቄ በቅድሚያ መልስ ይሻል። ይህ ጉዳይ በውል ካልተመለሰ ደግሞ ዛሬም ነገም ወደፊትም ያው እንደተለመደው ሽንፈት እናስተናግዳለን እንጂ ድልን ከቶ ማግኘት ምኞት ከመሆን ሌላ ትርፍ የለውም። ሞላ ስንት ወንድሞቻችንን በአሁኑ ወቅት አገር ውስጥ እንዳስጨፈጨፈ ለጊዜው ተጨባጭ የአሃዝ መረጃ በእጃችን ባይኖረንም፣ ብዙ እንደሆኑ ልቦናችን ያውቀዋል። ብዙዎች ሃገራቸውን ከወያኔ ለማዳን የሚጥሩ ተመልሰው በወያኔ እጅ ወድቀዋል። የዚህ እኩይ ተግባር ሰለባ የሆኑ በርካቶች ዛሬም እንደሚሰቃዩ መገመት አያዳግትም። ትላንት ማንዴላ ያልነው ሰው ዛሬ ባንዳ ከሆነ፣ ትላንት ቼ ጉቬራ ያልነው ሰው ዛሬ ወያኔ ሆኖ ካገኘነው፣ ትላንት የነጻው ፕረስ ታጋይ ብለን አጨብጭበን ያሸለምነው ሰው ዛሬ ራሱ የነጻ ፕረስ አፋኝ ከሆነ በእርግጥ ወያኔ እኛን ያነበናል እንጂ እኛ ወያኔን እያነበብነው አይደለም ማለት ነው።
ወያኔ እንደ ውሃ ሙላት በተለያየ መንገድ እየሰለለን ነው። ይህ መሰሪ ተግባር ወያኔ እስካለ ድረስ ዛሬም ነገም አያባራም። ከአንዳርጋቸው ጽጌ መታፈን ይሁን ከሞላ አስገዶም መክዳት የተማርነው ነገር ይህንንኑ ነው ። ክፍተቱ ምን ላይ እንደሆነ በውል ቆም ተብሎ መጠናት ይኖርበታል። በሰከነ በመደማመጥና ተቻችሎ እርስ በርስ በመማማር ስህተትን ዘወትር ለማረም ዝግጁ መሆንና ድክመትን ነቅሶ በማውጣት ቀዳዳን ለመድፈን ጠንክሮ መሠራት ይኖርበታል ። አለበለዚያ ግን “የሚሞት ልጅ አንገቱ ረዥም ነው” እንዲሉ፣ በክስረት ጎዳና እየተንደረደሩ የቅብብሎሽ ጨዋታ ከወያኔ ጋር መጫወት ነው የሚሆነው ። በዚሁ ከቀጠለ ጉዳቱም ቀላል የሚሆን አይመስለኝም።
እስካሁን በተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በሃይማኖት ድርጅቶች፣ በሲቪክ ድርጅቶች ወስጥ የታየው የወያኔ ሥራ ይህንኑ እኩይ ተግባር የሚያሳይ ነው። ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ድርጅቶችን የከፋፈሉ የጥፋት መልእክተኞች፣ ባመቱ ልማታዊ ኢንቬስተር ይሆናሉ። ቤተ ክርስቲያናትን የከፋፈሉ መነኮሳት ለጳጳስነት ሲታጩ ተገንዝበናል፣ መስጊዶችን ለወያኔ መፈንጫ ያደረጉ ጉግ ማንጉጎች ግዳይ እንደጣለ አርበኛ ይሾማሉ፣ ይሸለማሉ። በሌላም በኩል ኮምኒቲዎችን ያፈረሱ ምንደኞች የዲፕሎማቲክ ሠራተኛ ሲሆኑም ታዝበናል ። እነዚህ ተቃዋሚ ይመስሉ የነበሩ የወያኔ ደጋፊዎች ለወያኔ የተመለመሉት መጀመሪያ ሰርገው እንዲገቡ ታስቦ ይሁን ወይም መሐል ላይ በጥቅም ተደልለው ለጊዜው የምናውቀው ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ ለዚህ ያበቃን ዋናው ግድፈት ወያኔን በውል ማዳመጥ ያለመቻላችን ጉዳይ ነው። እሱ ግን አበክሮ ያዳምጠናል፣ ሰርክ ይቃኘናል። እንኳን በሕይወት ያለነውን የሞቱትን ጀግኖች ጓዶቻችንን እንኳ ትንፋሽ ለማዳመጥ ይሞክራል። ምክንያቱም ለወያኔ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንኳን ህልውናቸው ሞታቸውም ያባንነዋል። ማንን ማሰር፣ ማንን መግደል፣ የማንን ደብዛ ማጥፋት እንደሚገባው ጠንቅቆ የሚከታተለውና የሚያውቀውም ከዚህ ስጋቱ በመነሳት ነው ።
ጋሼ ሙሉጌታ ታምራት ላይኔን ከስልጣን ያስወገደው ጉዳይ ጀርመን ውስጥ በኢሕአፓ የተጀመረ ጥንስስ ነው ብሎ ያስብ ነበር። እውነቱን ለማወቅ ጥረት አድርጓል። ምን ያህል እንደሰመረለት አላውቅም ። ግን በአንዱ የጦብያ መጣጥፉ ላይ ይህንን ጉዳይ ጠቃቅሶት አንብቢያለሁ። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ደጋግሞ የኢሕአፓ አባላት ወጣቱን ትውልድ የትግል ልምዳቸውን ሊያስተምሩት ይገባል። ወያኔን ለመጣል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይችላል የሚል አቋም ነበረው። ይህ የጋሼ ሙሉጌታ አባባል ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ ዛሬም ቢሆን በውል ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል።
በጥቅሉ በቀደመው የተማሪዎች ንቅናቄና በዛ ትውልድ ወቅት የተተገበሩትን የትግል ስልቶች በጅምላ ማውገዝ ለወያኔ መቆየት ታላቅ አስተዋጽዖ እያደረገ ነው። ጠንከር ያለ ትግል የሚያወግዙ፣ የወያኔን መፈክር እያወቁትም ይሁን ሳያውቁ የሚያስተጋቡ ብዙ ናቸው። ለእያንዳንዱ የትግል ስልት ምላሽ ይሆን ዘንድ ወያኔ እንከንና አቃቂር እያወጣ ያጨናግፋል ። እኛም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አብረን እናጨበጭባለን። በሰላማዊ ትግል ላይም ቢሆን እንከን ያወጣል። እኛም አብረን እንዲሁ እናሸበሽባለን። የትጥቅ ትግልን ስለሚፈራው አጥብቆ ያወግዛል፣ በሰርጎ ገቦቹ ያስወግዛል። እኛም አብረን በእውር ድንብር በለው፣ ጣለው እንላለን። በተለይ በተማሪዎች ትግል ብሎም በኢሕአፓ የተተገበረውን የትግል ስልት ማውገዝማ የምሁርነት መለኪያ የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው። ድርጅታዊ ዲስፕሊን የእስታሊናዊ የትግል ስልት የሚመስላቸው የዋሆች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። የድርጅትን ምስጢር አደባባይ ላይ ካልተናገሩ የዴሞክራሲ መብታቸው የተነፈገ የሚመስላቸው የዋሆች እስካሉ ድረስ ድል መዳረሻዋ ሩቅ ነው የሚሆነው። ለትጥቅ ትግል ጫካ ገባሁ የሚል መሪ ያልተጤነ ጽሁፍም ይሁን በውል ያልተመከረበት ቃለ መጠይቅ መስጠት ጉዳቱ የትየለሌ ነው።
በእኛ በደልቃቆቹ መንደር ዛሬ በዴሞክራሲ ስም የድርጅትን ምስጢር አደባባይ መንዛት ፋሽን ሆኗል። በእኛ በዘመናዊ ታጋዮች ጎራ የድርጅት ዲስፕሊን እንዲቀር ይሰበካል። የሕብዕ አሰራር ወያኔን እስካልጠቀመው ድረስ እስታሊናዊ ነው እየተባለ መወገዙ ይቀጥላል ። ዛሬ መስዋዕትነት መክፈል ያረጀ ያፈጀ አሰራር እንደሆነ ይደሰኮራል። እኛም ይህንን ተቀብለን አብረን እናራግባለን። በሕብዕ መደራጀት ያስፈልጋል ሲባል ኢሕአፓ ነበርክ እንዴ? ይባላል። ወያኔ በትጥቅ ትግል መውረድ አለበት ከተባለ ደግሞ በመሣሪያ ስልጣን ላይ የወጣ ዴሞክራሲን ስለማያመጣ ይህን በሩቁ ይባላል። ሰላማዊ ትግል ከተባለ ደግሞ ወያኔ በሰላማዊ ትግል አይወርድም እያልን እንገለገላለን። ለሁሉም የትግል ዓይነቶች በወያኔ ሰርጎ ገቦች የተቀነባበረ መልስ ይዘጋጅለታል። እኛም እሱን እያቀነቀንን እናስተጋባለን። ለየዋህ ፖለቲከኞች የዴሞክራሲ መብት መቃወም እንጂ መደገፍ እንዳልሆነ ማሰብ ከጀመሩ ሰንብተዋል። “በውቤ ጊዜ የደነቆረ ፡ በውቤ አምላክ ሲል ይኖራል” እንዲሉ።
የሰላማዊ ትግል አከተመ ብለን ካመንን፣ በኤርትራ የሚደረገው ትግል ውጤቱ ያጠራጥራል ካልን፣ ባያጠራጥርም በቂ አይደለም ብለን የምናምን ከሆነ፣ የሚቀረን በሕብዕ ተደራጅቶ በሃገር ውስጥ ወያኔን መግቢያ መውጫ ማሳጣት ነው። ለዚህ ደግሞ ከኢሕአፓ ይሁን ከሌሎች ድርጅቶች የተገኘው ልምድ ወሳኝ ነው። ዲስፕሊኑን፣ የአደረጃጀት ስልቱን እና የመሳሰሉትን መቀበል የማይቀር ነው። የሃገር ውስጥ የሕብዕ ትግል ከተጀመረ ደግሞ ወያኔን መስማት፣ ማድመጥ፣ ወደ ውስጥ በጥንቃቄ ሠርጎ መግባት ያስፈልጋል። ያም ሲባል ቂጥ ገልቦ ክንብንብ ዓይነት ሊሆን አይገባም። በብርቱ ጥንቃቄ የተነደፈ ስልት መከተልና ለማስፈጸም ብቃት ያለው አመራርና ድርጅታዊ መዋቅር ያስፈልገዋል። ጋሼ ሙሉጌታ ሊያስገነዝበን የፈለገው ይህንን መሰል ጭብጥ ነበር።
ጋሼ ሙሉጌታ በሕይወት በነበረበት ወቅት ብዙ ሊያስረዳን ታግሏል። ነገር ግን ሰምተነዋል እንጂ አላዳመጥነውም። በርካታ ጽሁፎቹን አንብበናል እንጂ ምን እንደሚያስረዳን በውል አላጤነውም። እንዲያውም ይባስ ብለን በሕይወት ሳለ ያልተናገርነውን ከህልፈቱ በኋላ ብዙ ዝባዝንኬዎችን የምናወራ፣ ከወያኔ የስም ማጥፋት አልበም እየቀዳን ልናስተጋባ የምንሞክር ህሊናችንን የካድን በርካቶች ነን። ይህ ደግሞ በጣም አሳፋሪ ተግባር ነው።
ወያኔ ጀግኖቻችን ከዚህ ዓለም ካለፉም በኋላ አይተዋቸውም። ለአብነት ብናነሳ፣ ሎሬት ጸጋዬ ከአረፉ በኋላ ወያኔ በጣም ተረብሾ ነበር ። በተለይ ቀብራቸው ሃገር ውስጥ መፈፀሙን ሲያውቅ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር ። አበባው መላኩ የሚባል ገጣሚ “ለአባት ዓለም ጸጋዬ” በሚል ርዕስ እንዲህ ገጥሞ ነበር ፡ –
. . .
የምእመንህን መጨነቅ ፣ የሕዝብህን ማዘንን አውቆ፣
በሲዖል ደቼ ተቦክቶ ፣ የተሠራ ግንባሩ ቆጥሮ፣
ስምክን ለምን ስምቼው አለ ገድልህስ ለምን ተነግሮ።
በሲዖል ደቼ ተቦክቶ ፣ የተሠራ ግንባሩ ቆጥሮ፣
ስምክን ለምን ስምቼው አለ ገድልህስ ለምን ተነግሮ።
አጀብ ነው ! ያንተስ ጸጋዬ፣
ለሌላ ያልነገርኩትን ትዝብቴን በፊትህ ላውራ፣
በመብረቅ ከተገመደው ጅራፉ ቅኔህ ካለበት ፣
ከሕይወት ዘመንህ ይልቅ ዛሬ ሞትህ ተፈራ ።
በመብረቅ ከተገመደው ጅራፉ ቅኔህ ካለበት ፣
ከሕይወት ዘመንህ ይልቅ ዛሬ ሞትህ ተፈራ ።
ገሃነብ ድረስ በርግጎ ጠላትህ የተሸበረው
ያኔ ስትኖር አይደለም ሞትህ ሲገር ዛሬ ነው ።
ሞትህ ሲነገር ዛሬ ነው።
ያኔ ስትኖር አይደለም ሞትህ ሲገር ዛሬ ነው ።
ሞትህ ሲነገር ዛሬ ነው።
0 comments:
Post a Comment