ኢህአዴግ ከቀድሞ ሊቀ-መንበሩ አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በተከሰተበት ውስጣዊ ልዩነት በተለዋዋጭ የኃይል ሚዛን ሥር ለማደር በመገደዱ የስልጣኑን መዘውር የሚያሽከረክረውን አካል ለመለየት አዳጋች ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ሽኩቻ መፍትሄ ማግኘቱን የሚያመላክቱ ሁናቴዎች መፈጠራቸውን የውስጥ አወቅ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
እንደ መግቢያ
ድንገቴው የመለስ ህልፈት ህወሓትን ቢከፍለውም፣ ብአዴን ራሱን እንዲያጠናክር መደላድል ፈጥሮለታል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መለስ ዘመኑን ሙሉ በብአዴን ታማኝነት ላይ ጥርጣሬ ስላልነበረው ቀድሞውንም እንዲዳከም ባለማድረጉ ይመስለኛል፡፡ እርሱ በአይነ ቁራኛ ይጠብቀው የነበረው ህወሓትን ነበር፤ በተለይም በሠራዊቱ እና በደህንነቱ ውስጥ ‹‹ተፅእኖ መፍጠር ይችላሉ›› የሚባሉት አቦይ ስብሃት ነጋ እና የትግራይን መዋቅር በእጁ ያደረገው የቀድሞ የክልሉ አስተዳዳሪ ፀጋዬ በርሄ በጥርጣሬ ዓይን የሚታዩ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በምርጫ 2002ቱ ማግስትም ድርጅቱ አቦይን ‹‹በክብር›› እንዲሸኝ ሲደረግ፣ ፀጋዬ በርሄን ደግሞ ‹‹አማካሪ›› በሚል ሽፋን ከመቀሌ ወደ ቤተ-መንግስት (ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ) አዛውሮ በቅርብ እይታ ስር በማዋሉ ሁለቱንም ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል፡፡ በግልባጩ አዜብ መስፍንና ‹የመለስ ታማኞች› የሚባሉት እነአባይ ወልዱና ቴዎድሮስ ሀጎስ የፖሊት ቢሮውን ተቀላቅለዋል፡፡ ሁነቱም ከእነአቦይ ጋር በስጋ ዝምድናና በጋብቻ የተሳሰሩ ባለስልጣናትን በማስከፋቱ በድርጅቱ ውስጥ ብቻ የሚታወቅ (አደባባይ ያልወጣ) ልዩነት ፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል (በነገራችን ላይ ኦህዴድ የማዳከሙ ሴራ ሰለባ ነው፡፡ ይህ ሁናቴ ከመለስ ህልፈትም በኋላ ቀጥሏል፤ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የግንባሩ አባል ድርጅቶች፣ የየራሳቸውን ጠቅላላ ጉባኤ ባካሄዱበት ወቅት ብአዴን በ‹ክብር› ካሰናበተው ሁለት ዓመት ያለፈውን መሪውን አዲሱ ለገሰን ወደ ቦታው መልሶ ራሱን ሲያጠናክር፣ በተቃራኒው ኦህዴድ አንጋፋ አመራሮቹን፡- አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳና ግርማ ብሩን ከስራ አስፈፃሚነታቸው እንዲያነሳ ተገድዷል፡፡ ይህንን ነው መተካካት የሚሉትም፡፡
ህወሓት
የመለስን ህልፈት ተከትሎ በውስጡ ያደፈጠው ቅራኔ ፈንቅሎ በመውጣቱ ህወሓትን የ‹መቀሌው› እና የ‹አዲስ አበባው› በሚል ለሁለት ከፍሎት ነበር፤ ይህ ግን የመቀሌው-በአዲስ አበባ፤ የአዲስ አበባው-በመቀሌ ደጋፊ አልነበረውም እንደማለት አይደለም (የመቀሌውን አዜብ መስፍን፣ አባይ ወልዱ፣ ቴዎድሮስ ሀጎስ… መርተውታል፤ የአዲስ አበባውን ደግሞ አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃዬ፣ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ ታጋዮች ዘውረውታል)፡፡ ይህ አጋጣሚም ከእነ አዜብ ቡድን ጋር ትብብር የፈጠረውን ብአዴንን ለጊዜያዊ ድል አብቅቶት ነበር (በ93ቱ ክፍፍልም የብአዴን ድጋፍ መለስ በአሸናፊነት እንዲወጣ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ ይታወሳል)፡፡ አቦይ ስብሃት ነጋ በትግርኛ ቋንቋ በሚታተመው ‹‹ውራይና›› መፅሄት ላይ ‹‹ህዝቢ ትግራይ ዘቃልሶ ኣቃሊሱ ዝጠቕሞ ወያናይ ውድብ ይግብኦ›› (የትግራይ ህዝብ የሚያታግለው፣ ታግሎም የሚጠቅመው ወያኔያዊ ድርጅት ይገባዋል) በሚል ርዕስ በፃፉት ፅሁፍ ችግሩን እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡-
‹‹አባይ ወልዱም ባለፈው የህወሓት ጉባኤ ላይ በተደጋጋሚ ‹ህወሓት ውስጥ ማጠለሻሸትና (የሥልጣን) ሽኩቻ በስፋት እየተስተዋለ ነው› በማለት ሁኔታውን ገልፆታል፡፡ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ ደግሞ የለም፡፡ እንዲህ ያለ በኃይል አሰላለፍ ደረጃ ሊታይ የሚችል የአንድን የፖለቲካ ድርጅት አቅም ከማዳከምና መርሀ-ግብሩን ከማሰናከል አልፎ ተርፎም ድርጅቱን ለአስከፊ ውድቀት ሊጥል ከሚችል አደገኛ ሁኔታ የበለጠ አደጋ ያለ አይመስለኝም፡፡›› (‹ውራይና› ቁጥር 4 ነሐሴ 2005 ዓ.ም)
ከኃይለማርያም ጀርባ
ኃይለማርያም ደሳለኝ የግንባሩ ሊቀ-መንበር በመሆኑ ጉዳይ ላይ ብአዴንም ሆነ ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ቅሬታ አልነበራቸውም፤ ምክንያቱም እርሱም ሆነ ‹ደቡብን እወክላለሁ› የሚለው ድርጅቱ ለአሸናፊ ኃይል ከማገልገል አልፈው የፖለቲካ አመፅ ሊያስነሱ እንደማይችሉ ይታወቃልና፡፡ ይሁንና በወቅቱ ኃይለማርያም ሰልፉን በ‹መለስ ባርኔጣ› ከሚንቀሳቀሰው ከመቀሌው ህወሓትና ብአዴን ጋር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝበማስተካከሉ የኃይል ሚዛኑ በአንፃራዊነት ወደእነርሱ እንዲያጋድል አድርጓል፡፡ በግልባጩ ለእነ አቦይ እና ደጋፊዎቻቸው የመሸነፍ መገለጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ እንግዲህ እስከ ዘጠነኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ድረስ ‹መልከ-ኢህአዴግ› በዚህ መልኩ ነበር የቀጠለው፡፡
‹መፈንቅለ-ህወሓት›
ብአዴኖች፣ ከመቀሌው ህወሓት ጋር የፈጠሩትን ግንባር፣ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ካገኙት ድጋፍ ጋር በማዋሀድ፡- የአዲስ አበባውን ህወሓት የአመራር አባላት ሙሉ በሙሉ፣ የደህንነት ሀላፊው ጌታቸው አሰፋን እና አንጋፋ የህወሓት ታማኝ ጄነራሎችን ከመንግስታዊውም ሆነ ከፓርቲው ኃላፊነታቸው በማንሳት በአሸናፊነት ለመወጣት ስልታዊ እንቅስቃሴ አድርገው እንደነበር ለድርጅቱ ቅርብ ከሆነ ሰው አረጋግጫለሁ፡፡ በባህርዳሩ ጉባኤ ላይም መላኩ ፈንቴ ‹አላሰራ አሉኝ› ብሎ በአደባባይ እንዲያጋልጣቸው ከተደረጉት የንግድ ደርጅቶችና ሀብታም ነጋዴዎች አብዛኞቹ ከአዲስ አበባው ህወሓት ጋር የተሳሰሩ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ኩነቶችም ነው ‹መፈንቅለ-ህወሓት› ለማለት የተገደድኩት፡፡ ሴራው የከሸፈው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፤ የመጀመሪያው በሰውየው ህልፈት ማግስት (ተተኪው ጠቅላይ ሚንስትር ገና ባልተመረጠበት) እነአባይ ፀሀዬ ሶስት ሜጀር ጄነራል እና ሰላሳ አራት ብርጋዴር ጄነራሎች (አብዛኞቹ የህወሓት ሰዎች ናቸው) መሾማቸው ኃይላቸውን ሲያጠናክርላቸው፣ በአንፃሩ የመቀሌውን ህወሓትና ብአዴንን በሠራዊቱ ውስጥ የነበራቸውን ተፅእኖ ከማዳከሙም በላይ ኃይል የማሰባሰብ ሩጫቸውንም ገትቶታል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በደህንነት
መስሪያ ቤቱ አቀናባሪነት በ‹ፀረ ሙስና› ሽፋን የተከፈተው ዘመቻ ነው፤ እነበረከትንም ስልታቸውን መልሰው እንዲያጤኑ ያስገደዳቸው ይህ አይነቱ አስደንጋጭ እርምጃ ይመስለኛል፡፡
መስሪያ ቤቱ አቀናባሪነት በ‹ፀረ ሙስና› ሽፋን የተከፈተው ዘመቻ ነው፤ እነበረከትንም ስልታቸውን መልሰው እንዲያጤኑ ያስገደዳቸው ይህ አይነቱ አስደንጋጭ እርምጃ ይመስለኛል፡፡
የህወሓት ‹ቆሌ›
የኢትዮጵያን ልማዳዊ ፖለቲካ ከነሴራው ጠንቅቀው ከተረዱት ጥቂት ሰዎች መሀል አቦይ ስብሃት ነጋ አንዱ መሆናቸው ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ አቦይ ህወሓትን ጠፍጥፎ በመስራቱም ሆነ በስልጣን ለማቆየት የመለስን ያህል (ሊበልጥም ይችላል) ለፍተዋል፡፡ ዛሬም ተፈጥሮ ላመጣባቸው እርጅና እጅ ሳይሰጡ በህወሓት ላይ የሚሴረውን-ለመበጣጠስና ለተቀናቃኞቻቸው-ጉድጓድ ለመቆፈር እንደማይሳናቸው አሳይተዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ነው ‹የህወሓት ቆሌ› የሚል ቅጥያ ያሰጣቸው፡፡
ከመለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው ጥብቅ የመተባበር መንፈስም ከጓዳዊነትም በላይ እንደነበር የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ግና ይህ የጦፈ ፍቅራቸው ከ2000 ዓ.ም ወዲህ መደብዘዝ ጀምሮ ነበር፤ ልዩነታቸውም ቅስ በቀስ እየሰፋ ለመምጣቱ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ አንዱ መለስ፣ ለአዜብ መስፍን እየሰጠ የነበረውን የፖለቲካ ጉልበት፣ አቦይ ‹ህወሓትን በሴት ቀሚስ እንደማሳደር› አድርገው መውሰዳቸው ነበር፡፡ ሌላው የሴቲቱ ኃይለኝነት የአቦይን የተሰሚነት ክልል ከመፈታተን አልፎ በአደባባይ ክብራቸውን እስከ መዳፈር መድረሱ ይመስለኛል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ከመለስ ጋር ተገናኝተው መነጋገር አልቻሉም፤ ለህወሓት ቅርብ የሆኑ ወዳጄ እንደነገሩኝ መለስ ህይወቱ ሲያልፍ አቦይን ካገኛቸው ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል፤ ምክንያቱ ደግሞ እርሱ ማግኘት ባለመፈለጉ ነበር፤ ይህም ሆኖ አቦይ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም በልዩ ረዳቱ አማካኝነት ‹አስቸኳይ ጉዳይ ላይ ነው› እያስባለ መልሷቸዋል፤ በስራ አጋጣሚ ከቢሮ ውጪ ሲገናኙም ‹አጣዳፊ ስራ ስለተደራረበብኝ ነው፤ እኔ ራሴ አስጠራሀለሁ› እያለ ለሁለት ዓመት ያህል ሲርቃቸው ከቆየ በኋላ ነበር ድንገት ህይወቱ ያለፈው፡፡
አቦይ ወደ ህወሓት ተመልሰው በንቃት መሳተፍ የጀመሩት የመለስን ጤንነት ሲከታተሉ የነበሩ ሐኪሞች ‹ተስፋ የለውም› ባሉበት ማግስት ነበር፤ እንደምክንያት ያስቀመጡት ህወሓት ከድህረ-መለስ በኋላ፣ የብአዴንን የትከሻ ግፊያ መቋቋም አይችልም የሚል ስጋትን ነው፡፡ የሰውየው መጨረሻ ከታወቀ በኋላም የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ የታየው የኃይል ሚዛን ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ በወቅቱም አቦይ ‹መፍትሄ› ብለው ያቀረቡት ‹ብአዴንና ከጎኑ የተሰለፉትን የህወሓት የአመራር አባላትን ማሸነፍ ስለማንችል፣ አንጃው (የእነ ስዬ ተወልደ ቡድን) ተመልሶ ያጠናክረን› የሚል ነበር፤ በስማቸውም ‹‹ውራይና›› መፅሄት ላይ በፃፉት (ርዕሱ ከላይ በተጠቀሰው) ፅሁፍ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ገልፀውት ነበር፡-
‹‹…ሁላችንም ህወሓት ውስጥ እያለን እኮ አንጃው ድርጅቱን ተቆጣጥሮት በትረ-መንግስቱንም ሊጨብጥ ተቃርቦ ነበር፡፡ በአንጃው የመዋጥ አደጋ ጊዜ ሁላችንም ተኝተን ነበር፡፡ እነዚያ የተሰናበቱት ሰዎች በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ቢቆዩ ኖሮ ይተኙ ነበር ማለት ግን አይደለም፡፡ አሁን ላለው አመራር ይደግፉት ነበር ይሆን ማለቴ ነው እንጂ፡፡ …ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የወጣ ሁሉ እንደአዲስ ተደራጅቶ አሁን ላለው ማ/ኮሚቴ እገዛ የሚያደርግበትን መንገድ ማፈላለግ አለበት፡፡…›› (‹ውራይና› ቁጥር 4 ነሀሴ 2005 ዓ.ም)
ሆኖም አባይ ፀሀዬ፣ አርከበ እቁባይ፣ ፀጋዬ በርሄ፣ ጌታቸው አሰፋን የመሳሰሉት ‹በጭራሽ አይሆንም! የእነርሱ መመለስ ያውከናል› የሚል አቋም በመያዛቸው ሃሳቡ ተፈፃሚ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ከዚህ በኋላ የእነ አቦይና አባይ ቡድን ‹ህወሓትን ማዳኛ› ያለውን ሁለት ወሳኝ እርምጃ ወስዷል፤ ከህግ ውጪ ሶስት ሜጀር እና ሰላሳ አራት ብርጋዴር ጄነራሎችን ሲሾም፣ በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበረውን ወ/ስላሴ ወ/ሚካኤልን ከየትኛውም አይነት ‹ኦፕሬሽን› እንዲገለል አደረገው፤ ቀጥሎ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከሀላፊነቱ አነስቶታል፡፡ በዚህ በኩል ያገኙትን የፖለቲካ ጉልበት በመመንዘር ከህገ-መንግስቱም ሆነ ከተለምዶአዊው አሰራር በማፈንገጥ ተጨማሪ ሁለት ም/ጠቅላይ ሚንስትሮች እንዲሾሙ ጫና ፈጥረው ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ ኃ/ማርያም ደሳለኝን በቅርብ ርቀት እንዲከተል አድርገዋል (በነገራችን ላይ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመረጠበት ወቅት ወልደስላሴ ሲጠቆም፣ ጠንካራ ተቃውሞ አቅርቦ እንዳይመርጡት ያነሳሳበት የደህንነቱ ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ ሲሆን፣ በአንፃሩ ጌታቸው የተጠቆመ ጊዜ ወልደስላሴ እና ገብረሃዋድ ተቃውሞውን ቢያስተባብሩም ታናሽ ወንድሙ በላይ አሰፋን ጨምሮ ከመመረጥ ማደናቀፍ አልቻሉም፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወልደስለሴና ገብረሃውድ በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ)፡፡
ሌላኛው የህወሓት ‹ጠባቂ መልአክ› አባይ ፀሀዬ ነው (በ2005 ዓ.ም ወርሃ ጥቅምት በታተመችው ‹አዲስ ታይምስ› መፅሄት ላይ አባይ፣ መለስ ያደረገውን ማድረግ የሚችል /ከንግግር ችሎታ በቀር/ አደገኛ ሰው መሆኑን መግለፄ ይታወሳል) ዘግይቶም ቢሆን ቡድኑን የበላይ ባደረገው የ‹ፖለቲካ ጨዋታ› እርሱም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ታይቷል፡፡ ደብረፅዮንም ቢሆን ከህወሓት ጋር ባሳለፈው ዘመን ‹ትጉህ ደቀ-መዝሙር› ስለነበር ያካበተው ልምድ ህወሓትን በታደገው ንቅናቄ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሆነው ሆኖ እነ አባይ ከባህርዳሩ ጉባኤ በኋላ ነው ‹ከመከላከል ወደ ማጥቃት› ተሸጋግረው ብአዴንንና የመቀሌውን ህወሓት በ‹ሙስና› ስም ሰለባ ያደረጉት፡፡ ይህንን እውነታም የሚያጠናክርልን አቦይ ስብሃት ‹‹ውራይና›› መፅሄት ስለ ጉዳዩ ጠይቋቸው የሰጡት ምላሽ ነው፡-
‹‹አሁን በእስር የሚገኙት [እነመላኩ ፈንቴን ማለታቸው ነው] ሙሰኞች ብቻ አልነበሩም፡፡ የፖለቲካዊ ኃይል አሰላለፍንም ሲለውጡ የነበሩ ናቸው፤ ያስፈራሩም ነበር፤ ‹የስልጣን ሹዋሚም ሻሪም እኛ ነን› አስከማለትም ደርሰው ነበር፡፡›› (‹ውራይና› ቁጥር 2 ሠኔ 2005 ዓ.ም)
የብአዴን የአመራር አባል የሆነ አንድ ሚንስትር ለእስር ሲዳረግ፣ ሌላ ሚንስትር ደግሞ ከኃላፊነቱ መነሳቱ ይታወቃል፡፡
አዲሱ ግንባር
ብአዴን የአዲስ አበባው ህወሓት ክንደ-ብርቱ እየሆነ በመምጣቱ፣ የእነ አዜብን ቡድን አውላላ ሜዳ ላይ ትቶ አብሮ ለመስራት ተደራድሯል፡፡ እነ አባይም ‹ከብአዴን ተሻርኮ ሊያስበላን ነበር› ያሉትን የመቀሌውን የህወሓት ኃይል ከሞላ ጎደል ሲያስገብሩት፣ የቡድኑ መሪን አዜብ መስፍንን ደግሞ ከኤፈርት ከማሰናበታቸውም በላይ የፓርላማ ወንበሯን የሰዋችለትን የአዲስ አበባ የከንቲባነት ምኞቷን አጨልመው፣ በመለስ ፋውንዴሽን ገድበዋታል (የመለስ ሙት ዓመት በተከበረበት ወቅት የትግሉን ዘመንና የመለስን ገድል በኢቲቪ ሲተርኩልን የነበሩት የታሪኩ ዋና ተዋንያን አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ሳሞራ የኑስ…ሲሆኑ፣ በህልፈቱ ሰሞን ግን መድረኩን ተቆጣጥረውት የነበሩት ብአዴኖች፣ እነኩማ ደመቅሳ እና ትግሉን በመፅሀፍትና በቴሌቪዥን የሚያውቁት እነ ሬድዋን ሁሴን መሆናቸውን ስናስታውስ የእነ አባይ ፀሀዬ ህወሓት ምን ያህል ተገፍቶ እንደነበረ እንረዳለን፡፡)
በአናቱም ብአዴን የበላይነቱን በጨበጠበት ወቅት እንደ ስጋት ቆጥሮት ‹ሊፐውዘው› አስቦ የነበረውን መከላከያም፣ ከድርድሩ በኋላ በሁለቱ ኃይሎች ስምምነት ለአምስት ቀናት ኪራይ ሰብሳቢነትን እና ሙሰናን በተመለከተ ብቻ ተገማግሞ እንዲታለፍ ተደርጓል፡፡ ከኃላፊነታቸው ለማንሳት የታሰቡት ጄነራሎች ጉዳይም ‹ያልታሰበ አደጋ ሊያመጣ ይችላል› በሚል ለጊዜው ተዘሏል፡፡ ይሁንና ኤታማዦር ሹሙን ጄነራል ሳሞራ የኑስን በዚሁ ዓመት መጨረሻ በ‹ክብር› ሸኝቶ፣ ጄነራል አበባው ታደሰን የመተካት ዕቅድ መኖሩን ምንጮች ጠቁመዋል (ከዚህ በኋላ በጡረታ የሚሰናበቱ ጄነራሎች ‹መከላከያ ቴክኖሎጂ› /መቴክ/ በሚመራውና ወደፊት በሚያቋቁማቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በስራ-አስኪያጅነት ወይም በቦርድ አባልነት እንደሚመደቡ ቃል ተገብቶላቸዋል)
ከኃ/ማርያም ጀርባ ያደፈጠ-ስውር እጅ
በሁለቱም ቡድን ካሉ ምንጮቼ ‹‹ኃ/ማርያም ስራው ከብዶታል›› የሚል ቅሬታ እንደነበራቸው ሰምቻለሁ፤ ይሁንና መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው በረከት ስምዖንን የጠቅላይ ሚንስትሩ ‹የፖሊሲና ጥናት ምርምር› አማካሪ በሚል ሹመት በጽ/ቤቱ ማስቀመጥን ነው፤ እርሱሁሉንም ነገር ከጀርባ ሆኖ እንዲያከናውን ወስነዋል፡፡ በረከት የተመረጠው ‹ከመለስ ጋር በቅርብ ስርቷል፣ መለስ ያነበበውን አንባቧል፣ የመለስን የዕለት ተዕለት ሥራ በቅርብ ተከታትሏልና መንገድ ይመራል› በሚል እንደሆነ ምንጮቼ ነግረውኛል (በነገራችን ላይ መለስ ሞት ባይቀድመው ኖሮ የወደፊት ዕቅዱ ቤተ-መንግስቱ ውስጥ ጀምሮት የነበረውን ግንባታ አጠናቅቆ፣ ከ2007ቱ ምርጫ በኋላ ስልጣኑን፣ ከአሻንጉሊቶቹ ለአንዱ አስረክቦ፣ መኖሪያውንም ወደ አዲሱ ህንፃ አዛውሮ፣ በለቀቀው ቤት ውስጥ የሚያስገባውን ጠቅላይ ሚንስትር ከጀርባ ሆኖ መዘወር ነበር፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ህልፈቱን ተከትሎ ግንባታውም የተቋረጠው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ግንባታው ሊቀጥል እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በረከት ስምዖን እንዲገባበት ታስቦ ይሆን? …አባይ ፀሀዬም ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የጠቅላይ ሚንስትሩ ‹አማክሪ› ሆኖ እንደሚሾም ‹ፎርቹን› ጋዜጣ በ‹ጎሲፕ› አምዱ አትቷል፡፡ መቼም ኃ/ማርያም ‹‹ሰርክ ‹እኔም አንደ ዳዊት ጨርቄን ልጣልለት› እያልኩ እዘምርለታለሁ›› ያለን አምላኩ ካልታደገው በቀር፣ ከእነዚህ ጉልበታም ሰዎች በጤና መውጣቱን እንጃ!)
ህወሓትና ብአዴን ልዩነታቸው መፈታቱን ለማሳየት፣ በረከት ስምዖን ከአዲሱ ሹመት በኋላ በሃያ ሁለት ዓመታት የስልጣን ዘመኑ አድርጎት የማያውቀውን መንግስትን ወክሎ (በግሉ ሄዶ ሊሆን ይችላል) በትግራይ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የስራ ጉብኝት አካሄዷል፡፡ ‹ድምፀ ወያኔ› የተባለው የክልሉ ሬዲዮ ጣቢያም ጉብኝቱን ሳምንት ሙሉ ሳይታክት ደጋግሞ አስተላልፎታል፡፡
ሽራፊ-መረጃ
የአቦይ ስብሃት ነጋ ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ ተከስቶ ከነበረው ክፍፍል በአሸናፊነት መውጣቱ ከተረጋገጠ በኋላ አዲስ ወሬ እየተሰማ ነው፡፡ ይኸውም ‹ህወሓት የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታውን በመልቀቁ፣ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሚያስረክቡትን ወንበር አቦይ ስብሃት መያዝ አለባቸው› የሚል ነው፤ ምንም እንኳ ሃሳቡ ተፈፃሚነት ባይኖረውም፣ ምንጮቼ አቦይ ራሳቸው በዘወርዋራ መንገድ ያሰራጩት ወሬ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ አዜብ መስፍንም ቦታውን የመያዝ ፍላጎት ያላት ይመስለኛል፡፡
ብዙ ሲባልለት የቆየው የድህረ-መለስ ኢህአዴግ ከላይ ለማቅረብ በሞከርኩት መንገድ ግራና ቀኝ ሲዋልል፣ የመከፋፈል ተግዳሮትን ሲሻገርና እንደገና እየተመለሰ ሲሰባሰብ እዚህ ደርሷል፡፡ በዚህ ኮሮንኮቻማ ሂደት ውስጥ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሚና ‹እዚህ ግባ› የምንለው እንዳይመስለን ሆኗል፡፡ ኃይለማርያም መንግስታዊ ብቻ ሳይሆን የፓርቲው ሊቀ-መንበርነትን የመሰለ ጠንካራ ፖለቲካዊ ስልጣን መያዙ ይህ ሰው የሚባለውን ያህል የዳር ተመልካች ሆኖስ ይቆያልን? ለሚለው ጥያቄ ቀጣይ ጊዜያቶች ብቻ መልስ ይኖራቸዋል፡፡ የጠቀስኳቸው የስርዓቱ ጉምቱ ሰዎች በዚህ መልኩ እየተንቀሳቀሱም ቢሆን፣ ይህን የኃይል መገዳደር እያደረጉ ያሉት በስልጣን ሞኖፖሊ ላይ ተቀምጠው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እናም ባቀረብኳቸው ሂደቶች እያለፉም ይሁን አይሁን ለስልጣናቸው የሚያሰጋ ጠንካራ የታቃውሞ ስብስብ አለመኖሩን ማመናቸው ይመስለኛል፣ የኃይል ትንቅንቁን ‹ግዜው አይደለም› ብለው ለማራዘም ሳይጠነቀቁ በግላጭ እርስ በእርስ የተፋለሙት፡፡
የሆነው ሆኖ የፓርቲው የታሪክ ድርሳን እንደሚነግረን ‹ይሆናሉ› የተባሉት ተቀልብሰው፣ ባልተጠበቁ ሁነቶች (የኃይል መገለባበጥ ተከስቶ) ፖለቲካው የሚመራበት አጋጣሚ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም መዘንጋት አያስፈለግም፡፡